አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ ከጦርነት ይልቅ የሕጻናትን ደኅንነት መምረጥ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስራኤል ጦር እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ጦርነት ሲጀመር በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱ የ30 እስራኤላውያን ሕጻናት ወላጆች ለልጆቻቸው ደኅንነት እና መፈታት ጸሎት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በእንግሊዝ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የግጭት አስወጋጅ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ፖሊሲ አራማጅ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥በእስራኤል እና በሃማስ ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙት ሕጻናት መሆናቸውን ገልጸው፥ በሕይወት የተረፉት ደግሞ የጥቃት ጠባሳን ለዓመታትተሸክመው እንደሚኖሩ አስረድተዋል።
ይህ ግጭት በተለይ በልጆች ላይ ያደረሰውን ተጽእኖ በትክክል ለመረዳት ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ ከፍተኛ ተፅእኖ የወደቀው አቅመ ደካማ በሆኑት ሕጻናት ላይ እንደሆነ ተናግረው፥ ብዙ ሕዝብ ከሚኖርባቸው የዓለማችን ክፍሎች መካከል አንዱ በሆነው ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕጻናት እንደሚገኙ እና በእነዚህ ሕጻናት ላይ ጦርነቱ ያስከተለው ተፅእኖ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቁትም በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ይህ ቁጥር ግምታዊ መሆኑን በመጥቀስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በተፈጸሙት ጥቃቶች የተገደሉት ሕጻናት ቁጥር በግምት ቢያንስ 5,000 እንደሚሆን እና በፈራረሱ ቤቶች ስር የሚገኙ ወይም የጠፉ ሕጻናት ቁጥርም በርካታ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በግልጽ የሚታይ እና ከሕጻናቱ አሳዛኝ ታሪክ ክፍል እንደሆነ ተናግረዋል።
ከሁሉም የሚበልጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሕጻናት እንደሆኑ የተናገሩት፥
እነዚህ ከባድ ጉዳቶች ብዙውን ጊዜ ሕይወትን የሚያጨልሙ፥ ሥራ የማግኘት ዕድልን የሚዘጉ እና ቀሪ ሕይወታቸውን በሙሉ ተሸክመው የሚኖሩት ጉዳቶች ናቸው ሲሉ አክለዋል።
ከባድ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሕጻናት ቀጥሎ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ ብዙውን ጊዜ በማይመች መጠለያ ውስጥ ለሚኖሩት ሕጻናት በተለይም ለታዳጊዎች ውሃን እና ምግብን ማቅረብ አስቸጋሪ እንደሚሆን አስረድተዋል። በጦርነቱ የተጎዱት እና ግጭቱ አእምሮአዊ ተፅእኖ ያሳደረባቸው እና ሕይወታቸውን በሙሉ ጠባሳን ተሸክመው የሚጓዙ አጠቃላይ የሕፃን ክፍል መኖሩንም አቶ ጄምስ ዴንሰሎ አስታውሰዋል።
በእንግሊዝ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የግጭት አስወጋጅ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ፖሊሲ አራማጅ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ባለሙያ የሆኑት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ ከዚህ ግጭት በፊትም ቢሆን በጋዛ ከሚገኙ አምስት ሕጻናት መካከል አራቱ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶችን እያሳዩ እንደነበር ይገመታል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከባድ የጦርነት ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ለአደጋ የትጋለጠ አቅመ ደካማ የሕዝብ ክፍል እንደሆነ ተናግረው፥ በዚህ ምክንያት ድርጅታቸው እና ሌሎች ብዙ ኤጀንሲዎች ተኩስ እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ዕርዳታ አቅርቦቱን ያጋጠሙት ችግሮች
የእነዚህ ልጆች መብት ጦረኞቹ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ያሉት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት ምን መደረግ እንዳለበት ጠይቀው፥ ማድረግ የሚችሉት እገዛ የተከሰተው ችግር ከሚጠይቀው ጋር ሲወዳደር እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን ከ100 በላይ የቡድኑ አባላትን በሞት እንዳጣ ገልጸው፥ ጋዛ ለዕርዳታ አገልግሎት ሠራተኞች እጅግ አደገኛ ቦታ እንደሆነ ጠቁመዋል። ጋዛ ውስጥ የሚገኘው ቡድናቸው በሚያመቸው መንገድ መሥራት እንደማይችል ገልጸው፥ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ከቤታቸው የተባረሩ በመሆናቸው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸውን ጨምረው አስረድቷል።
ዕርዳታ አቅርቦቱን በተገቢ መንገድ ማካሄድ የልተቻለው ዕርዳታ ማስገቢያ መስመሮቹ በመዘጋታቸው እና የሚደርሰው የዕርዳታ መጠን ከጭነት መኪኖቹ ቁጥር ጋር ሲታይ ጥቂት እንደሆነ ገልጸው፥ ዘላቂ የውሃ አቅርቦት ማነስ፣ የነዳጅ እና የመብራት መቆራረጥ በመኖሩ ምክንያት ወቅቱ የመከራ ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል። በተጨማሪም ክረምቱ ጋዛ ውስጥ ኃይለኛ ዝናብ የሚዘንብበት ከመሆኑ አኳያ እና ሕይወትን የበለጠ ከባድ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ያለጊዜው የተወለዱ ሕፃናትን ከጦርነት አካባቢ ማስወጣት
በዚህ የጨለማ አውድ ውስጥ ብቸኛው አዎንታዊ ታሪክ በሺፋ ማዕከላዊ ሆስፒታል ውስጥ በአራስ ክፍል በሕይወት የተረፉ ብዙ ሕፃናትን በተሳካ ሁኔታ ወደ ግብፅ መውሰድ መቻላቸውን ገልጸው፥ እንደ አለመታደል ሆኖ ያለጊዜው የተወለዱ ሕፃናት በሙሉ ይህን ዕድል ማግኘት ባለማቻላቸው ልናፍር ይገባል ብለዋል።
ወላጆች አብረው መኖርን ወይም ካልሆነ መሞትን ይመርጣሉ
ከሕጻናት አድን ድርጅታቸው እና ከሌሎች ጋዛ ውስጥ ከሚገኙ የዕርዳታ ቡድኖች የሚሰሙ ታሪኮች ልብ የሚሰብሩ ናቸው ያሉት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ ወላጆች ምንም ዓይነት የደህንነት ማረጋገጫ በሌለበት አካባቢ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ስለሚቸገሩ አስቸጋሪ ምርጫዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረው፥ ብዙውን ጊዜ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብረው መሆንን ወይም ካልሆነ አብረው መሞትን እንደሚመርጡ እና ይህም እንደገና ነገሮች ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆኑ ያረጋግጣል ብለዋል።
ከሆስፒታሎች እና ከዘብ ጠባቂዎች እንደሰሙት ከሆነ፥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሕጻናት ከሞት የተረፉ ዘመዶች ሳይቀሩ ቆስለው እየመጡ እንደሆነ አቶ ጄምስ ዴንሰሎው ገልጸው፥ በሌሎች ሁኔታዎች ድርጅታቸው በማከናወን ላይ የሚገኘው ተግባር የሕጻናትን ደህንነት ማስጠበቅ እና ሕጻናት ከወላጆቻቸው እና ተንከባካቢዎቻቸው እንዳይገለሉ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። ነገር ግን በክልሉ ካለው ሁከት የተነሳ ይህን ማድረግ አይቻልም ብለዋል።
የታገቱት የእስራኤል ሕጻናት እንዲፈቱ ጥሪ ቀረበ
“የማንዘነጋው ጉዳይ በጋዛ ታግተው የሚገኙት የእስራኤል ሕጻናት በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ብለዋል አቶ ጄምስ ዴንሰሎ። እስካሁን መፈታት ነበረባቸው ወይም መታገት የለባቸውም ብለው፥ ሕጻናትን ማገት ትልቅ የመብት ጥሰት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በእንግሊዝ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የግጭት አስወጋጅ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ፖሊሲ አራማጅ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጄምስ ዴንሰሎ፥ በደቡብ እስራኤል ውስጥ በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የበርካታ ሕጻናት ችግር በማስታወስ፥ ብዙውን ጊዜ ይህ ግጭት ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ተቆጥሮ ወደ ጎን እንደሚባል በመግለጽ፥ ነገር ግን ሰዎች በሙሉ ከሞት ይልቅ የሕጻናትን ደኅንነት እንዲመርጡ ጠይቀዋል።