የዩክሬን 58ኛ ሞተራይዝድ ብርጌድ እግረኛ ወታደር ቪክቶር በዶኔትስክ ክልል በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ሆኖ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መኖር አለመኖራቸውን ሲቃኝ  የዩክሬን 58ኛ ሞተራይዝድ ብርጌድ እግረኛ ወታደር ቪክቶር በዶኔትስክ ክልል በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ሆኖ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መኖር አለመኖራቸውን ሲቃኝ  

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ትጠቀማለች መባሉ በተለያዩ ሃገራት ላይ ስጋት ማሳደሩ ተገለጸ

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም የደህንነት ቢሮዎች ሞስኮ በዩክሬን ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያን ጨምሮ እየወሰደቻቸው በሚገኙ ወታደራዊ ሥነ ምግባር ጉድለቶች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ገልጸው፥ ሩሲያ ላይ ማዕቀብ እና ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያን ተጠቅማለች ለሚለው ዘገባ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ በተገለጸው ጥቃት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ካደረሰችው ትልቁ ነው የተባለ የአየር ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፥ በዚህ ጥቃት ከ500 በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሌስቲክ እና የክሩዝ ሚሳዔሎችን ተጠቅማ ዋና ከተማዋን ኪየቭን ማጥቃቷ ተነግሯል።

የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ሾፍ የኔዘርላንድ እና የጀርመን የመረጃ ኤጀንሲዎች ሩሲያ በዩክሬን ላይ የተከለከሉ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች መጠቀሟን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንዳሏቸው ገልጸው፥ ይህ ድርጊት የአውሮፓን እና የሌሎችንም ሃገራት ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።

ባለፈው ዓመት የዩክሬን የባህር ኃይል ሩሲያ የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በዩክሬን ሃይሎች ላይ ትጠቀማለች ሲል መክሰሱ ይታወሳል።

የደች አጠቃላይ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት (AIVD) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ሾፍ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ድርጅት (OPCW) ስብሰባን በምታስተናግደው የኔዘርላንድ ከተማ በሆነችው ዘ ሄግ ላይ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር ‘የሩሲያ ድርጊት እጅግ ከባድ ነገር መሆኑን’ ገልጸው፥ ‘ምክንያቱም እየተነጋገርን ያለነው ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርሱት ገዳይ የኬሚካል መሳሪያዎች ነው’ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሩሲያ በዩክሬን እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነትን በመጣስ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በማለት የከሰሱ ሲሆን፥ ሩሲያ በጦርነቱ ወቅት “ክሎሮ-ፒክሪን” የተባለውን የኬሚካል የጦር መሳሪያ በዩክሬን ወታደሮች ላይ መጠቀሟን ገልጸዋል።

ሩሲያ ተጠቅመዋለች የተባለው “ክሎሮ-ፒክሪን” ኬሚካል ቀለም አልባ ፈሳሽ ሲሆን፤ በዓይን፣ በቆዳ እና በጉሮሮ ላይ የማቃጠል ስሜት የሚፈጥር ነው ተብሏል።

ሩሲያ የዩክሬን ወታደሮች በመሸጉባቸው ቦታዎች ላይ ኬሚካሉን በመተኮስ ወታደሮቹ ከኬሚካሉ ለመሸሽ ከጉድጓዶቹ በሚወጡበት ወቅት በጥይት እንደሚመቷቸው ተገልጿል።

ይህ ኬሚካል አሁን ላይ ፀረ ተባይ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉን የቀጠለ ቢሆንም፥ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ክልከላ ድርጅት እ.አ.አ. በ 1997 ዓ.ም. በተደረገው የጦር መሳሪያ ስምምነት (CWC) በጦር ሜዳ ጥቅም ላይ እንዳይውል እግድ ወጥቶበታል።

አስጊ የደህንነት ሁኔታ
የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲህ አይነት መሳሪያ ከዩክሬን ውጭም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረው፥ የአውሮፓ ህብረት በምላሹም በሩስያ ላይ ስለሚጥለው ተጨማሪ ማዕቀብ ውይይት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

 

ሞስኮ የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀሟን በማስተባበል በተቃራኒው ኪየቭን የወቀሰች ሲሆን፥ ይሁን እንጂ የኔዘርላንድ መከላከያ ሚኒስትር ቢያንስ የሶስት ዩክሬናዊያን ወታደሮች ሞት ከኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ የዩክሬን የጤና ባለስልጣናት ከ2,500 በላይ ሰዎች በጦር ሜዳ ላይ ከኬሚካል ጦር መሳሪያ ጋር በተያያዙ ምልክቶች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

በዩክሬን እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት የኬሚካል ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ብዙ ሀገራትን ወደ ጦርነቱ ሊስብ ይችላል የሚል ስጋትን ጨምሯል።

ይህ ጉዳይ የተነሳው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ሲሆን፥ ትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም በምርጫ ዘመቻው ወቅት የገቡትን ቃል ለመፈጸም ባላቸው ዕድል ተስፋ የቆረጡ ይመስላል ተብሏል።

ሞስኮ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 2014 ዓ.ም. በግዴታ የወሰደቻትን ክሬይሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት እየተቆጣጠረች ትገኛለች።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ እ.አ.አ. የካቲት 2022 ሙሉ ጥቃት ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ በአስር ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ ወታደራዊ ድጋፎችን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፥ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ክምችት በጣም አነስተኛ ነው ሲል ቅሬታውን ማሰማት ጀምሮ ነበር።

ይሄን ተከትሎ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ለኪየቭ የምትሰጠውን የተወሰነ የጦር መሳሪያ ማቆሟን ዋይት ሐውስ ያስታወቀ ሲሆን፥ ቢሮው ማክሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ ውሳኔው ላይ የተደረሰው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ ‘ለሌሎች አገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ’ መገምገሙን ተከትሎ ‘የአሜሪካን ጥቅም ለማስቀደም’ ታስቦ እንደሆነ አስታውቋል።

ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ያደረጉት የስልክ ግንኙነት ዋሽንግተን በቅርቡ ወደ ዩክሬን የምታደርገውን የተወሰኑ ወታደራዊ እርዳታዎችን ባቆመችበት ወቅት ሲሆን፥ ዘለንስኪ ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ሩሲያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ድሮኖች እና ባለስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ሃገራቸው ከተኮሰች በኋላ ዋሽንግተን እና ኪየቭ የዩክሬን አየር መከላከያን ለማጠናከር መስማማታቸውን ገልጸዋል።

07 Jul 2025, 13:35