ፍልስጤማዊያን ህፃናት  ንብረታቸውን ተሸክመው በጋዛ ከተማ በሚገኘው እና ያልፈነዳ  ሚሳየል የተጣለበት የቆሻሻ መጣያ በኩል ሲያልፉ ፍልስጤማዊያን ህፃናት ንብረታቸውን ተሸክመው በጋዛ ከተማ በሚገኘው እና ያልፈነዳ ሚሳየል የተጣለበት የቆሻሻ መጣያ በኩል ሲያልፉ   (AFP or licensors)

በጋዛ የሚታየው እጥረት አሁንም የዕለት ተዕለት ኑሮን እያከበደ መሆኑ ተነገረ

በጋዛ ውስጥ የምግብ አቅርቦቶች ቀስ በቀስ ወደ መደርደሪያዎች እየተመለሱ መሆኑ ቢነገርም፥ ነገር ግን ሁኔታው አሁንም አስቸጋሪ እንደሆነ እና የአቅርቦቶች እጥረት እንዳጋጠመ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ውስጥ የምግብ አቅርቦት ላይ ቀስ በቀስ መሻሻሎች ቢታዩም፥ ነገር ግን በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ለሁለት ዓመታት በተደረገው ጦርነት ምክንያት እጥረቱ አሁንም ከባድ መሆኑ ተነግሯል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጥቅምት ወር ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ለተመለሱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚደረገው የእርዳታ አቅርቦት አሁንም በጣም ውስን መሆኑን ገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በጋዛ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ የምግብ እሽጎች አሰራጭቷል።

አቅርቦቶች የተወሰኑ ቢሆንም፥ የአከባቢው ቤተሰቦች ለ10 ቀናት የሚቆይ አነስተኛ የምግብ አቅርቦት እየተቀበሉ እንደሆነ ተቋሙ ገልጿል።

በሌላ በኩል የሕፃናት ሲሰጥ የነበረው የመጀመሪያ ደረጃ የክትባት ዘመቻ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን፥ ለሁለት ዓመታት ያክል ሲካሄድ የነበረው ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን መሰረታዊ የጤና እንክብካቤ እንዳያገኙ ማድረጉ ቢታወቅም፥ ነገር ግን በአከባቢው የሚገኙ ህፃናት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ቀድሞ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ክትባቶችን ማግኘታቸው ተጠቁሟል።

ይህ በዩኒሴፍ፣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ (UNRWA) የተመራው ዘመቻ የሥነ-ምግብ ቁጥጥርንም ማካተቱ ተነግሯል።

የዚህ ዘመቻ ግብ 44,000 ለአደጋ የተጋለጡ ህጻናትን መድረስ ሲሆን፥ በርካቶቹ ህፃናት በጦርነቱ ወቅት መደበኛ ክትባቶች ያመለጣቸው እንደሆነ እና የአከባቢው ባለሥልጣናት እንደገለጹት ክፍተቱ ክረምት እየቀረበ በመጣ ቁጥር ለገዳይ ወረርሽኞች የመጋለጥ እድልን ከፍ ማድረጉን አስጠንቅቀዋል።

የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 10 ድረስ በ149 ጤና ጣቢያዎች የተካሄደ ሲሆን፥ የዘመቻው ተንቀሳቃሽ ቡድኖች በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ህፃናት እየፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ክትባቶችን፣ መርፌዎችን፣ የማቀዝቀዣ መሳሪያዎችን እና የተመጣጠነ የምግብ ዕርዳታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀቱን እና ለጥረቱ መሳካት ከ450 በላይ ልዩ ባለሙያዎችን (ስፔሻሊስቶችን) ማሰልጠኑን ገልጿል።

26 Nov 2025, 14:11