በፓኪስታን ከፍተኛ አለመረጋጋት ይታያል በፓኪስታን ከፍተኛ አለመረጋጋት ይታያል   (ANSA)

በፓኪስታን በመንፈሳዊ ንግደት ላይ የነበረ ካቶሊካዊ ጎልማሳ ከተገደለ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጥሪዎች ቀረቡ

በፓኪስታን የላሆር ሀገረ ስብከትን ለመጎብኘት በመንፈሳዊ ንግደት የመጣ የ42 ዓመቱ ጎልማሳ በጥይት ተመትቶ በመገደሉ በአከባቢው ከፍተኛ ሃዘን እና ድንጋጤ መስፈኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በፓኪስታን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባለሙያዎች እንደዚህ አይነት ጥቃቶችን ለመከላከል በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ ጠንካራ እና ውጤታማ ማህበራዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መጠየቃቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሻባዝ ብሃቲ ሚስዮን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ፖል ጃኮብ ብሃቲ ክስተቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ‘ሟቹ የተገደለው በአክራሪ ወጣቶች ቡድን’ መሆኑን ጠቁመው፥ ገዳዮቹ በሟች አንገት ላይ ያለውን መስቀል እንዳዩ በጠመንጃ ተኩሰው እንደገደሉት ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለአካለ መጠን ያልደረሰ የአጎቱን ልጅ በጥይት መትተው ማቁሰላቸውን የገለጹት አቶ ፖል፥ በፓኪስታን የላሆር ሃገረ ስብከት ሥር በሚገኘው እና የክርስቲያን መንደር በሆነው ማሪያ-ማባድ ከተማ የሚገኘውን የቅድስት ድንግል ማርያም ብሄራዊ ቤተ መቅደስን ሲጎበኝ የተገደለውን የ42 ዓመቱ የካቶሊክ እምነት ተከታይ አቶ አፍዛል ማሲህ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

ይህ ግድያ የተፈጸመው ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. መሆኑም ያስታወሱት አቶ ፖል፥ ግድያው የተፈፀመው ክርስቲያኖችን መግደል ጥሩ ነገር ነው ብሎ በፅኑ በሚያምን ሰው መሆኑን ጠቁመዋል።

የብሃቲ ማኅበር ስያሜውን ያገኘው እ.አ.አ. በ 2011 ዓ.ም. የፓኪስታን የፌዴራል አናሳ ሃይማኖቶች እና ብሔራዊ ስምምነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ‘የእግዚአብሔር አገልጋይ’ ተብለው የተሰየሙት ወንድማቸው አቶ ሻባዝ በጽንፈኞች ከተገደሉ በኋላ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ባለሙያው እንደዚህ ያሉ በርካታ ትዕይንቶችን ማያታቸውን ገልጸው፥ ሃይማኖታዊ ጥቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ጥቃቶች እየጨመሩ በሄዱበት በአሁኑ ወቅት ተሃድሶ ያስፈልጋል
በአሁኑ ወቅት ፓኪስታን ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የስነ-ሕዝብ እድገት እያሳየች መሆኑ የሚነገር ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በተለይ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ እና ውጤታማ የማህበራዊ ማሻሻያ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ብሃቲ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት ማህበራዊ ማሻሻያዎች ባለመደረጉ የአክራሪነት መስፋፋት እንዲባባስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ አደጋው ክርስቲያኖች ላይ ብቻ ያንዣበበ ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንደሚያሳስብ ገልጸዋል።

በአከባቢው ሙስሊሞችን ጨምሮ በጣም ብዙ አስተምህሮዎች እና እምነቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ፖል ብሃቲ፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መሆናቸውን እና ትምህርቶቹ አክራሪነት የሚታይባቸው መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

አደገኛ አስተምህሮ
በርካታ የድሃ ቤተሰብ ልጆች በእነዚህ አክራሪዎች ወደሚተዳደሩ መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች እንደሚወሰዱ ያስታወሱት አቶ ፖል ብሃቲ፥ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የምግብ እና መጠጥ ድጋፍን ተገን በማድረግ ልጆቹ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩባቸው አስረድተው፥ አሁን ያለው መንግስት እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ ይህን አደገኛ አካሄድ ቢያውቅም ችግሩን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት በቂ አለመሆኑን በመግለጽ፥ ይህ አካሄድ እየተከሰተ ላለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል።

አስፈላጊ ማሻሻያዎች
አቶ ፖል በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የመንግስት ትኩረት በፑንጃብ ክልል በቅርቡ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ምክንያት የተከሰቱትን ጥልቅ ቁስሎች መፈወስ ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት ለሰብአዊ ክብር እና የሃይማኖት ነፃነት መከበርን የሚያበረታታ የሲቪክ እና ማህበራዊ ትምህርትን ጨምሮ ወሳኝ ማሻሻያዎችን ለመተግበር አስፈላጊ የሰው እና የገንዘብ ሀብት እንደሌለ አመላክተዋል።

አፋጣኝ ምላሽ
የአፍዛል ማሲህ ግድያን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት የመከላከያ እርምጃዎችን በመተግበር ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፥ ነገር ግን እርምጃዎች ውጤታቸው ጊዜያዊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፖል ብሃቲ፥ በመጨረሻም ሁሉም ሰው ያለ ፍርሃት የሚኖርባት ፓኪስታንን መመስረት እንደሚገባ በማሳሰብ አጠቃለዋል።

16 Sep 2025, 14:24