ቅድስት መንበር ጦርነቶች እና ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ሥርዓት ላይ አደገኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው ገለጸች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም ተቋማት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፈርናንዶ ቺካ አሬላኖ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጉልህ የሆነ መስተጓጎል ባጋጠማቸው የግብርና ሥርዓትን በማስመልከት ቅድስት መንበር ያላትን ስጋት የገለጹ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ይሄንን ጥሪ ያቀረቡት ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ማክሰኞ ዕለት በታጃኪስታን ዋና ከተማ ዱሻንቤ በተካሄደው 35 ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የግብርና ድርጅት የአውሮፓ ክልላዊ ጉባኤ ላይ መሆኑ ተነግሯል።
ሞንሲኞር ቺካ አሬላኖ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ‘ማንኛውም ሰው በሰላም እንዲኖርና የተሟላ ሕይወት እንዲመራ የሚያስችለውን ምግብ የማግኘት መብት እንዳለው’ በመግለጽ፥ የጉባዔውን ግብ የግብርና ሥርዓትን ማበረታታት መሆን እንደሚገባው አሳስበው፥ በቅርቡ በተከሰቱት ዓለም አቀፍ ቀውሶች የምግብ ዋስትናን ለማጎልበት እንዲቻል ተጨባጭ እርምጃዎችን የመውሰድ አስፈላጊነት በአጽንዖት ገልጸዋል።
‘ርህራሄ የለሽ ጦርነቶች፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታዎች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የገበያ ተለዋዋጭነት ጥምረት ለዓለም የምግብ ሥርዓት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠሩን’ ያመላከቱት ሞንሲኞር ቺካ፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ግጭቶች የዓለም የምግብ ገበያዎችን ማወካቸውን፤ ከእነዚህም መካከል የእህል ምርትን እና የማዳበሪያ አቅርቦትን በእጅጉ የጎዳውን የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፣ እንዲሁም እየተካሄደ ያለው የኢራን እና የአሜሪካ ጦርነት የነዳጅ እና የማዳበሪያ ዋጋን ከፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ሞንሲኞር ቺካ አሬላኖ ከዚህም ባሻገር በዋና ዋና ከተሞች ላይ ለከፋ የምግብ እጥረት እና የአስከፊ ረሃብ መባባስ ምክንያት የሆነውን በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ግጭቶች በአካባቢ የምግብ ሥርዓቶች ላይ አስከፊ ችግር ማስከተሉን ጠቅሰው፥ ሃገራት “በወንድማማችነት ተስማምተው” ለመራመድ እንዲችሉ ጣልቃ-ገብነትን በማስተባበር ይህንን “በጣም አሉታዊ አዝማሚያ” እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“ዋናው ግብ ሁሉም የሰው ልጅ የተረጋጋ እና ቋሚ የሆነ በቂ፣ አልሚ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ እንዲያገኝ ማስቻል ነው” ያሉት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢው፥ የአውሮፓ ሀገራት “ማህበራዊ ፍትህን፣ የአካባቢ ዘላቂነትን እና የሰውን ልጅ ማክበር የሁሉም የህዝብ እና የግል እርምጃዎች መሪ መርሆች” ወደሆኑት የምግብ ሞዴሎች ለመሸጋገር የህግ ማዕቀፎችን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሊቀ ጳጳስ ቺካ በዓለም የግብርና ሥርዓት ላይ የመቋቋም አቅምን መገንባት በጊዜያችን ካሉት በአስቸኳይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ተመሳሳይ የምርት ዘዴዎችን ከመጠቀም ይልቅ ምግብ የሚመረትበት መንገድ እንዲሻሻል፣ ከስግብግብነት ብዝበዛ ወጥቶ በጣም ተጋላጭ እና የተረሱ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ጥሪ አቅርበዋል።
“የግብርናውን ዘርፍ በጥበብ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ውሳኔዎች መደገፍ፣ ወጣቶች በተስፋ መቁረጥ ስሜት አከባቢያቸውን ጥለው ወደ ከተማ ከመሰደድ ይልቅ በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት ሞንሲኞር ቺካ አሬላኖ በመጨረሻም፥ የምግብ ግብርና ሂደት የሰውን ልጅ ክብር ማዕከሉ ማድረግ እንዳለበት፣መጪውን ጊዜ ሳይጎዳ የምግብ ፍላጎቶችን ማሟላት እና በአገር ውስጥ ጨዋነት ያለው ሥራን ማበረታታት እንዳለበት በአጽንዖት በመግለጽ አጠቃለዋል።