ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የሃይል ማመንጫ ግድብ አስመረቀች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የሃይል ማመንጫ ግድብ አስመረቀች  (AFP or licensors)

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የሃይል ማመንጫ ግድብ አስመረቀች

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የውሃ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጳጉሜ 4/2017 ዓ. ም. በይፋ አስመርቃለች። በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው እና አምስት ቢሊዮን ዶላር የፈጀው ህዳሴ ግድብ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የመብራት ሃይል አቅርቦት እና በምሥራቅ አፍሪካ ለውጭ ገበያ የሚውል ትርፍ ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የኢነርጂ ክፍተት ለመቅረፍ እና ልማትን ለማቀጣጠል የሚረዳ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ “ብሔራዊ ኩራት እና የዕድገት ምልክትም ነው” ሲሉ አወድሰዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ፥ የኢትዮጵያውያን ኅብረት ምሳሌ በሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች
በኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን እና የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ወደ ጉባ በማቅናት ከሃይማኖት አባቶች ጋር በኅብረት በምረቃው መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙ ሲሆን፥ “ላለፉት በርካታ ዓመታት በግንባታ ላይ ቆይቶ ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ. ም. ለምረቃ የበቃው ህዳሴ ግድብ ለመላው ኢትዮጵያውያን ብሎም አፍሪካውያን የስኬት ምሳሌ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በ 1.78 ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ የተዘረጋው እና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ግድብ ከ11 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር በላይ አርማታ ያለው እንደሆነ ታውቋል። “ንጋት ሐይቅ” ተብሎ የሚጠራው ሰፊው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ቀድሞውንም ቢሆን የክልሉን የውሃ ችግር እየቀረፈ የሚገኝ እንደ ነበር ተገልጿል።

በአገር ውስጥ በስፋት የሚወደሰው ታላቁ ህዳሴ ግድብ “GERD” የታችኞችን ተፋሰስ አገራት በተለይም “የውሃ ደህንነታችንን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል” ብለው ከሚሰጉ ግብፅ እና ሱዳን ጋር ውጥረት ፈጥሮ መቆየቱ ይታወሳል።

90% የሚሆን ንጹህ ውሃ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው ግብፅ፥ ታላቁ ህዳሴ ግድብ “GERD” በድርቅ ጊዜ ፍሰቱን ቀንሶ ወደፊት በሚሠሩ ፕሮጀክቶች ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ጠንካራ ስጋቷን ተናግራለች። ካይሮ ግድቡ “በብሔራዊ የደህንነት ጉዳይ ላይ አደጋ የሚፈጥር” ስትል ገልጻ፥ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ እንደምትወስድም ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

ሱዳን በግድቡ አሞላል እና ሥራ ላይ ህጋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲኖር በማለት የግብፅን ጥያቄ አስተጋብታለች። ይሁን እንጂ ካርቱም ግድቡ የተሻለ የጎርፍ ቁጥጥር እና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በመጨመር ጥቅሞችን ሊሰጥ እንደሚችል አስባለች።

ሦስቱ አገራት ለዓመታት ካደረጓቸው ውይይቶች በኋላ ወደ ጋራ መግባባት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም። ኢትዮጵያ ግድቡ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት እንደማይጎዳ በመግለጽ የአባይን ሃብት የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን አጥብቃ ትናገራለች።

 

 

10 Sep 2025, 11:12