የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አካል የሆነው ኮፕ30 በብራዚል የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አካል የሆነው ኮፕ30 በብራዚል   (AFP or licensors)

ኮፕ 30 የቅሪተ አካል ነዳጆችን ለማስወገድ ስምምነት ላይ ሳይደርስ መጠናቀቁ ተነገረ

ምንም እንኳን በአማዞን እምብርት ላይ ሲደረግ በነበረው የኮፕ 30 ጉባዔ ላይ ቀደም ብሎ ተስፋዎች ተደርገው የነበረ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን ጉባዔው የቅሪተ አካል ነዳጆችን የማስወገድ ጉዳይ ላይ ሳይስማማ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም ተጋላጭ አገራት ተስፋ እንዲቆርጡ እና የባለብዙ ወገን ሒደቱ ውጥረት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኮፕ የሚለው ስያሜ 'ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ' የሚሉት ቃላት ምህጻረ ቃል ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ፀባይ ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ስር የሚካሄድ የዓላማችን ዋነኛው የአካባቢ ጥበቃ ጉባዔ ነው።

ይህ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አካል የሆነው ኮፕ30 ለሁለት ሳምንታት በብራዚሏ ቤለም ከተማ ሲካሄድ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ ውስጥም 200 ከሚሆኑ ሃገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች የምድራችንን የሙቀት መጠን መቀነስ ላይ አተኩረው መነጋገራቸው ተጠቁሟል። 

የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ እንዳባባሰው የሚነገርለትን የበካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ለመቀነስ የዛሬ አስር ዓመት በርካታ ሃገራት ፓሪስ ላይ ከብዙ ክርክርና ድርድር በኋላ ተስማምተው የተፈራረሙ ቢሆንም፥ ከዚያ ወዲህ እንደታሰበው ከባቢ አየርን በካይ የሚባሉትን በኢንዱስትሪው ያደጉት ሃገራት የልቀት መጠንን መቀነሳቸው አጠያያቂ መሆኑ ይነገራል።

በብራዚሉ ጉባኤ ዋዜማ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት 10ኛ ዓመት በታሰበበት መድረክ የተገኙት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ተናግረዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ከተሳታፊና ተደራዳሪዎች በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ለችግር የተጋለጡ ሃገራት ነዋሪዎችም ድምፃቸውን ሊያሰሙ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፥ በተለይም የአማዞን አካባቢ ነዋሪዎች ለቀናት በባሕር ላይ ተጉዘው በስፍራው መገኘታቸው ትኩረትን ስቧል።

በአየርላንድ በሚገኘው የሜይኖት ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ስዌኒ ይህ የኮፕ 30 ጉባዔ ለእሳቸው አሥራ አምስተኛው የኮፕ ጉባዔ እንደነበር ገልጸው፥ ጉባዔው ሊገመቱ የሚችሉ መስመሮችን መከተሉን አመላክተዋል።

ነገር ግን የዘንድሮው ማጠቃለያ ብዙዎች ባልገመቱት ሁኔታ ያለስምምነት መጠናቀቁን ገልጸው፥ በርካቶችም በዚህ ቅር መሰኘታቸውን አስታውሰዋል።

ብዙ ቃል የተገባለት እና ትንሽ ብቻ የሰጠ ጉባዔ
ፕሮፌሰር ስዌኒ ብራዚል ከመሪዎች ጉባዔው ቀደም ብሎ ትልቅ መሰረት እንደጣለች በመግለጽ፥ ጉባዔውን በአማዞን መዘጋጀቱ ዓለም ችላ ሊለው የማይችለውን ተምሳሌታዊነት እና አጣዳፊነት ማሳየቱን ጠቁመው፥ አዘጋጅ ኮሚቴው በደን ጥበቃ፣ የቅሪተ አካል ነዳጅን ማስወገድን እና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሀገራት በሚደረገው ፋይናንስ ላይ ግልፅ ቁርጠኝነትን እንደሚያመጣ ተስፋ አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ትልቁ አሸናፊ በዋሽንግተን ተቀምጧል” ያሉት ፕሮፌሰር ስዌኒ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በዩናይትድ ስቴትስ እና በሳውዲ አረቢያ መካከል የተደረገው ስብሰባ ከመጨረሻው የምልአተ ጉባኤው ቀናት ቀደም ብሎ የጉባዔውን መግለጫ እጣ ፈንታ የሚያረጋግጥ ይመስላል ያሉ ሲሆን፥ በዚህም የየትኛውም የቅሪተ አካል ነዳጆች ጉዳይ መወገዳቸውን ገልጸው፥ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋና መንስኤዎች ወሳኝ ውሳኔዎች እንዲሰጡ ግፊት ለሚያደርጉት ለአብዛኞቹ ሃገራት ይህ መራራ ሽንፈት ነበር ብለዋል።

የዓለማችን ኃያል አገር አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ራሷን ከጉባኤው ያገለለች ሲሆን፥ ባለፈው መስከረም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ፕሬዝዳንቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚባለው ሐሰት መሆኑን እና አጭበርባሪዎች የፈጠሩት ሃሳብ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ይታወሳል።

በ 30 ዓመታት የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ የኮፕ ጉባዔዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋይት ሀውስ በቤሌም በተካሄደው ዝግጅት ላይ ምንም አይነት ይፋዊ ውክልና ያልነበረው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም በጉባዔው ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳደረ ውሳኔ እንደነበር ተነግሯል።

ከጉባኤው አዳራሽ ውጪ የአየር ንብረት ለውጥ እውነታዎችን የሚያንፀባርቁ እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ፣ እና የእሳት አደጋን የመሳሰሉ ሌሎች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰሩ፥ ሁሉም ተምሳሌታዊ መስተጓጎሎች በታዛቢዎች ሳይስተዋሉ መቅረታቸውን በአግራሞት ተናግረዋል።

እያሽቆለቆለ የሚገኘው ሥርዓት
በኮፕ ጉባዔዎች ለረጅም ጊዜ ሲተች የነበረው የሙሉ ድምጽ ህግ መሆኑን ያስታወሱት ስዌኒ፥ በየዓመቱ አንድ ወይም ሁለት ሃገራት መላውን ዓለም እንደመያዣነት እንደሚይዙ ጠቁመው፥ ክብደት ያለው ድምጽ መስጠት እና የአናሳ ውክልና ሞዴሎችን የመሳሰሉ የሥርዓት ማሻሻያ ሙከራዎች በየዓመቱ ውይይት እንደሚደረግባቸው፥ ነገር ግን ሁልጊዜ ጉዳት ከደረሰባቸው ሃገራት ተጠቃሚ በሆኑ ሃገራት ውድቅ ይደረጋሉ ብለዋል።

የኮፕ ጉባኤ አስተናጋጅ አገራት በስብሰባው የፕሬዝዳንትነት ሚና ስለሚኖራቸው የጉባኤውን ግቦች ለመቅረጽ ከመቻላቸው በተጨማሪ፣ የራሳቸውን የአየር ፀባይ ለውጥን የተመለከቱ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ የሚያስችላቸው ሲሆን፥ በተጨማሪም በጉባኤው ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመሸምገል እና መፍትሄ ለማስቀመጥ ሥልጣን ያገኛሉ።

ነዳጅ አምራች ሃገራት ጉዳዩን ለመቀየር ምንም ዓይነት ፍላጎት አለማሳየታቸውን ያስታወሱት ስዌኒ፥ የገቢ ፍሰቱ እስከቀጠለ ድረስ የመለወጥ ሃሳቡ እንደሌላቸው በመግለጽ፥ ህንድ እና ኢንዶኔዥያን የመሳሰሉ ዋና ዋና የችግሩ መንስኤዎች እንኳን ሳይቀሩ በተመሳሳዩ የቅሪተ አካል-ነዳጅ መንገዶች ላይ ኢንዱስትሪያቸውን ለማስቀጠል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የ ኮፕ ጉባዔ ዘላቂ እሴት እና ገደቦች
በብራዚሏ ቤሌም ከተማ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የቀረበውን የቅሪተ አካል ነዳጆችን ለማስወገድ የቀረበዉን ፍኖተ ካርታ ሀሳብ የተወሰኑ ሃገራት የደገፉት ቢሆንም፥ ጉባዔው ያለስምምነት መጠናቀቁን የገለጹት ስዌኒ፥ አሁንም ድረስ ጉዳዩ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ሂደቱ ወደፊት እንደሚቀጥል ገልጸው፥ ምክንያቱንም ሲገልፁ “የኮፕ ጉባዔ ትንንሾቹ ሃገራት ትልልቆቹን ሃገራት በእኩልነት ማስተናገድ ከሚችሉባቸው ጥቂት መድረኮች አንዱ በመሆኑ ነው” ብለዋል።

እ.አ.አ. በ 2015 በፓሪስ በተካሄደው የኮፕ 21 ጉባዔ ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ለመገምገም የዘንድሮው ጉባኤ አጀንዳ አድርጎ የነበረ ሲሆን፥ በወቅቱ 196 የሚሆኑ አካላት የዓለም የሙቀት መጠንን ከኢንዱስትሪው አብዮት በፊት ወደ ነበረበት ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመተግበር መስማማታቸውን ፕሮፌሰር ስዌኒ አስታውሰው፥ ነገር ግን አሁን ባለው መዋቅር የኮፕ ጉባዔ ዓለማችንን ከ 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ማድረግ እንደማይችል አስጠንቅቀዋል።

ሆኖም ፕሮፌሰር ስዌኒ እንዳስታውሱት፣ ሂደቱ ፍፁም ስለሆነ ሳይሆን በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት አሁንም ድምፃቸው የሚሰማበት ቦታ ስለሚያስፈልጋቸው ሥራው መቀጠሉን ገልጸው፥ በዚያ ደካማ እና ፍጽምና የጎደለው የሃገራት ስብስብ ውስጥ ምንም እንኳን ደካማ ቢሆንም የጋራ ተስፋ የመሆን ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።

ይህ ዓመታዊ ጉባኤ መካሄድ የጀመረው እ.አ.አ. በ 1992 ዓ.ም. የአየር ፀባይ ለውጥ የዓለማችን ስጋት መሆኑ በመንግሥታቱ ድርጅት ተቀባይነት አግኝቶ ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው።

ለአፍሪካ አህጉር የተሰጠውን የኮፕ32 ጉባኤ አስተናጋጅነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ ተመርጣለች።

25 Nov 2025, 13:23