የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ - የማህደር ምስል የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ - የማህደር ምስል  

እስራኤል በደቡባዊ የሃገሪቷ ክፍል የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ልታነሳ እንደሆነ ተገለጸ

እስራኤል ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የነበረውን እና በ“ልዩ ሁኔታ” የተሰየመውን አዋጅ እንደምታነሳ ያስታወቀች ሲሆን፥ ይህም በሃማስ የሚመራው የታጣቂዎች ቡድን መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት አድርሶ በርካታ ጉዳት ካደረሰ በኋላ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚያካትት ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ደቡባዊውን የአገሪቱን ክፍል ለሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት በድንገተኛ አደጋ ጊዜ ተጨማሪ ስልጣን የሚሰጣቸውን በ “ልዩ ሁኔታ” ሥር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት ወታደራዊው ክፍል የሰጠውን ምክረ ሃሳብ መቀበላቸውን ይፋ አድርገዋል።

ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች የሞቱበት እና 250 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የታገቱበትን የሃማስ ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በጋዛ አዋሳኝ አካባቢዎች ተሰይሞ የነበረው አዋጁ እስከ አሁን ተግባራዊ ሆኖ የቆየ ሲሆን፥ በመኖሪያ አከባቢዎቹ ይህ ‘ልዩ ሁኔታ’ የታወጀው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘሩ እንደሆነ ይታወቃል።

ካትዝ ይህ ውሳኔ የተላለፈው ባለፉት ሁለት ዓመታት ሃገራቸው በሃማስ ላይ በወሰደችው “ቆራጥ እና ጠንካራ ሥራዎች” የተገኘውን አዲስ የደህንነት እውነታ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸው፥ እስራኤል የሐማስን ወታደራዊ አቅም ለማፍረስ እና ጋዛን ከወታደራዊ ኃይል ለማላቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን ጭምር ገልፀዋል።

በሌላ ዜና የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ በሃገራቸው ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት እና የሥነ-ህዝቡን ስብጥር በመጥቀስ በትራምፕ አስተዳደር የተኩስ አቁም እቅድ መሰረት ሀገራቸው ጦሯን ወደ ጋዛ እንደማትልክ የገለጹ ሲሆን፥ ከአጠቃላይ የዮርዳኖስ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የፍልስጤም ዝርያ መሆኑን ንጉሱ በማስታወስ “ከፍልስጤም ጋር በፖለቲካ ረገድ በጣም እንቀራረባለን” ብለዋል።

ዮርዳኖስ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር የሆነውን 2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ስደተኞችን በአስርት ዓመታት ውስጥ ተቀብላ እያስተናገደች የምትገኝ ሃገር ስትሆን፥ የንጉሱ አስተያየት በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ወይም በሃማስ እና በተቀናቃኙ የፍልስጤም አንጃዎች መካከል ለረጅም ጊዜ ግጭት ውስጥ መግባትን በተመለከተ በአሜሪካ አጋሮች መካከል ያለውን ሰፊ ስጋት አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሰረት ሰላምን ማጠናከር ማለት ወታደራዊ ሃይልን ጨምሮ አስገዳጅ እርምጃዎችን የሚያካትት ሲሆን፥ ሰላም ማስከበር ደግሞ የሁሉንም ወገኖች ስምምነት የሚፈልግ እና ራስን ለመከላከል እና ጥበቃ ለማድረግ ሃይልን የሚገድብ እንደሆነ ይታወቃል።

በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀረበው ባለ 20 ነጥብ የሰላም እቅድ መሰረት የአረብ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች የማረጋጋት ሃይሎችን በማሰማራት በጋዛ ውስጥ ያለውን የፍልስጤም ፖሊስ ማሰልጠን እና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቀጣናው የጸጥታ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ዮርዳኖስ እና ግብፅ ጋር መምከር እንዳለበት ዕቅዱ ይጠይቃል።

ሆኖም ግን ሃማስ እስከ አሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዳልፈታ እና የጋዛን አንዳንድ ክፍሎች ለመቆጣጠር ተዋጊዎቹን በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል።

28 Oct 2025, 14:21