ከማኒላ በስተሰሜን ባለ መንደር ታይፎን የተሰኘው አውሎ ነፋስ ከተከሰተ በኋላ ከማኒላ በስተሰሜን ባለ መንደር ታይፎን የተሰኘው አውሎ ነፋስ ከተከሰተ በኋላ   (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ ‘በተፈጥሮ ላይ በደል የማድረሱን ሂደት ቀላል ማድረግ የለብንም’ ማለታቸው ተነገረ

በብራዚሏ ከተማ ቤሌም እየተካሄደ ከሚገኘው የኮፕ 30 ጉባዔ ጎን ለጎን የፊሊፒንሱ ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ዴቪድ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኙት የሃገራቸው ዜጎች መሆናቸውን አንስተው፥ በጉባዔው ላይ የሁሉንም ፊሊፒናውያን ድምጽ ማሰማታቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከኅዳር 1 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በብራዚል፣ ቤሌም ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው 30ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በርካታ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰማ እንደሚገኝ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በዚህ ጉባዔ ላይ የተገኙት በፊሊፒንስ የካልኦካን ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፓብሎ ቪርሊዮ ዴቪድ በመርሃ ግብሩ ላይ ከዚህን ቀደም ከማያውቁት እና ከኦሳ-ግራፊክ ፓቪሊዮን ከመጣ ከአንድ ሰው ጋር በተገናኙበት ወቅት ከፊሊፒንስ መመጣታቸውን ሲነግሩት፥ “የአየር ንብረት ለውጥ የመጀመሪያ ተጠቂ ከሆኑት መካከል አንዱ እንደሆንኩ” ነገረኝ በማለት ስለሁኔታው በማስታወስ ተናግረዋል።

ሰውዬው በመቀጠልም በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ የአንድ ዲግሪ የሙቀት መጠን መጨመር ሁሉንም የባህር ጠረፍ አለታማ ጉብታዎች እንዴት እንደሚያጠፋ የገለፀላቸው ቢሆንም፥ ነገር ግን ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ ይህንን እውነታ እንደሚያውቁት፥ እሳቸው እና ይሄንን እውነታ የሚነግራቸው ሰው ሌሎች ሰዎችም ይሄንን እውነታ እንዲረዱት በርካታ ነገር ማድረግ እንደሚገባቸው እንደተረዱ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ብዙ የውጭ አገር ሰዎች ወደ ባህር ዳርቻዎቻቸው በመምጣት ነጩ አሸዋ ላይ እንደሚዝናኑ በመግለጽ፥ “የሚረግጡት ነጭ አሸዋ ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ከአለታማው የባህር ጠረፍ ግግሮች የተሰባበሩ ቅሪቶች መሆናቸውን አይገነዘቡም” ካሉ በኋላ፥ እነዚህ አሸዋዎች ጥሩ ነገር ቢመስሉም፥ ነገር ግን ‘የሞተ ነገር ላይ እየረገጡ’ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ‘ሃገራቸው ለአየር ንብረት አደጋዎች እንግዳ የሆነች አገር ባትሆንም ሰዎች ስለ ፊሊፒንስ የማይገነዘቡት በርካታ ነገሮች አሉ’ በማለት ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ውጤቶች
ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ አዲሱ የሴቡ ሊቀ ጳጳስ ከተሾሙ በኋላ በደሴቲቱ ሰሜናዊ ክፍል ላይ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱን እና ከቀናት በኋላም በተመሳሳይ መንገድ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ፍሊፒናዊው ካርዲናል፥ በወቅቱ ሌሊት ላይ የጎርፍ ውሃው ከፍታው ጨምሮ የወንድማቸውን ቤተሰቦች ለመታደግ ያዩትን መከራ በማስታወስ አስቸጋሪ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱት አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች ቸልተኝነት እንደሆነ የገለጹት ካርዲናሉ፥ አብዛኛው የጎርፍ አደጋ የሚከሰተው በደንብ ባልተገነቡ የጎርፍ መከላከያ ስርዓቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ እነዚህ የመከላከያ ሥርዓቶች የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግባቸው የተገነቡ የከሸፉ ፕሮጄክቶች እና የሙስና ውጤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ በጎርፍ መከላከል ስም፥ ለትምህርት፣ ለጤና አጠባበቅ እና ለማህበራዊ ደኅንነት ሊውሉ የሚችሉ በቢሊዮን የሚቆጠር የሃገሪቱ ገንዘብ አላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው፥ የሃገሪቱ ህዝብ እንዴት በትክክል ምላሽ መስጠት እንዳለበት በማያውቅበት የአየር ንብረት ቀውስ እና የብልሹ አስተዳደር ሰለባ እንደሆነ አስታውሰው፥ በዚህም ‘ድርብ ተጎጂዎች’ እንደሆኑ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ የኮፕ ጉባዔውን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ ዝግጅቱን ከጴንጠቆስጤ በዓል ጋር በማመሳሰል ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ በርካታ ሰዎች እንደተሳተፉበት በመግለጽ፥ የተለያየ ማንነት ካለው በርካታ ህዝብ ጋር መገናኛት የሚያስደንቅ እንደነበር ጠቅሰው፥ በዚህም ሰዎች ኮፕ 30ን ምን ያህል በቁም ነገር እንደሚወስዱት አልተረዳሁም ነበር ካሉ በኋላ፥ “የጋራ ቤታችን ስለሆነችው ምድር በእውነት የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ አሳምኖኛል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ፥ ይህ ብቻውን ትልቅ የመጽናኛ ምንጭ እንደሆነ አስታውሰዋል።

በካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የፊሊፒንስን ህዝብ በመወከል በትውልድ ሀገራቸው ከደረሰው የአውሎ ንፋስ አደጋ ከተረፉ ሰዎች ጋር በመሆን ከዚህች የቱሪስት መዳረሻ ሃገር ጀርባ ያለውን እውነታ ማካፈላቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ፥ ፊሊፒንስን ከመልቀቃቸው በፊት ከሚንዳናኦ-ሱሉ ክልል የመጡ ብፁዓን ጳጳሳትን አግኝተው እንደነበር እና እነዚህም ጳጳሳት ‘የምድር ታሪፍ’ የተሰኘ በአየር ብክለት ላይ ብቻ ሳይሆን በማውጣት ሂደቱ ላይ ያተኮረ፣ ከመሬት ውስጥ በሚወጣው እያንዳንዱ የድፍድፍ ነዳጅ በርሜል ላይ ታሪፍ ለመጣል ሃገራት የሚስማሙበት ተጨባጭ የታሪፍ ሀሳብ ይዘው መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ታሪፍ በሚገኘው ገንዘብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደኖችን፣ አለታማ የባህር ግድግዳዎችን እና ስነ-ምህዳሮችን ለማደስ እንዲቻል ለአካባቢው ተወላጅ ማህበረሰቦች የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ሆኖ እንደሚያገለግል ያስረዱት ካርዲናሉ፥ ዋና መሰረቱ ከሆነው ከማውጣት ሂደቱ በመጀመር ብዝበዛን ልናስወግድ እንችላለን ብለዋል።

                                   ‘በተፈጥሮ ላይ የሚደርሰውን የበደል ሂደት ቀላል ማድረግ የለብንም’

“ለዓለም ሙቀት መጨመር አነስተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሰዎች ከሁሉም የበለጠ ይሠቃያሉ” ያሉት ካርዲናሉ፥ ነገር ግን በትክክል መደማመጥ ካለ ይሄን መለወጥ እንደሚቻል ጠቅሰው፥ የእርስ በእርሳችንን ድምጽ እና የምድራችንን ጩኸት በደንብ ከሰማን አሁንም ተስፋ አለ ብለዋል።

ለለውጥ የተደረገ ጥሪ
በኮፕ 30 ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ በማውገዝ ላይ ሳይሆን በለውጥ ላይ አተኩረው ባስተላለፉት መልዕክት “በሌላው ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልመጡ” ገልጸው፥ “የመጣሁት አብረን ቁጭ ብለን ለችግሮቹ መፍትሄ ለመፈለግ እንድንወያይ ለመጠየቅ ነው” ብለዋል።

አራቱ የማስታረቂያ መንገዶች ብለው የጠሯቸውን የካቶሊክ ትውፊቶች ማለትም ከኑዛዜ፣ ንስሐ፣ ጸጸት እና ይቅርታ በመነሳት የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ይሄንን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው አብራርተዋል።

መናዘዝ ማለት ውድቀታችንን፥ ያደረግነውን እና ለአካባቢ ጥበቃ ማድረግ ያልቻልነውን መቀበል ማለት እንደሆነ ገልጸው፥ ጸጸት ማለት ደግሞ 'ለፈጠርነው መከራ አዝናለሁ' የማለት ችሎታ እንደሆነ፣ ንስሐ በበኩሉ የሚገለጠው እርምጃዎችን ለማስተካከል በማካካሻ ድርጊቶች ላይ እንደሆነ እንዲሁም ይቅርታ የሚሰጥ እና የሚጠየቅ፣ ብሎም የሂደቶች ማጠቃለያ እንደሆነ አስረድተዋል።

እነዚህ አራት ነገሮች መሰረታዊ ተግባራት ከሆኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ሥነ ምህዳራዊ ለውጥ’ ብለው ለጠሩት አስተማማኝ ምልክቶች እንደሚሆኑ የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ዴቪድ፥ በመጨረሻም “የጋራ ቤታችንን ለማዳን እንችላለን፥ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደም” በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

17 Nov 2025, 12:56