የላቲን አሜሪካ ተወካዮች በሮም ስለ አደንዛዥ እፅ ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“የአደንዛዥ እፅ ቀውስን ለማስወገድ፣ በእምነት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ለመስጠት እና ወንጀልን ለመከላከል የሚያግዝ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን አገራት እንዲሁም መላውን ዓለም የሚያስታፍ ውይይት” በሚል ጭብጥ ከእስያ፣ ከአፍሪካ እና ከአውሮፓ የተወጣጡ ባለሞያውችን ጨምሮ ከላቲን አሜሪካ እና ከካሪቢያን አገራት የመጡ ተወካዮች በሮም ከነሐሴ 19-21/2018 ዓ. ም. ጀምሮ ውይይት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የውይይት መድረኩን በጋራ ያዘጋጁት የላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (CELAM)፣ የላቲን አሜሪካ የአደንዛዥ ዕጽ ሱስ መከላከያ እና መቋቋሚያ ሚኒስቴር (PLAPA)፣ የላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን (CAL) እና በኢንተር-አሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ያለአግባብ መጠቀም ቁጥጥር ኮሚሽን (CICAD) ናቸው። ስብሰባው “በመንፈስ ቅዱስ እገዛ መወያየት” የሚለውን የውይይት ዘዴን በመከተል ለመደማመጥ፣ ለማሰላሰል፣ ገንቢ ሃሳቦችን ለማካፈል እና የጋራ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ዕድሎችን የሚሰጥ፥ ዓላማውም የጋራ ተግዳሮቶችን እና የሚሰጡ ምላሾችን ለመለየት ሲሆን፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች በመጨረሻ የውይይታቸውን ውጤት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማቅረብ እንደሚጠቃልሉ ታውቋል።
ተነሳሽነቱ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና የቦይነስ አይረስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ከተጀመረ ተሞክሮ ሲሆን፥ በከተማው የሚገኝ “ፋሚሊያ ግራንዴ ዴል ሆጋር ደ ክሪስቶ” የተሰኘ የቤተ ክርስቲያን ድርጅት በሱስ ለተጎዱ ወጣቶች ዕርዳታን በማድረግ ከማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ እንደሚያግዝ ታውቋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ልምዱ በመላው የላቲን አሜሪካ አገራት ውስጥ በመስፋፋት የሂደቱ ውጤት ዛሬ በጋራ በተዘጋጀ መመሪያ አማካኝነት ተደራሽነቱን ለማስፋፋት የሚፈልግ የመንከባከብ ዘዴ እንደሆነ ታውቋል።
የላቲን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ኤሚልስ ኩዳ በአስተያየታቸው፥ “ተግዳሮቱ እንደገና እንዳይከሰት መከላከል እና ተጠቂዎቹ የማኅበረሰብ አካል ሆነው ለመቀጠል የሚያስችሉ ግንኙነቶችን እንደገና መገንባት ነው” ብለዋል።
"የሚያድነው ቤተሰብ ነው" ሲሉ ገልጸው፥ ሰዎች ከሱስ ጋር በሚታገሉበት ወቅት ቤተሰቦቻቸው ብዙውን ጊዜ እንደታመሙ ሊቆጥሯቸው፣ ሊቀጧቸው ወይም ሊያፍሩባቸው ስለሚችሉ በዚህም ምክንያት ተንከባካቢ ማዕከላት ተጎጂዎችን እንደ ቤተሰብ አባል በመመልከት ማኅበራዊ ውህደትን፣ እምነትን እና በራስ መተማመንን እንደገና በመገንባት እና ክህሎቶቻቸውን በማሳደግ ወደ ሥራ ዘርፍ ማሰማራት ክብራቸውን ለማደስ እንደሚረዳ ኤሚልስ ኩዳ አስረድተዋል።
“ቤተ ክርስቲያን የጉዳዩን አሳሳቢነት መረዳት አለባት”
የተደራጀ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ኔትወርክ (RECOR) አስተባባሪ አባ ካርሎስ ኦሊቬሮ ተግዳሮቱን ከሐዋርያዊ እይታ አንፃር በመመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ቤተ ክርስቲያን እጅግ የተጎዱት እና በመንገድ ዳር የውቀሩትን ወጣቶች ከእርሷ እንዳይርቁ መንከባከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ችግሩ እንዳይቀረፍ ከሚያደርጉ ዋና ዋና እንቅፋቶች አንዱ “የአደንዛዥ ዕጽ ሱስን ማስወገድ የሕክምና ባለሞያዎች ተግባር ብቻ አድርጎ መመለከት ነው” የሚለውን ያስታወሱት አባ ካርሎስ፥ የነርቭ ሐኪሞች እና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ሊጫወቱ የሚችሉት መሠረታዊ ሚና ቢኖራቸውም ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ሌላ ሚና እንዳላት እና እርሱም ማህበረሰብ መሆን፣ ሕይወትን መቀበል እና አብሮ መጓዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
አባ ካርሎስ አክለውም፥ ተግዳሮቱ ሐዋርያዊ መለወጥን እንደሚጠይቅ፥ ወንጌል ለአምልኮ ወይም ለሥነ ምግባር ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ነገር ግን ማህበረሰቦች የተደራጁበትን መንገድ ጨምሮ የሰው ልጅ ህልውና እያንዳንዱን ገጽታ እንደሚነካ እና ሁለተኛው መንገድም ሲኖዶሳዊነት እንደሆነ አስረድተዋል።
ሰላም በሁሉ ሰው ጥረት ይገነባል
በሜክሲኮ ብሔራዊ የሰላም ውይይት አስተባባሪ የሆኑት ሐና ፓውላ ሄርናንዴዝ ሮማኖ በስብሰባው ላይ ተነሳሽነትን የሚያስቀጥል እምነት በማቅረብ፥ “ማንም ሰው ወጣቶችን ከጉዳት የመጠበቅ ኃላፊነትን ለሌላ ወገን አሳልፎ መስጠት አይችልም” ብለው፥ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባት፥ መንግሥትም የራሱን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት፣ እናቶች እና አባቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የንግድ ተቋማት፥ ሁሉም ዘርፎች በጋራ የኃላፊነት መንፈስ መጫወት በሚችሉበት ሚና ውስጥ መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስብው፥ ያለበለዚያ በዓመፅ እና በዕፅ ዝውውር በተሞላች አገር ውስጥ ሰላምን መገንባት እና ወጣቶችን ከጉዳት መጠበቅ የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ እስከ መመልመል
የዕጽ ፍላጎት ቅነሳ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጂሜና ካላውስኪ ውይይቱን ከዓመታት በፊት በተጀመረ ሂደት ውስጥ በማስገባት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2018 ጀምሮ በኢንተር-አሜሪካ የአደንዛዥ ዕፅ ያለአግባብ መጠቀም ቁጥጥር ኮሚሽን (CICAD) እና የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች በክልሉ ውስጥ በ14 አገሮች ውስጥ ለስልጠና ቁሳቁሶች እና ለተግባራዊ ስልጠና የሚያመራ አጋርነት እያዳበሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ማኅበረሰቦች ብዙውን ጊዜ ከመንግሥት አገልግሎቶች ተደራሽነት ውጪ ወደ ሆኑ ሰዎች እና ቤተሰቦች መድረስ ስለሚችሉ የቴክኒክ እውቀትን በማኅበረሰብ ላይ ከተመሠረተ ድጋፍ ጋር የሚያጣምሩ አውታረ መረቦችን ማጠናከር እንዲሁም በእምነት እና በሳይንስ መካከል የሚደረግ ውይይት አስፈላጊነትን በማስመልከት ተናግረዋል።።
ካላውስኪ እንደገለጹት የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ከአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ችግሮች ጋር ተመሳሳይ ለሆኑ አደጋዎች የተጋለጡ ሰዎችን ኢላማ እንደሚያደርጉ፣ በዓመፅ የተጎዱ አካባቢ ወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ እና የባለቤትነት ስሜት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረው፥ የተደራጀ ወንጀል መጀመሪያ ላይ ጠባቂ እና ተንከባካቢ፣ ገንዘብ እና የተሻለ ሕይወት ማቅረብ የሚችል ቢመስልም በኋላ ላይ ግን ከወንጀሉ መውጣት የህልውና ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።
ስለ አደንዛዥ ዕጽ ሱስ ቀጥተኛ ልምድ ያላቸው ካህን
ሮም ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ምስክርነቶች መካከል አንዱ እና በፊሊፒንስ የማኒላ ሀገረ ስብከት ካኅን እና የ “ሳንላክባይ” ኃላፊ የሆኑት አባ ሮቤርቶ ዴላክሩዝ፥ በልዩ የግል ገጽታ አማካይነት “አንድ ጉዞ” በተሰኘ ማኅበረሰባዊ ፕሮግራም ውስጥ ሱስን ከአባታዊ እይታ በላይ እንደሚያውቁት አስረድተዋል።
“ሳንላክባይ” እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም . የተመሠረተ ሲሆን በወቅቱ በፊሊፒንስ እየተካሄደ ባለው ከባድ የፀረ-ዕፅ ዘመቻ መካከል አንዱ እንደ ነበር ይታወሳል። ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል አባ ዴላክሩዝን በማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ ፕሮግራም እንዲያቋቁሙ መጠየቃቸው ሲታወስ፥ እምነት በእውነተኛ ለውጥ ውስጥ መሠረታዊ ሚና ሊጫወት እንደሚችል፣ ዕጽን መጠቀም መተው ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን፣ ሌሎችን እና ራስን የማየት መንገድን መቀየር መሆኑን አባ ሮቤርቶ አስረድተዋል።
አባ ሮቤርቶ የተለወጠ ነገር ቢኖር አስተሳሰባቸው፣ እግዚአብሔርን እና ሌሎች ሰዎችን የሚመለከቱበት መንገድ እንደሆነ አስረድተው፥ ተደጋጋሚ የመልሶ መቋቋም ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ እግዚአብሔርን በማወቅ፣ የራስን ማንነት በመረዳት እና የሰውን ክብር በመገንዘብ ላይ ያተኮሩ ልምዶች ቀደም ሲል የተደረጉ ሕክምናዎች ሊያመጡት ያልቻሏቸውን የለውጥ ዕድሎች ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።
“ቦታችንን መልቀቅ አለብን”
በጣሊያን ፓቪያ ግዛት በሚገኘው “ካዛ ዴል ጆቫኔ” ውስጥ ከወጣቶች እና ከሌሎች በሱስ ከተያዙ ሰዎች ጋር በመሥራት ለአሥር ዓመት ያህል ያካበተውን ልምድ ወደ ስብሰባው ያመጣው ሲሞን ፌደር በበኩሉ ከተጨባጭ እውነታ በመነሳት ባቀረበው አስተያየቱ፥ “ሰዎች ወደ ህክምና ማዕከላት እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ ትክክል ባለመሆኑ ነገር ግን ወደሚገኙበት አካባቢ መሄድ አለብን” ብሎ፥ ብዙውን ጊዜ የጤና ተቋማት በማይደርሱባቸው ቦታዎች ስቃይ ከሚያጋጥማቸው ጋር ለመገናኘት መሄድ እንደሚገባ አስረድቷል።
የሲሞን ፌደር ሥራ የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳያኑ በ2017 ዓ. ም. ሲሆን፥ ሴት ልጁ አንድ ምልከታ ካሳየች በኋላ እንደሆነ ታውቋል። ሲሞን ፌደር ለብዙ ዓመታት ከሥራ በኋላ በአቅራቢያው ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማየት ለምን እንዳልሄደ ሲጠየቅ በሰጠው ምላሽ፥ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ጫካ ሲያመሩ ማግኘቱን እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ወይም ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ አደንዛዥ ዕጽ በትንሽ ገንዘብ በቀላሉ ወደሚገኙበት ቦታ ይሄዱ እንደ ነበር ገልጾ፥ ከእነዚያ ትዕይንቶች በስተጀርባ የበለጠ ጥልቅ የሆነ ብቸኝነት እና ተስፋ መቁረጥ መኖሩን አስረድቷል። ወጣቶች በመጥፋት አደጋ ላይ በሚወድቁባቸው ቦታዎች ላይ መገኘት እና መላው ማኅበረሰብ ከቤተሰቦች ጋር የማስተማር ሥራን መሥራት እንዳለበት አሳስቧል።
የመከላከል ሥራ የሚጀምረው በቤት ውስጥ ነው
በብራዚል የሐዋርያዊ ሥራ ብሔራዊ አስተባባሪ የሆነች ዴኒስ ፌሬራ ለስብሰባው ተካፋዮች ያመላከተችው ሌላ ወሳኝ ነገር “ቤት” መሆኑን ጠቁማ፥ የብራዚል ቤተ ክርስቲያን በከተሞች ዳርቻ፣ በዋና ዋና የከተማ ማዕከላት እና በገጠር አካባቢዎች መድረስ የሚችሉ ሰፊ የበጎ ፈቃደኞች እና ማኅበረሰቦች አውታረ መረብ እንዳላት፥ ይህ ሰፊ መድረክ ከመከላከያ እርምጃ ዋና ዋና ጥንካሬዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድታለች።
ነገር ግን የመከላከል ሥራዋን የምትጀምረው በልዩ ተቋም ውስጥ ሳይሆን በቤተሰብ ውስጥ በሦስት ቀላል በሚመስሉ ጥያቄዎች መጀመር እንደሚቻል እነርሱም፥ “ልጅህ የት ነው? ከማን ጋር ነው? እና ምን እያደረጉ ነው?” የሚሉት መሆናቸውን ገልጻለች።
ውይይት እና የቤተሰብ ሕይወት ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን እንደሚፈጥሩ የተናገረችው ዴኒስ ፌሬራ፥ወጣቶች በቤተሰቦቻቸው መካከል ደህንነትን፣ እምነትን እና ተቀባይነትን በሚያገኙበት ወቅት ራሱን እንደ አማራጭ የባለቤትነት ምንጭ አድርጎ የሚያቀርበው የወንጀል ቡድን ዕድሉ አነስተኛ እንደሚሆን ተናግራለች።
ፌሬራ በተጨማሪም የወንጀል ምልመላ በቀጥታ በአደንዛዥ ዕጽ ሱስ ዙሪያ ለሚሠሩ ሐዋርያዊ ሠራተኞች ብቻ የተወሰነ መሆን እንዳለበት፥ እንዲሁም የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች፣ የቤተሰብ አገልግሎት እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ዘርፎች አካል መሆን እንዳለበት እና ይህም ወንጀሉን ለመከላከል አስፈላጊ እና ልዩ ስትራቴጂ መሆኑን አስረድታለች።