ሱዳን ውስጥ ባለው ግጭት ምክንያት አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች በየቀኑ እየጨመሩ መምጣታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሱዳን ውስጥ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. የእርስ በርስ ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቷ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ የተነገረ ሲሆን፥ ግጭቱን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወቅል። በቅርቡ የወጣው የዩኒሴፍ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ቴድ ቼይባን መግለጫ ሱዳን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ካሉ ቀውሶች ትልቁ ሰብዓዊ ቀውስ የሚገኝባት ሃገር መሆኗን እና ግጭቱ እየተባባሰ መምጣቱን በማረጋገጥ፥ በዚህም ግጭት በጣም እየተሰቃዩ የሚገኙት ደግሞ ህፃናት ልጆች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ምክትል ሥራ አስፈፃሚው ዳርፉርን እና ካርቱምን ከጎበኙ በኋላ እንደተናገሩት ይህ እየተካሄደ ያለው ግጭት የአከባቢውን ማህበረሰብ እንዴት እየከፋፈለ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፥ በጉብኝታቸው ወቅት በአልፋሸር እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ከበባ የተነሳ ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የተገደዱ ሴቶችን እና ህጻናትን ያነጋገሩት ሃላፊው በታጣቂዎች በሚጠበቁ የፍተሻ ኬላዎች ንብረቶቻቸው እንደተዘረፉ፣ እንግልትና ድብደባ እንደደረሰባቸው መናገራቸውን ብሎም በርካታ ቤተሰቦች ለቀናት ያለ ምግብ እና ውሃ መቆየታቸውን እንደነገሯቸው አስታውሰዋል።
አስከፊው እውነታ
በዳርፉር እና በኮርዶፋን 1.4 ሚሊዮን ህፃናት የረሃብ ስጋት ባለባቸው ወይም በረሃብ በተጠቁ አካባቢዎች ስለሚኖሩ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ቼይባን፥ ከዚህም በተጨማሪ “አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ካልተጀመረ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ” በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።
በሰሜን ዳርፉር ብቻ በዚህ ዓመት 150,000 የሚያህሉ ህፃናት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጋለጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ከአል ፋሸር የሚሸሹ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰባሰቡባት ታዊላ ከተማ የሚሰደዱ ሰዎች ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በወር ከመቶዎች ወደ 2,000 ከፍ ማለቱ ተገልጿል።
ከዚህም በላይ ወላጆች ልጆቻቸው ለዓመታት ትምህርት ቤት ሳይገቡ በመቅረታቸው በጣም እንደሚያዝኑ የገለጹት ቼይባን፥ በሱዳን ከሚገኙ አምስት ህጻናት አራቱ ማለትም ወደ 14 ሚልዮን የሚጠጉ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው እና አጠቃላይ ትውልዱ ያለ ትምህርት እያደገ እንደሆነ አሳስበዋል።
በሀገሪቱ የጤና ሥርዓቱ በመውደቁ የተነሳ ኮሌራ፣ የጉሮሮ በሽታ፣ ወባ እና የመሳሰሉት በሽታዎች የበርካታ ወጣቶችን እና ህጻናትን ህይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ህፃናት ልጆች ደህንነታቸው እንደማይጠበቅ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ግድያ እና የአካል መጉደልን ጨምሮ በሰሜን ዳርፉር ቢያንስ 350 ከባድ የመብት ጥሰቶች ሪፖርት ተደርጎ መረጋገጡን ቼይባን አስረድተዋል።
አል ፋሸር ለአስራ ስድስት ወራት ያህል በጦር ሃይሎች በመከበቧ ምክንያት 130,000 የሚሆኑ ህጻናት ያለ ምግብ፣ ውሃ እና ጤና አገልግሎት ሳያገኙ መቆየታቸውን ያመላከቱት ምክትል ሥራ አስፈፃሚው፥ ‘ወደ ውስጥ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት አስተማማኝ የሆነ መንገድ የለም’ ሲሉ አስምረውበታል።
በጨለማ ውስጥ የሚታይ የብርሃን ፍንጣቂ
ይህ በእንዲህ እያለ ግን በአስፈሪ ሁኔታዎች መካከል ሆነው የአከባቢው ማህበረሰቦች ህፃናቱ ትምህርት መማር እንዲጀምሩ ትምህርት ቤቶችን በጽናት እየገነቡ እንደሆነ የገለጹት ቼይባን፥ በጉብኝታቸው ወቅት ለህጻናት በተዘጋጀ ቦታ ላይ ህፃናቱ ሲሳሳቁ እና ሲጫወቱ ማየታቸውን ጭምር ገልጸዋል።
ቼይባን ሱዳንን ከጎበኙ በኋላ ከዩኒሴፍ ሰራተኞች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባልደረቦች እና አጋሮቻቸው ብሎም አደገኛ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠው ለ8 ሚሊየን ሰዎች የኮሌራ ክትባቶችን እና የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበሮችን የሰጡ፣ ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጋለጡ ከ250,000 በላይ የሚሆኑ ህጻናትን የተንከባከቡ፣ ወደ አካባቢው የተመለሱ ቤተሰቦችን ጨምሮ 11 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን የሚያገለግሉ የውሃ ስርዓቶች የጠገኑ ወይም የዘረጉ የፊት መስመር የጤና ሰራተኞችን አግኝተው ማነጋገራቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ የጠቆሙት ምክትል ስራ አስፈፃሚው፥ ፍላጎቶች በየቀኑ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሰው፥ “አሁን ሱዳን የምትፈልገው ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ በቂ የገንዘብ ድጋፍ እና ግጭቱን ለማስቆም ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው” በማለት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።