2025.11.20 treasures within 2025.11.20 treasures within 

'በውስጣችን ያለን ውድ ሀብት' የተሰኘው መጽሃፍ ር.ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለህፃናት የነበራቸው መልዕክት የተላለፈበት ነው ተባለ

ሎዮላ ፕሬስ የተባለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የህትመት ተቋም 'በውስጣችን ያለን ውድ ሀብት' (Our Treasures Within) የተሰኘ ሥዕላዊ የህፃናት መጽሃፍ አሳትሞ የለቀቀ ሲሆን፥ ይህ መጽሃፍ ፒተር እና ፖል ሬይኖልድስ በተባሉ ደራሲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ህፃናት ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ስጦታዎች እንዲያውቁ እና እንዲካፈሉ ባደረጉት ጥሪ ላይ በመነሳሳት የተፃፈ እንደሆነ፥ ብሎም ህፃናት እና ቤተሰቦች ተሰጥዎቻቸው ለሌሎች ማበርከት የሚችሉበትን መንገድ እንዲያሰላስሉ ያበረታታል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሎዮላ ፕሬስ በተባለው የካቶሊክ ማተሚያ ድርጅት የታተመው ይህ ምስላዊ የህፃናት መጽሃፍ ፒተር ሬይናልድስ እና ፖል ሬይኖልድስ በተባሉ ሁለት ደራሲያን የተፃፈ ሲሆን፥ ከጥር 12 ጀምሮ በጥራዝ ደረጃ እና በዲጂታል ለተጠቃሚዎች መቅረብ እንደሚጀምር ተገልጿል።

አዲሱ መጽሃፍ ዋና ሃሳቡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በተደጋጋሚ ባቀረቡት ግብዣ ሰዎች እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያስቀመጠውን ስጦታዎች እንዲያውቁ እና እንዲያካፈሉ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር ወጣት አንባቢዎች እና ቤተሰቦች የግል ተሰጥዖአቸውን ለሌሎች ጥቅም ማበርከት የሚችሉበት መንገድ ላይ እንዲያሰላስሉ ዕድል እንደሚሰጥም ተነግሯል።

እ.አ.አ. በ 2022 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዚህ ዓለም ድካም ካረፉ በኋላ ባሉት ወራት ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል።

ደራሲዎቹ
ሥዕላዊ የህፃናት መጽሃፍትን በመፃፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ፒተር ሬይኖልድስ ስለ መጽሃፉ እንደተናገረው እሱ እና ወንድሙ ነፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለህፃናት እና ተንከባካቢዎቻቸው ያስተላለፉትን መልዕክት ለማስተላለፍ በማሰብ ይሄንን መፅሃፍ እንደፃፉ የገለጸ ሲሆን፥ መጽሐፉ እ.አ.አ. በ 2016 ዓ.ም. ‘የተወደዱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ’ በሚል ርዕስ የተፃፈውን መፅሃፍ ጨምሮ፥ ቀደም ሲል በሎዮላ ፕሬስ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መካከል የተደረጉትን ትብብሮች ተከትሎ መፃፉን ተናግሯል።

የሎዮላ ፕሬስ ፕሬዚዳንት እና አሳታሚ ጆሊን ሲቺያሬሊ መጽሐፉ በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኙ አንባቢያን የመኖር ዓላማቸውን እንዲረዱ እና ሰፊውን ማህበረሰብ ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ እንዲያሰላስሉ ለማበረታታት መሆኑን ገልጸው፥ መፅሃፉ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታዋቂ አስተንትኖዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን “በቀላሉ ስለማይገኝ ‘ውድ ሀብት ፍለጋ’ የሚለውን ጨዋታ እንደመጫወት ነው፥ ነገር ግን አንዴ ካገኛችሁት ለሌሎች አካፍሉት” የሚለውን ማካተቱ ተነግሯል።

21 Nov 2025, 13:47