የፍልስጤም ሃገረ መንግስት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሃላፊነት
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፈረንሣይ ለፍልስጤም ሃገረ መንግስት እውቅና እንደምትሰጥ ያስታወቁ ሲሆን፥ ማክሮን ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ለመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ መጪው መስከረም በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መደበኛ መግለጫ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ማክሮን መካከለኛው ምሥራቅን አስመልከቶ ከጋዜጠኞች፣ ከፍልስጤም እና ከእስራኤል የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራቸው ፈረንሳይ ለ"ፍልስጤም ግዛት" ዕውቅና እንደምትሰጥ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “ለፍልስጤም ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት እና የሁለት-ሃገራት የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ” ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ጉባኤ መጀመሪያ ላይ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት ባለፈው ሰኔ ወር በፈረንሣይ እና በሳዑዲ መንግስት መሪነት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን እስራኤል ኢራን ላይ ባደረሰችው ጥቃት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል።
በቦምብ እየተደበደቡ የሚሞቱትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች እልቂት እና በአሁኑ ወቅት በረሃብ እና በክልከላው ምክንያት በመድሃኒት እጦት እየሞቱ የሚገኙ፣ እንዲሁም ምግብ ለማግኘት ሲሞክሩ በጥይት እየተመቱ የሚሞቱትን ጨምሮ በጋዛ እየደረሰ ያለው አሳዛኝ ክስተትን በተመለከተ መንስኤ የሆኑትን ወታደራዊ ጥቃቶች ለማስቆም ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ለሁሉም ሰው ግልፅ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ መልኩ ለፍልስጤም ጥያቄ መፍትሄውን መፈለግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ይሄ መፍትሔ እንዲፈለግ ቅድስት መንበር ላለፉት አስርት ዓመታት በተደጋጋሚ ስትጠይቅ የነበረ እንደሆነ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ንቁ አስተዋጽዖ እንዲሁም በቀጥታ የሚመለከታቸው አገሮች ተሳትፎ ብቻ ሊመጣ የሚችል መፍትሔ እንደሆነ ተገልጿል።
ቅድስት መንበር ከፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት (PLO) ጋር ከ25 ዓመታት በፊት መሠረታዊ ስምምነት መፈራረሟን ማስታወስ ጠቃሚ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ከአሥር ዓመታት በፊት ጥር ወር 2008 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለው የፍልስጤም ሃገረ መንግስት ጋር ሁሉን አቀፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ ውሳኔ እና እውቅና ከ 1940 ዓ.ም. ጀምሮ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስለ ቅዱስ ቦታዎች ሁኔታ እና ስለ ፍልስጤም ህዝብ እጣ ፈንታ ከተገለጹት አሳሳቢ ጉዳዮች ጋር የሚጣጣም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ ፍልስጤማውያን የጦርነት ስደተኞች ቡድን ብቻ ሳይሆኑ ህዝቦች መሆናቸውን በግልፅ ያረጋገጡ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ቅዱስነታቸው በ 1967 ዓ.ም. የገና በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ሉዓላዊት ሀገር ሆና የተቋቋመችው እስራኤል ውስጥ የሚገኙ የአይሁድ ህዝቦች የሌላውን ህዝብ ማለትም ለረጅም ጊዜም ስቃይ ውስጥ የኖሩትን የፍልስጤም ህዝብ መብት እና ህጋዊ ምኞቶች እንዲገነዘቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
እ.አ.አ. በ 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከእስራኤል መንግስት በ(1993 ዓ.ም.) እንዲሁም ከፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር በ (1994 ዓ.ም.) ጥሩ የሆነ ግንኙነት መስርተው የነበረ ሲሆን፥ በወቅቱ ሁለቱ ወገኖች ወደ ስምምነት ለመምጣት የተቃረቡበት እና ለሁለት ሀገራት የጋራ እውቅና የነበራቸው በሚመስልበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።
በ 1992 ዓ.ም. የካቲት ወር ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኤሪኤል ሻሮን ወደ አል-አቅሳ መስጊድ ግቢ ከመግባታቸው ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ እና ሁለተኛው ኢንቲፋዳ ከመቀስቀሱ በፊት ቅድስት መንበር ከላይ የተጠቀሰውን መሰረታዊ ስምምነት ከፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር መፈራረሟ ይታወቃል።
ቅዱስነታቸው በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ቤተልሔምን በጎበኙበት ወቅት “ቅድስት መንበር የፍልስጤም ሕዝቦች ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸው፣ እንዲሁም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በሰላምና በመረጋጋት የመኖር መብት እንዳላቸው ትገነዘባለች” ያሉ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ መድረክ እሳቸውና ቀደምት አባቶቻቸው በአከባቢው የሚገኙ ህዝቦች በዓለም አቀፍ ህግ እና በተጓዳኝ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔዎች እና አዋጆች መሰረት ተረጋግቶ የመኖር መብት ዋስትና ካልተሰጣቸው በስተቀር በቅድስት ሀገር ያለው አሳዛኝ ግጭት ማብቂያ እንደሌለው ደጋግመው ሲናገሩ እንደነበር ተገልጿል።
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ቅድስት ሀገርን በጎበኙበት ወቅት እስራኤል እንደ ሃገር የመኖር መብት እንዳላት እና በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት በተለዩ ድንበሮች ውስጥ ሰላምና ደኅንነት የማግኘት መብት እንዳላት በዓለም አቀፍ ደረጃ መታወቅ እንዳለበት ጠቅሰው፥ በተመሳሳይ መልኩ የፍልስጤም ህዝብ ሉዓላዊ የሆነ ነጻ ሀገር የማግኘት፣ በክብር የመኖር እና በነጻነት የመጓዝ መብት እንዳለው እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቅድስት መንበር በ 2004 ዓ.ም. "የፍልስጤም ግዛት" የተባበሩት መንግስታት ታዛቢ አባል ሆና መመረጧን እንደምትደግፍ ያሳወቀች ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2006 ዓ.ም. ቅድስት ሀገርን በጎበኙበት ወቅት ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ሁሉም ሰው ለጋራ ጥቅም ሲባል ተባባሪ እና ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ድፍረት የሚያሻበት ጊዜ መድረሱን” ጠቁመው፥ የሁለቱ መንግስታት የመኖር መብት ሙሉ በሙሉ እውቅና መስጠት ላይ የተመሰረተ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ድንበሮች ውስጥ በሰላም እና በደህንነት መኖር ላይ የተመሰረተ ሰላም የመፍጠር ድፍረት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበው የነበረ ሲሆን፥ ተቀብሎ ያስተናገዳቸውን ሃገር ለመጀመሪያ ጊዜ “የፍልስጤም ግዛት” በማለት ሲጠሩ እንደነበርም ይታወሳል።
የነዚህ ድምር ውጤቶች በቅድስት መንበር እና በፍልስጤም ግዛት መካከል በ 2007 ዓ.ም. ወደተፈረመው እና ህዳር 1939 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ቁጥር 181 አስቀድሞ የተላለፈውን የሁለት መንግስታት መፍትሄ ላይ ወደሚያተኩረው አጠቃላይ ስምምነት የመሩ እንደሆነ ተነግሯል።
የስምምነቱ መግቢያ ዓለም አቀፍ ህግን በመጥቀስ፥ የሁለት-መንግስታት የመፍትሄ ግቦችን፣ የፍልስጤም ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ ኢየሩሳሌም ለአይሁዶች፣ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ያላት ምሳሌያዊ እና መንፈሳዊ ጠቀሜታ፣ እንዲሁም ሁለንተናዊ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱ ለሁሉም የሰው ልጅ ውድ ሀብት መሆኑን ያመላክታል።
የሰነዱ መግቢያው ላይ የፍልስጤም ህዝብ በራሱ ሉአላዊ ሃገር “በነፃነት፣ በደህንነት እና በክብር” የመኖር መብት እንዳለው የሚጠቅስ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ “ነጻ፣ ሉዓላዊ እና ዲሞክራሲያዊ የሆነች የፍልስጤም ግዛት ከ 1959 ዓ.ም. በፊት በነበረው ድንበሮች በምዕራብ ባንክ ፣ምስራቅ እየሩሳሌም እና በጋዛ ሰርጥ ላይ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በሰላም እና በፀጥታ አብሮ የመኖር መብት አላት” የሚለውን በድጋሚ ያረጋግጣል።
አጠቃላይ ስምምነቱ በ 1992 ዓ.ም. ከፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር የተደረገውን መሰረታዊ ስምምነት በመጥቀስ እና “የኢየሩሳሌምን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ላይ በመመስረት ፍትሃዊ መፍትሄ የማግኘት ጥያቄን በድጋሚ በማንሳት፥ ‘የኢየሩሳሌምን ልዩ ባህሪ እና ደረጃ የሚቀይሩ የአንድ ወገን ውሳኔዎች እና ድርጊቶች ከሥነ ምግባር እና ከህግ አንፃር ተቀባይነት እንደሌላቸው’ እና ማንኛውም ሕገ-ወጥ የአንድ ወገን እርምጃ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደናቅፍ በአጽንዖት አረጋግጧል።
ይህ ሰነድ በቅርቡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅድስት መንበር ለተባበሩት መንግስታት በሰጡት መግለጫ ያቀረቡት ጥሪ ላይ የተገለጸውን አቋም ወጥነት እና ተጨባጭነት የሚመሰክር እንደሆነም ተገልጿል።
ከዚህም ባለፈ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ሃማስ እስራኤል ላይ ያደረሰውን ኢሰብአዊ የሽብር ጥቃት ተከትሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጭፍጨፋውን በማውገዝ ታጋቾች በሙሉ እንዲፈቱ ደጋግመው መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በዚሁ ጊዜ ቅድስት መንበር እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት እንዳላት እንደምትገነዘብ፣ ሆኖም ግን መላውን የፍልስጤም ሕዝብ ኢላማ ያደረገ በጋዛ ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣ እንዲሁም የፍልስጤም ግዛት አካል በሆነው በዌስት ባንክ ውስጥ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ ሰፋሪዎች እያደረሱት የሚገኘውን ጥቃት ማውገዛቸው ይታወቃል።
በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በጋዛ እና በተለያዩ አከባቢዎች ተቀባይነት የሌላቸው እና ከፍተኛ እልቂቶችን ያስከተሉ ከህሊና ውጪ የሆኑ ጥቃቶች ተከስተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ግቢ ውስጥ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባደረሱበት ወቅት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባስተላለፉት ግልጽ ጥሪ መሰረት ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ እንዲከበር፣ ሰላማዊ ሰዎችን የመጠበቅ ግዴታ እንዲሁም የወል ቅጣትን የሚከለክለውን ህግ እንዲከበር፣ ብሎም ከልክ በላይ የሆነ የኃይል አጠቃቀምን እና ህዝቡን በግዳጅ ማፈናቀልን ማቆም አስቸኳይ እና አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑ ተጠቅሷል።
ይሄንን እልቂት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መደገፍ እንደማይገባው የተገለጸ ሲሆን፥ መጪው ዓመት ላይ የሚደረገው ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለፍልስጤም ጥያቄ ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚያመጣ፥ ብሎም ለፍልስጤማዊያን ስቃይ በአስቸኳይ የጋራ ምላሽ መስጠት ያለውን አስፈላጊነት በመገንዘብ የሁለት-ሃገራት መፍትሄ አፈጻጸም ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ፣ በመጨረሻ አስተማማኝ፣ የተከበረ እና እውቅና ያለው ድንበሮች ያላት ሀገር እንድትሆን የሚያረጋግጥ መፍትሄን እንደሚያመጣ ተስፋ ተጥሎበታል።