የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ አስተሳሰብን እንደሚጠይቁ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዋና ዳይሬክተሯ ሜሊሳ ፓርክ፥ በዓለማችን ውስጥ ግጭቶች እየጨመሩ በሄዱበት እና ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎችን ለማስወገድ የሚደረግ ጥረት ዓለም አቀፍ ገጽታን በሚያሳይበት በዚህ ወቅት የዓለም መሪዎች ለውይይት፣ ለዲፕሎማሲ እና ትጥቅ ለማስፈታት ለሚደረግ የድጋፍ ዘመቻ ያላቸውን ተቃውሞ እንዲተዉ አሳስበዋል።
ሜሊሳ ፓርክ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ በመካሄድ ላይ ካለው ጉባኤ ጎን ለጎን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ሲናገሩ፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታ በሚያስከትለው የጅምላ ውድመት ላይ ዘላቂ ሰላምን መገንባት እንደማይቻል አስረድተዋል።
“ጦርነት ባለበት ዓለም ውስጥ ወይስ በፍቅር፣ በመተባበር እና እርስ በርስ በመተሳሰር ላይ ባለ ዓለም ውስጥ መኖር እንፈልጋለን?” በማለት የጠየቁት ሜሊሳ ፓርክ፥ “ሰላም እና እርስ በርስ በፍቅር መኖር የሰው ልጅ እውነተኛ መሠረት እንደሆነ አስባለሁ” ብለዋል።
“የቅርብ ጊዜ ግጭቶች የደኅንነት ስትራቴጂያችን ውስን እና ገደብ እንዳላቸው አሳይተውናል” ያሉት ሜሊሳ ፓርክ፥ በዩክሬን እና በኢራን የተካሄዱትን ጦርነቶች በመጥቀስ፥ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ሰላም አላመጡም ጦርነትንም አላስወገዱም” ብለዋል።
“ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የሌላቸው እጅግ አደገኛ እና ውድ ናቸው” ብለው “ሆኖም ከበስተጀርባ ሆነው ለሰው ልጅ መኖር እና በእያንዳንዱ ቅጽበት የህልውና ስጋት መፍጠራቸውን ቀጥለዋል” ብለዋል።
እየጨመረ የመጣው የኒውክሌር ስጋት
እንደ ፓርክ ገለጻ መሠረት የአሁኑ ዓለም አቀፍ የደህንነት ሁኔታ ፍጹም የሆነ የመተማመን እጥረት ያለበት ሲሆን፥ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ የታጠቁ አገራትን የሚያካትቱ ግጭቶች የመሣሪያ ቁጥጥር ስምምነቶችን ከማፍረስ በተጨማሪ የኒውክሌር ስጋቶችን እና አዲስ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ውድድርን እየጨመሩ እንደሚገኙ ታውቋል።
ሜሊሳ ፓርክ በገለጻቸው፥ “እያየነው ያለው የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች የመጠቀም ከፍተኛ አደጋ ነው” ብለው፥ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከወታደራዊ ሥርዓቶች ጋር መዋሃድ አደጋውን እያባባሰው እንደሚገኝ አስጠንቅቀዋል። በወታደራዊ መንገድ ከመቀጠል እና ከግጭት ይልቅ ውይይት፣ ወታደራዊ ኃይልን ከመጠቀም ይልቅ በዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ አዲስ የአስተሳሰብ መንገድ ማግኘት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰብዓዊነትን ማዕከል ማድረግ
ሜሊሳ ፓርክ፥ በዩክሬን እና በኢራን የሚካሄዱ ጦርነቶችን ጨምሮ በዛሬዎቹ ግጭቶች ላይ በማሰላሰል እንደተናገሩት፥ ሲቪሎች የዓመፅን ከፍተኛ ጫና እየተሸከሙ መሆናቸውን ተናግረው፥ በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እና ሰዎች በሕይወት ለመትረፍ የሚለማመዱባቸው መንገዶች እየተለመዱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም ዘመናዊ ጦርነት አስገድዶ መድፈርን እንደ ጦርነት ዘዴ አድርጎ መጠቀምን እንደሚያካትት ተናግረው፥ እንደዚሁም ማኅበራዊ ሚዲያ እና ፈጣን ግንኙነቶች የግጭት እውነታዎችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲታዩ ማድረጉን እና ይህም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ጦርነት ሲከሰት የሚከፍሉት ዋጋ ከፍተኛነት እንዲታይ ማድረጉን አስረድተዋል።
“የምናየው ትምህርት ጦርነትን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለብን ነው” ያሉት ሜሊሳ ፓርክ፥ “ይህንን እውነታ በአእምሯችን ይዘን በካስቴል ጋንዶልፎ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የኖቤል ተሸላሚዎች ጉባኤ ሰብዓዊነትን ማዕከል ለማደረግ ትክክለኛ አጋጣሚ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ የጉባኤው ውይይቶች የዛሬውን ዓለም አቀፍ የደህንነት ተግዳሮቶች ለመፍታት ከፖለቲካዊ እና ከሳይንሳዊ እውቀት ጎን ለጎን የሥነ-ምግባር አመራር አስፈላጊነትን እንደሚያንጸባርቁ አስረድተዋል።
ሞራላዊ ግዴታ ነው
የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን የማስወገድ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካይነት የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመፍታት የሚደረገው ዘመቻ የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በመሠረቱ የሞራል ጉዳይ ነው” ያሉት ሜሊሳ ፓርክ፥ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ማስወገድን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎን አስተዳደር ከባርነት መወገድ እና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ተቀባይነት ጋር የሚመሳሰል የሞራል ግዴታ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ዕድገት ለሕይወት ይጠቅማል ወይስ አደጋ ላይ ይጥላል በሚለው ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ምርጫ እንደሚገጥመው ተናግረዋል።
አንድ ተጨባጭ እርምጃ
እስከሚቀጥለው ዓመት የዓለም መሪዎች ዓለም ደኅንነቱ ይበልጥ እንዲጠበቅ ምን ማድረግ እንደሚችሉ የተጠየቁት ሜሊሳ ፓርክ፥ አንድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል እርምጃን ጠቁመው፥ ይህም የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ክልከላ ስምምነትን መቀላቀል ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ቅድስት መንበር ስምምነቱን የተቀላቀለች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን የገለጹት ሜሊሳ ፓርክ፥ አሁን ወደ 100 የሚጠጉ ፈራሚዎች እንዳሏት እና ከኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች የጸዳ ዓለምን በመፈለግ ረገድ ዓለም አቀፍ ትብብር ተጨባጭ ምሳሌ እንደሆነች ገልጸዋል።
ስምምነቱ እንደሚያሳየው ውይይት፣ ባለብዙ ወገን ትብብር እና ዓለም አቀፍ ሕግ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለሰው ልጅ የሚሰጥ አክብሮት ለወታደራዊ መስፋፋት እና ለኒውክሌር መከላከያ አስተማማኝ አማራጭን እንደሚሰጡ ገልጸው፥ “ወደፊት መጓዝ የምንችለው በውይይት፣ በብዙ ወገን ትብብር፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና ለሰብዓዊ መብቶች እና ለሰው ልጅ አክብሮት በመስጠት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።