አንድ ቤት አልባ ሰው ከአንድ ሆቴል አጠገብ ተኝቶ - ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. አንድ ቤት አልባ ሰው ከአንድ ሆቴል አጠገብ ተኝቶ - ጥቅምት 5 ቀን 2018 ዓ.ም.   (AFP or licensors)

ዓለም አቀፍ ድህነትን የማጥፋት ቀን ተከበረ

ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ድህነትን ለማጥፋት ግቡ ያደረገ ዓለም አቀፍ ቀን የሚከበርበት ሲሆን፥ ይሄን ተከትሎ በዚህ ዓመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "ለቤተሰቦች ክብር በመስጠት እና ውጤታማ ድጋፍን በማረጋገጥ ማህበራዊ እና ተቋማዊ በደልን ማስቆም” ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ድህነትን ለማጥፋት በሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ርብርብ ውስጥ ሀገራት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ 1992 ባሳለፈው ውሳኔና ባጸደቀው አዋጅ አበክሮ የሚጠይቅ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግሥታት ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በየዓመቱ እ.አ.አ ጥቅምት 17 ድህነትን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት የሚዘከርበት ቀን እንዲሆን ዓልሞ ዓለም አቀፍ ቀን አድርጎ አውጇል። በዚህም መሰረት የሚመለከታቸው ሀገራት ተወካዮች በተገኙበት የድህነት ቅነሳ ቀን በኒውዮርክ ከተማ ተካሂዷል።

ከሰኔ ወር ጀምሮ የዓለም ባንክ በየጊዜው የሚያወጣውን አስከፊ የድህነት ግምቱን በ125 ሚሊዮን ሰዎች ከፍ ያደረገ ሲሆን፥ ይህ ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ድህነት ሳይሆን አዲስ እና ከፍተኛ የዓለም አቀፍ የድህነት መስመር መኖሩን ያሳያል ብሏል።

እ.አ.አ. ጥቅምት 17 ቀን በተከበረው ድህነትን የማጥፋት ቀን ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ 838 ሚሊዮን ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ግንባር ቀደም አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል።

ከፍተኛ የድህነት መስመር እና የበለፀጉት ሃገራት
ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት እና ብሔራዊ የድህነት መገለጫዎች ዓለም አቀፍ የድህነት መስመር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ የእነዚህ ሃገራት የድህነት መስመር ባደገ ቁጥር አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ የድህነት መስመሩም አብሮ ከፍ ማለት እንደነበረበት ተገልጿል።

በውጤቱም የዓለም ባንክ በየዓመቱ የሚያወጣውን እጅግ የከፋ የድህነት ግምት የተለወጠ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት እ.አ.አ. በ 2022 ዓ.ም. በድህነት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር ከ713 ወደ 838 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ እና አዝማሚያው በዚህ ከቀጠለ 8.9 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በጎረጎሳዊያኑ በ2030 በከፋ ድህነት ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል።

ከአንድ በላይ ምክንያቶች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሳሰቡት ድህነት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ላይ ብቻ የተመሰረተ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ድህነት የአንድ ግለሰብ ውድቀት ብቻ ሳይሆን፥ የስርዓት ውድቀት እንደሆነ እንዲሁም ክብርን እና ሰብአዊ መብቶችን መካድ እንደሆነ አመላክተዋል።

የዓለም ባንክ በበኩሉ የአየር ንብረት ለውጥ ድህነትን እና ኢፍትሃዊነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ አደጋ እንዳለው ያመላከተ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ከአምስት ሰዎች አንዱ በሕይወቱ ውስጥ ለከፋ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እንደተጋረጠ ጠቅሶ፥ ይህም ማለት በኑሮአቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል እና ይህም የድህነት ቅነሳ ጥረቶችን በእጅጉ እንደሚጎዳ ገልጿል።

ሰዎችን ከእነዚህ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች መጠበቅ ማለት የአደጋ አያያዝን በማሻሻል እና የወደፊት የአየር ንብረት አደጋዎች እንዳይባባሱ በማድረግ ተጋላጭነትን መቀነስ ማለት እንደሆነም ጭምር ተገልጿል።

ድህነትን ወደ ማጥፋት መሸጋገር
ቀኑን በማስመልከት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እንደገለጸው ድህነትን ለማስወገድ እና የጋራ ብልፅግናን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ሲሆን፥ የዘንድሮው ድህነትን የማጥፋት ዓለም አቀፍ ቀን ጭብጥ የሆነው “ለቤተሰቦች ክብርን በመስጠት እና ውጤታማ ድጋፍን በማረጋገጥ ማህበራዊ እና ተቋማዊ በደል ማቆም” የእያንዳንዱን ቤተሰብ ክብር የመጠበቅ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቤተሰቦችን ለመርዳት በተዘጋጁ ቦታዎች፥ ማለትም በበጎ አድራጎት ቢሮዎች፣ በህፃናት ጥበቃ ስርዓቶች እና ክሊኒኮች ውስጥ መገለል እና የማዋረድ ተግባራት እንደሚያጋጥማቸው የተጠቆመ ሲሆን፥ ሰዎችን የሚያዋርድ ፍርድ እና ቁጥጥርን ለመዋጋት የዕለቱ መሪ ሃሳብ ሶስት ለውጦች እንዲደረጉ ጥሪውን አቅርቧል።

እነዚህም ለውጦች፦
1. ከቁጥጥር ወደ እንክብካቤ፡- በመተማመን ላይ የተመሰረተ አገልግሎቶችን መፍጠር እና ጥብቅ መስፈርቶችን መገደብ፣ የወረቀት ሥራዎችን ቀላል ማድረግ እንዲሁም በአክብሮት እና ሰውን ያማከለ ተሳትፎ ላይ ማተኮር።
2. ስህተትን ከመፈለግ ሰውን ወደ ማብቃት፡- የገንዘብ ድጋፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ከክትትልና ከመለያየት ማራቅ፣ እንዲሁም የገቢ እርዳታ፣ ጥራት ያለው የሕጻናት እንክብካቤ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ መኖሪያ ቤት፣ የአእምሮ ጤና ድጋፍ፣ የወላጅነት መርጃዎች እና የህግ ድጋፎችን የመሳሰሉ ቤተሰቦችን ወደሚያጠናክሩ አገልግሎቶች ማተኮር።
3. ከመጫን ወደ አካታች ወይም ሁሉን አቀፍ መፍትሄዎች፡- ለድህነት የተጋረጡ ቤተሰቦችን በግምገማ፣ እቅድ በማውጣት፣ በጀት በማውጣት፣ በትግበራ እና በግምገማ ሂደቶች በየደረጃው ማሳተፍ፣እንዲሁም የሚወጡ ፖሊሲዎች በህይወት ልምድ ላይ የተመሰረተ እና ትክክለኛ ፍላጎቶችን የሚፈታ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆኑ ተገልጿል።

20 Oct 2025, 16:00