የሩሲያ እና የቅድስት መንበር ልዑካን በሞስኮ ውይይት ሲያደርጉ የሩሲያ እና የቅድስት መንበር ልዑካን በሞስኮ ውይይት ሲያደርጉ  

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ‘ቅድስት መንበር በሰላም የሚያምን ዲፕሎማሲን ትከተላለች’ ማለታቸው ተነገረ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሞስኮ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‘ቅድስት መንበር በሰላም የሚያምን ዲፕሎማሲን ትከተላለች’ ማለታቸው ተገልጿል።

    አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት መንበር የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ኃላፊ ነሃሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ዓርብ ዕለት ወደ ሮም የሚወስዳቸውን አውሮፕላን ሲሳፈሩ በሞስኮ ሰማይ ላይ ፀሐይ በደማቁ ታበራ የነበረ ቢሆንም፥ ሮም ሲደርሱ ግን መሽቶ እንደነበር እና ጉዞው በኢስታንቡል በኩል የተደረገ ረጅም እና አድካሚ ጉዞ እንደነበር ተገልጿል።

በሩሲያ እና በአውሮፓ ህብረት ሀገራት መካከል ያለው ቀጥተኛ የበረራ ግንኙነት መቋረጥ ወደ ሞስኮ ለመድረስ ያሉትን አማራጮች የገደበ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ጥቂት የማይባሉ በረራዎች በረጅሙ የበረራ መንገዶች ለመጓዝ መገደዳቸው እና ይህም ከኢስታንቡል ተነስቶ የባልካን አካባቢን ማቋረጥን፣ የዩክሬን ድንበሮችን አቅጣጫ ተከትሎ መሄድን እና በመጨረሻም የቤላሩስን የአየር ክልል ማቋረጥን እንደሚያካትት ተገልጿል።

እ.አ.አ. ከ2022 ዓ.ም. በፊት ለአራት ሰዓታት ያህል በረራ ብቻ ይጠይቅ የነበረው ይህ ጉዞ፣ አሁን በአውሮፕላን በረራዎች እና በየመሃሉ በሚደረጉ ማረፊያዎች ምክንያት ቢያንስ አስራ ሁለት ሰዓታት የሚወስድ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጉዞው “ረጅም እና አድካሚ ጉዞ እንደነበር” ገልጸው፥ “ነገር ግን ይህ ጉዞ ተምሳሌታዊ ትርጉም እንዳለውና ከ2022 ዓ.ም. በፊት ወደ ሞስኮ ለመድረስ ጥቂት ሰዓታት ብቻ ይፈጅ እንደነበር፣ ዛሬ ግን መንገዱ ረዘም ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ ጉዞ ቅድስት መንበር በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እንዲደረግ የምትፈልገውን የሰላም ውይይት ፍላጎት ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም በቅድስት መንበር (ቫቲካን) በሚገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲ እንዲሁም በሞስኮ በሚገኙት የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጆቫኒ ዳኒዬሎ አማካይነት ለዓመታት ሲደረግ የቆየ ውይይት መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ይህ ለዚህ ጉዞ የተሰጠውን ቁርጠኝነትና አስፈላጊነት እንደሚያሳይ፥ ብሎም ጉዞው የተከናወነው በቅድስት መንበር ስም እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቡራኬ መሆኑን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ወደ ሞስኮ ያደረጉት ጉብኝት በሩሲያ ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት እንዳተረፈ እና ይህም ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ እና ከአማካሪያቸው ጋር በተደረጉት ይፋዊ ውይይቶች ላይ በግልጽ የታየ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በውይይቱ ወቅት ከዩክሬን ጋር እየተካሄደ ያለው ጦርነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ማግኘቱን እና ጋላገር ግጭቱን ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ወደ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መመለስ እንደሆነ በተደጋጋሚ አጽንዖት ሰጥተው ማንሳታቸው ተገልጿል።

ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ግንኙነቶችን መልሶ ለመገንባት ያለው ሁኔታ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚሄድ የገለጹት ሊቀ ጳጳሱ፥ በርካቶች በጦርነቱ መጎዳታቸው እና እስከ አሁንም በርካታ ያልዳኑ ቁስሎች ቢኖሩም፥ ነገር ግን በታሪክ እንደሚታወቀው ሁሉም ግጭቶች እና ጦርነቶች በመጨረሻ የሚቋጩት በድርድር እና በስምምነት መሆኑን ገልጸው፥ ከዚያም በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ወገኖች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነትን መልሶ የመገንባት ሂደት እንደሚጀመርና በዚህም ረገድ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

“ይሄንን ማወጅ እንደ ቤተክርስቲያን የእኛም ኃላፊነት እና ግዴታ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ወደ ሞስኮ የተጓዙት ስለ ሰላም ለመናገር፣ በጦርነቱ ምክንያት የተረበሹትን ነፍሳት ለማጽናናት እና ለማበረታታት፣ እንዲሁም ጽናት እንዲኖራቸው፣ የሰላምን መንገድ እንዲከተሉ እና የተሻለ ቀን እንደሚመጣ እምነቱ እንዲኖራቸው ለመናገር እና ለማበረታታት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሁለትዮሽ ውይይቱ በኋላ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ እንደተናገሩት፣ ሊቀ ጳጳሱ በውይይቱ ወቅት ግጭቱ በተቻለ ፍጥነት እንዲቆም አጠቃላይ ጥሪ ከማቅረብ ውጪ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ያልገቡበትን ምክንያት የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ይህ እውነት መሆኑን ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም የምትከተለው አቋም ይሄንን መሆኑን፣ ቅድስት መንበር በድርድሩ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ እንደማትገባ እንዲሁም ቴክኒካዊ መፍትሄዎችን እንደማታቀርብ አስታውሰው፤ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች በቀጥታ የተፋላሚ ወገኖች ኃላፊነት መሆናቸው እና ይልቁንም ቅድስት መንበር ይህንን ኃላፊነት በማስታወስ፣ ወገኖቹ በቁም ነገር ውይይት ለመጀመር የሚያስችል በጎ ፈቃድ እንዲያሳዩ ጥሪ እንደምታቀርብ ጠቁመው፥ ይህንንም የምታደርገው ለሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ለዩክሬን እና ለሌሎችም ሀገራት ጥሪ በማቅረብ እንደሆነ እና ለውይይት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሁሉም ዓይነት ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪዋን እንደምታቀርብ አመላክተዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ሲቪሉ ማህበረሰብ እየደረሰበት ያለውን ስቃይ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን የሚያደርጉትን ጉዞ ከግምት በማስገባት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን በአጽንዖት ሲናገሩ የቆዩት ሊቀ ጳጳሱ፥ በዚህ ረገድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን አስመልክተው እንደተናገሩት ይህ ጉዳይ እጅግ ወሳኝ መሆኑንና፤ ቅድስት መንበርም የበኩሏን አስተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ጠቁመው፥ ይህ ጥረቷም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን የገለጹ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ራሳቸው “በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግና አጽንዖት መስጠት እንደሚገባ” ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የብፁዕ ካርዲናል ዙፒ የሰላም ተልዕኮ እንደሚቀጥል እና በአካባቢው የምትገኘው ቤተክርስቲያን፣ እንዲሁም የካቶሊክ ማህበረሰቦች እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት ለመመልከትና ለመመስከር እንዲችሉ በቅርቡ ወደ ሞስኮ እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ቅድስት መንበር የውይይት እና የድርድር መንገድን እንደገና ለመክፈት የሚያስችል አወንታዊ ሚናዋን ለማበርከት ያላትን ፍላጎት አስመልክቶ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ይህ ጥረት ቀደም ተብሎ የተጀመረ ነገር ቢሆንም፥ እስካሁን ድረስ ግን ወደ ተግባር እንዳልተለወጠ አመላክተው፥ በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ መስሪያ ቤቶች በኩል ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖር ፍላጎቱ ያለ እንደማይመስላቸው፣ ነገር ግን ጉዳዩን ችላ ብለው እንዳልተውት እና ያሳዩት ተነሳሽነት አድናቆት ማግኘቱን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ መልዕክቱ ግልጽ መሆኑን እና በዛሬው ዓለም ማንም ሰው ብቻውን ምንም ነገር መፍታት እንደማይችል ያመላከቱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ሩሲያም ሆነች ዩክሬን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እና አጋሮቻቸውን እንደሚፈልጉ ጠቁመው፥ ‘ቅድስት መንበር የአደራዳሪነት ጥረቷን በማቅረብ እና በማጠናከር በማንኛውም መንገድ ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን ለሁለቱም ወገኖች እንገልጻለን’ ያሉ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አክለውም ይሄንን ለማከናወን ያለው ግብዓት ውስን ቢሆንም ይህ በቅን ልቦና የሚደረግ ጥረት መሆኑን አስረድተዋል።

ሞስኮ ውስጥ ከዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ጋር የመገናኘት እድል የነበራቸው ሊቀ ጳጳሱ፥ ቅድስት መንበር በተመሳሳይ ጊዜ ከዩክሬን እና ከሩሲያ ጋር በመወያየት ረገድ ስኬታማ የዲፕሎማሲያዊ አቅም መገንባቷን አስመልክቶ እንደተናገሩት፥ ሞስኮ ውስጥ ከተለያዩ የዲፕሎማሲ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ስብሰባዎች የቅድስት መንበርን የውይይት መንገድ ክፍት የማድረግ ተነሳሽነት ማጠናከር እንደቻሉ እና በዚህ ረገድ ሰዎችን ወይም ሀገራትን ማግለል ምንም እንደማይጠቅም ያላቸውን ጠንካራ እምነት ጠቁመው፣ ይህ የቅድስት መንበር አቋም መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በእርግጥ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን ስትራቴጂ በራሱ የመወሰን ሙሉ መብት እንዳለው አስታውሰው፥ ሞስኮ በመምጣት እና ሌሎች በአሁኑ ወቅት የማያደርጉትን ነገር በማድረግ፥ እስካሁን የተተገበሩት ስትራቴጂዎች ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ በመፍታት ረገድ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ክርስቲያኖችን የሚመለከቱ ሃሳቦች እንደሚገኙበት እና በዚህ ረገድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ የተጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በዩክሬን ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን በተለያዩ ጉዳዮች ለዓመታት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፥ ሩሲያ ከራሷ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ጥልቅ ትስስር እንዳላት፤ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ችግሮች የሚገጥሟቸው ክርስቲያኖችን ጨምሮ፥ ምንም እንኳን በአንዳንድ ሃገራት ሁኔታውን በይፋ 'ሃይማኖታዊ ስደት' ብሎ መጥራት ትክክል ባይሆንም፣ የደህንነት እጦት፣ መድልዎ፣ የተዛባ አመለካከት እና መገለል በሚታይባቸው ቦታዎች ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ የጋራ ስጋት እንዳለ ገልጸው፥ “ይህ የጋራ ቁርጠኝነታችንን ለማደስ የምንጥርበት ዘርፍ ነው” ብለዋል።

ሞስኮን በጎበኙበት ወቅት በሩሲያ የሚገኘውን የካቶሊክ ማህበረሰብ የመገናኘት እና የሰላም አራማጅ እንዲሆኑ የማበረታታት እድል ያገኙት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በዚህ ረገድ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁርጠኝነት ምን መሆን እንዳለበት ተጠይቀው፥ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከገዳማዊያት ማህበረሰብ አባላት እና ከተለያዩ ካህናት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ እነርሱ ቀድሞውንም የሰላም አራማጆች እንደሆኑ እና በዕለት ተዕለት ህይወታቸው፣ ትናንሽ የሰላም ድልድዮችን በመገንባት ይህንን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን እና ባላቸው ቀረቤታ በማህበረሰቡ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ስላላቸው የቤተክርስቲያንን የበጎ አድራጎት ስራዎች የሚያስቀጥሉ፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን የትምህርት እና የጤና ተቋሞች አማካኝነት በሥራ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ይህ ደግሞ ቤተክርስቲያኗ ለእርቅ እና ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተጨባጭ ማሳያ ስለሆነ፥ ይህ ከማንኛውም ቃል በላቀ ሁኔታ አሳማኝ እና ገላጭ መሆኑን አስምረውበታል።

በእነዚህ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ባሉት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ምክንያት ሁለንተናዊቷ ቤተክርስቲያን እነዚህን ማህበረሰቦች እንዴት የበለጠ መደገፍ እንደምትችል፣ እረኞቻቸውን እና ምዕመናኑን እንዴት ማበረታታት እና መንፈሳዊ ትስስሮችን እንዴት ማስቀጠል እንደምትችል ማሰብ እንዳለባት አሳስበው፥ ወደ ዓለም የትኛውም ክፍል ለጉብኝት በሚሄዱበት ወቅት የሚያገኟቸውን ሰዎች እና ማህበረሰቦች ሁልጊዜ በጸሎታቸው እንደሚያስቧቸው የገለጹ ሲሆን፥ ስለ ተልዕኮው ዲፕሎማሲያዊ ገጽታም ተመሳሳይ ነገር ማለት እንደሚችሉ ጠቁመው፥ የሰላም እና የፍትህ ፍላጎቶችን ሁልጊዜ በጸሎታቸው እንደሚደግፉ፤ ሰላም ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ ስለሆነ በዚህ ጊዜም ይሄንኑ እንዳደረጉ ገልጸው፥ ይሄንን ሰላም ለመቀበል ዝግጁ መሆን ግን በእያንዳንዱ ሰው ላይ የተመሰረተ መሆኑን በማሳሰብ አጠቃለዋል።

02 Sep 2026, 15:02