እስራኤል በጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ፈጸመች እስራኤል በጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ፈጸመች  (ANSA)

እስራኤል በጋዛ ላይ በወሰደችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 100 ፍልስጤማውያን መሞታቸው ተገለጸ

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከማክሰኞ ዕለት አመሻሹ ጀምሮ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 100 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እና የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ተባብሶ ከቀጠለው ጥቃት መካከል የአከባቢው ባለስልጣናት ከፍተኛው እንደሆነ በገለፁት እስራኤል ከማክሰኞ አመሻሽ እስከ ረቡዕ ዕለት ድረስ በጋዛ ሰርጥ ላይ ባደረሰችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 100 ፍልስጤማውያን መሞታቸው ተገልጿል።

በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቃባይ ጥቃቱ የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉበት መኖሪያ ቤቶችን እና ድንኳኖችን ኢላማ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን፥ ከሟቾቹ መካከል 35 ህፃናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ ተከታታይ የአየር ድብደባ ጥቃቱን የፈጸመችው ሐማስ ስምምነት የተደረሰበትን የተኩስ አቁም ጥሷል በሚል እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፥ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቢሮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው ዘገባ “በደርዘን የሚቆጠሩ የሽብር ኢላማዎች እና አሸባሪዎች” ላይ ተከታታይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በራፋህ በእስራኤል ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ ጥቃት አንድ ተጠባባቂ ወታደር መገደሉን ተከትሎ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በዚህም የእስራኤል ባለስልጣናት ሃላፊነቱን አልወስድም ያለውን ሃማስን ተጠያቂ ያደረጉ ቢሆንም፥ ሐማስ ከጥቃቱ ጋር ‘ምንም ግንኙነት’ እንደሌለው በመግለጽ ለተኩስ አቁሙ አሁንም ተገዢ መሆኑን አስታውቋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ሐማስ ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል ወታደሮችን አጥቅቷል በማለት የወነጀሉ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር የታጋቾች አስከሬን ሲመለስ ጥሰት ተፈጽሟል ብለዋል።

እስራኤል ካትዝ ማክሰኞ ዕለት ሐማስ በጋዛ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት በመክፈት "በደማቁ የተሰመረውን ቀይ መስመር" ጥሷል ያሉ ሲሆን፥ ‘ሐማስ ወታደሮቻቸው ላይ ጥቃት በመፈጸሙ እንዲሁም የተሰው ታጋቾችን ለመመለስ የገባውን ስምምነት በመጣሱ በተደጋጋሚ ዋጋ ይከፍላል’ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ቀይ መስቀል የፍልስጤም እስረኞችን እንዳይጎበኝ መከልከሉ
በሌላ በኩል እስራኤል የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ተወካዮች የፍልስጤም እስረኞችን “ሕገ-ወጥ ተዋጊዎች” በሚለው ህግ መሰረት በመፈረጃቸው ምክንያት እንዳይጎበኙ መከልከሏ ተገልጿል።

ይሄንን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ የባለሙያ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት እንደዚህ ያሉ ጉብኝቶችን መፍቀድ “ብሔራዊ ደህንነትን በእጅጉ ይጎዳል” ብለዋል።

በእስራኤል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ሃሞክድ (HaMoked) በተጠቀሰው የእስራኤል እስር ቤት መረጃ መሰረት በጥቅምት ወር ብቻ እስራኤል 2,673 ፍልስጤማውያንን በህግ ቁጥጥር ሥር መያዟን ተመላክቷል።

30 Oct 2025, 13:29