“ለሰው ልጅ ፊት እና ድምጽ ጥበቃ ማድረግ” በሚል መሪ ሃሳብ ሐሙስ ዕለት ሮም በሚገኘው በጳጳሳዊ የኡርባኒያና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ “ለሰው ልጅ ፊት እና ድምጽ ጥበቃ ማድረግ” በሚል መሪ ሃሳብ ሐሙስ ዕለት ሮም በሚገኘው በጳጳሳዊ የኡርባኒያና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ   (@Fatima Mesaud Barreras)

አሁን ባለንበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ሰብዓዊነታችንን ጠብቆ ለማቆየት ማሰብ፣ መተባበር እና መማር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

በቫቲካን በተካሄደው ዓለም አቀፍ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ቁልፍ የሆኑ ባለሙያዎች እንደተናገሩት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰውን ልጅ ነባራዊ እውነታ እየቀየረ መምጣቱን ጠቁመው የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል በትኩረት የተወያዩ ሲሆን፥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ ለጋራ ጥቅም አገልግሎት ዕርምጃ እንዲወስዱ ሲደረግ ተስፋ እና ብሩህ የሆነ ዕድል እንደሚኖር አመላክተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ “ማግኒፊካ ሂዩማኒታስ” በተሰኘው አዲሱ እና የመጀመሪያው ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ በዚሁ ከቀጠለ ሰብዓዊነትን በመጻረር የሰውን ልጅ ክብርን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ሁሉም ሰው አስቸኳይ ኃላፊነት መውሰድ እና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የገለጹበት ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ቅዱስነታቸው “ለሰው ልጅ ፊት እና ድምጽ ጥበቃ ማድረግ” በሚል መሪ ሃሳብ ለዓለም አቀፍ የማህበራዊ ግንኙነቶች ቀን በቅርቡ ያስተላለፉት መልዕክት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለሰው ልጅ ጥቅም ለማዋል እንደሚያስፈልግ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የዘመናችን ዋነኛ ጉዳይ ላይ የሰጡትን ትርጉም በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።

“ለሰው ልጅ ፊት እና ድምጽ ጥበቃ ማድረግ” በሚል መሪ ሃሳብ ሐሙስ ዕለት ሮም በሚገኘው በጳጳሳዊ የኡርባኒያና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት እና ከባህል ዓለም የተውጣጡ ቁልፍ ተናጋሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎት በህብረተሰቡ ላይ ያለውን ተፅዕኖ እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት ላይ በተጠቆሙት ሶስት ዋና ዋና ሃሳቦች ወይም ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሃሳባቸውን እንዳካፈሉ ተገልጿል።

ሦስቱ ምሰሶዎች፡ ኃላፊነት፣ ትብብር፣ ትምህርት
ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው ጉባኤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ የተገለጹት ሦስቱ ምሶሶዎች ማለትም ኃላፊነት፣ ትብብር እና ትምህርት ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ከመምራት ይልቅ የሰው ልጅ መገልገያ መሳሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ለማረጋገጥ ያለመ እንደነበር ተገልጿል።

ኃላፊነት፡ ከትርፍ ይልቅ የሥነ ምግባር ዋስትናዎች
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኒል ላውረንስ እንደተናገሩት የሰው ልጅ ፊት በሰው ሰራሽ አልጎሪዝም የሚተካበት፣ የሰው ልጅ ድምፅም በሰው ሰራሽ ድምፆች የሚቀየሩበት መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆነችንን ጠቅሰው፥ ኃላፊነት ማለት በእያንዳንዱ የእድገት ደረጃ ላይ ተጠያቂነትን መምረጥ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰውን ልጅ ክብር ከመበዝበዝ ይልቅ የሚያገለግል መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

ትብብር፡- ለጋራ ጥቅም ዓለም አቀፍ ስምምነት
መጪውን ጊዜ አስመልክቶ በአንዳንድ ተሳታፊዎች በተነሳው ሃሳብ መሰረት ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር፣ ጥልቅ የሆኑ ሐሰተኛ መረጃዎች እና ማኅበራዊ መራራቅ የማይቀር ነገር እንደሆነ አመላክተው፥ ነገር ግን ይህ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ የተስማሙ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ ይህንን ችግር ለመቋቋም በቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሃይማኖት ምሁራን እና የሲቪል ማህበረሰብ መካከል ህብረት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአልጎሪዝም እድገት ከሞራላዊ እድገት ጋር መመሳሰል እንዳለበት የተስማሙት ተሳታፊዎቹ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ብቻውን አንድንም ሀገር ወይም ኮርፖሬሽን ሊመራው እንደማይችል ጠቁመው፥ የዲጂታል ክፍፍሉ የማይታለፍ ተግዳሮት እንዳይሆን ለማረጋገጥ በአንድነት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በትምህርት፡ አእምሮንና ልብን መግራት
የመጨረሻው እና ሶስተኛው ምሰሶ የሆነው ትምህርት የሰው ልጅን ለመጠበቅ የመጨረሻው የመከላከያ ዘዴ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ውስጥ ያለው ትምህርት ቴክኒካል ክህሎቶችን በማስተማር ወይም በኮድ አሰጣጥ ላይ ብቻ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመው፥ ከዚህ ይልቅ፥ ሂሳዊ አስተሳሰብን፣ ርኅራኄን እና መንፈሳዊ ማስተዋልን በማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

“አሁን በምንገኝበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን ማሰብ፣ ትስስር እና መማር ማለት ወጣቶቻችን እነዚህን መሳሪያዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን ይህን በሚያደርጉበት ወቅትም ሰብዓዊነታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ማስተማር ማለት ነው” በማለት በጉባኤው ላይ የተሳተፉ ፕሮፌሰሮች እና የዩኔስኮ ተወካዮች የተስማሙ ሲሆን፥ መጪው ትውልድ እውነትን ከፈጠራ እና ከተግባቦት ማግኘት እንዲችል ሚዲያ እና መረጃን መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የተግባር ጥሪ
ምንም እንኳን የአልጎሪዝም አድልዎ ማስጠንቀቂያዎች እና ትክክለኛ የሆነ የሰዎች መስተጋብር መሸርሸር ቢኖርም፥ የጉባኤው አጠቃላይ ስሜት ብሩህ ተስፋ እና ዕድል መኖሩን ያመላከተ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ የቴክኖሎጂ እድገቶቻችንን የሰውን ልጅ ፊት እና ድምጽ ትክክለኛ በሆነ መንገድ በመጠበቅ ላይ በማድረግ የሰው ልጅ ይህንን የዲጂታል ድንበር መጠቀም እንደሚችል ተገልጿል።

ጉባኤው በጎ ፈቃድ ያላቸው ወንዶች እና ሴቶች ለጋራ ጥቅም የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎች “የሚመሩበት” የወደፊት ጊዜን ለመቅረጽ የመጨረሻውን ኃይላቸውን እንዲጠቀሙ በማሳሰብ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጥሪ በጋራ ማስተጋባቱ ተነግሯል።

የሰብዓዊ ኤጀንሲ ጉልበት
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የቅድስት መንበር የባህልና ትምህርት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ብፁዕ አቡነ ፖል ቲጌ በዚህ ከቅድስት መንበር የተግባቦት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተገኙትን አስተያየቶች በማስታወስ የራሳቸውን እይታ ያካፈሉ ሲሆን፥ ብፁዕ አቡነ ቲጌ የዕለቱ በጣም አስፈላጊው መገለጥ ስሜታዊነትን አለመቀበል እንደሆነ ጠቅሰው፥ ‘ከአቅማችን በላይ የሆነ እጅግ በጣም ብዙ መረጃ’ እንዳለ በማመላከት፥ እንዲህ ያለው ፈጣን ለውጥ እየተካሄደ የእድል አስተሳሰብ የሆነውን ‘የመጠበቅ እና ማየት' ባህሪን መከተል ምን ያህል ቀላል እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

“እኔ እንደማስበው ይህ ጉባኤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንም የማይቀር ነገር መሆኑን ያሳሰበ ጉባኤ ነው” ያሉት ብፁዕ አቡነ ቲጌ፥ ከዚህም ይልቅ ማህበረሰቦችን ለመገንባት ሰዎች ሲተባበሩ የሚመጣውን “ኤጀንሲ” ወደሚለው ቃል በማተኮር እንደተናገሩት በሂደቱ ወቅት የተነሳውን “ዌ-ጀንሲ” የተሰኘውን ጽንሰ-ሀሳብ ያስታወሱ ሲሆን፥ ጉባኤው ራሱ ለዚህ የጋራ ሃይል ህያው ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል በማለት አብራርተዋል።

ከዚህም ባሻገር ይህ ጉባኤ የተለያዩ ሰዎችን ከቴክኖሎጂ እና ከትምህርት ተቋማት እንዲሁም ድንበር ላይ ካሉ የዓለማችን ክፍሎች አንድ ላይ በማሰባሰብ እኛ የሰው ልጆች ይህ አስደናቂ የሆነ አዲስ ቴክኖሎጂ የሁላችንንም ፍላጎት ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ማረጋገጥ የምንችልበትን መንገድ ለመፈለግ ውይይት ለማድረግ ያስቻለ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት አረጋግጠዋል።

በርዕሰ ለቃነ ጳጳሳት ሊዮ መልዕክት ውስጥ በተገለጹት ሦስት ምሰሶዎች ዙሪያ ንግግር አቅራቢዎቹ ያላቸውን አንድነት የተጠየቁት ብፁዕ አቡነ ቲጌ፥ የቅዱስነታቸው መልዕክት ወደዚህ አስቸኳይ የሰብዓዊ ኤጀንሲ ፍላጎት በቀጥታ እንዲመለሱ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶላቸዋል ብለዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን መቼ እና ዬት መጠቀም ይገባል?
ብፁዕ አቡነ ቲጌ ኃላፊነትን በቀጥታ ታስቦ ከሚደረግ ነገር ጋር በማገናኘት ‘ኤጀንሲ’ ከሚለው ነገር ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከመሐንዲሶች እስከ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም እስከ ተጠቃሚዎች ድረስ ሁላችንም ያሉብን የተለያዩ ኃላፊነቶችን በማስታወስ፥ ይህ ኃላፊነት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በምንጠቀምበት ወቅት በትኩረት እና በሃላፊነት መሆን እንዳለበት ብሎም መቼ እና ዬት መጠቀም አለብን የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል ብለዋል።

ወሳኝ ግንዛቤን ማዳበር
ትምህርት በተፈጥሮው የሚመነጨው ከዚህ የሥነ ምግባር ሃላፊነት እንደሆነ ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ቲጌ፥ በዚህም ማንበብና መጻፍ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ግንዛቤን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመው፥ ሰዎች ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥንካሬዎች እና ድክመቶች ወሳኝ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና በጥሩ አጠቃቀሞች ረገድ እራሳቸውን እንዲያስተምሩ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ተሻጋሪ ጥምረት
ብፁዕ አቡነ ቲጌ በመጨረሻም የትብብር ምሰሶውን አስመልክተው ሲናገሩ፥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሁሉንም የሰው ልጅ የሕይወት ገጽታ ስለሚነካ የተነጠሉ መፍትሄዎችን መፈለግ ከንቱ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ ከዚህም ይልቅ ተሻጋሪ ለሆነ ነገር በቂ ምላሽ እንዲኖረን በተለያዩ የምርጫ ሃሳቦች መካከል ጥምረት መፍጠር እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በዚህም ረገድ የእሳቸው ጽህፈት ቤት በቅርቡ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከተቋቋመው አዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኮሚሽን ጋር አብሮ ለመስራት በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ይህ ሲሆን በጣም ጠቃሚ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ፥ ምክንያቱም ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን፣ የጦርነት እና የሰላም ጉዳዮችን፣ የትምህርት እና የግንኙነት ጉዳዮችን ጨምሮ የሁሉንም ሰው ልጅ ህይወት የሚነኩ ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውሰው፥ ዬትኛውም የቅድስት መንበር ጽህፈት ቤት ካልተባበረ በስተቀር ይሄንን ጉዳይ ብቻውን ሊወጣው እንደማይችል በመግለጽ አጠቃለዋል።

26 May 2026, 14:55