በሃማስ ተይዘው የነበሩ ታጋቾች በመለቀቃቸው እስራኤላዊያን ደስታቸውን በአደባባይ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ለሁለት ዓመት ያህል የዘለቀውን ጦርነት ያስቆማል የተባለው እና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት የቀረበው የሰላም ዕቅድ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ በሕይወት ያሉ 20 ታጋቾች በሙሉ መለቀቃቸውን የእስራኤል መከላከያ ይፋ አድርጓል።
ታጋቾቹ በሃማስ የተወሰዱት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ በወሰደው ድንገተኛ ጥቃት ወቅት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፥ ከታጋቾቹ አንዱ የሆነው ኢታን ሞር በእስራኤል ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈው ዝግጅት ከቤተሰቡ ጋር ሲገናኝ ታይቷል።
ሃማስ ተገድለዋል ተብሎ የሚታሰቡትን 28 የሚደርሱ ታጋቾችን አስከሬን እስከአሁን ያልለቀቀ ሲሆን፥ የታጋች ቤተሰቦችን ወክሎ ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን እንዳሳወቀው አራት አስከሬኖች ሰኞ ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
በተለቀቁት ታጋቾች ምትክ እስራኤል 250 ፍልስጤማዊያን እስረኞችን እና ከ1,700 በላይ እስረኞችን መልቀቅ የጀመረች ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹ ቡድኖች በቀይ መስቀል አስተባባሪነት ራማላህ እና ጋዛ ከተማ መድረሳቸው ተነግሯል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ግብጽ ከማምራታቸው በፊት ለእስራኤል ፓርላማ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የታጋቾቹን መለቀቅ “አዲስ ጅማሮ” በማለት የገለጹ ሲሆን፥ ሰኞ ዕለት በግብጽ፣ ሻርም አል-ሼይክ ከተማ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ሰላም ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል።
በግብጽ የተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ዋና ዓላማው በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ሁለቱ አካላት የደረሱበትን ስምምነት ከፍጻሜ ለማድረስ እና የቀጠናው የሰላም ጥረቶች ላይ ለመወያየት እንደነበር የተነገረ ሲሆን፥ በኳታር፣ ቱርክዬ እና ዩናይትድ ስቴትስ አሸማጋይነት ለሶስት ቀናት ሲካሄድ በቆየ ጠንካራ ድርድር በኋላ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሶ፥ ስምምነቱ አርብ ዕለት ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ይታወሳል።
የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ለሁለት ዓመታት ስታካሂድ በነበረው ወታደራዊ ዘመቻ ከ67,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ባለሥልጣናቱ በግዛቱ ከፍተኛ ረሃብ መከሰቱን ይፋ አድርገዋል።