‘ሳግራዳ ፋሚሊያ’ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ካሉት ረጅሙ ቤተክርስቲያን መሆኑ ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በስፔን ትልቋ ከተማ በሆነችው ባርሴሎና ውስጥ የሚገኘው የሳግራዳ ፋሚሊያ ባሲሊካ ማዕከላዊ ግንብ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ የተጀመረ ሲሆን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ምስል የያዘው የመጀመሪያው የመስቀል አካል በግምቡ ማማ ላይ እንደሚኖር እና በዚህም ጭማሪ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑ በይፋ በዓለም ላይ ካሉት አቢያተ ክርስቲያናት ረጅሙ ተብሎ መመዝገቡ ተገልጿል።
በአሁን ወቅት ላይ 162.91 ሜትር የሚረዝመው በባርሴሎና የሚገኘው ባዚሊካ እ.አ.አ. ከ 1890 ዓ.ም. ጀምሮ ረጅሙ ተብሎ ከሚታሰበው በጀርመን ከሚገኘው ‘ኡልም ሚንስተር’ ቤተክርስቲያን ሪከርዱን የወሰደ ሲሆን፥ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል የተቀረጸበት ማዕከላዊው ግንብ ሲያልቅ ባዚሊካው 172 ሜትር ቁመት ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
7.25 ሜትር ቁመት እና 24 ቶን የሚመዝነው ይህ አዲሱ ክፍል የመስቀሉ የታችኛው ክንድ ሲሆን፥ ይህም ክፍል ተሰርቶ ወደ ከተማው የመጣው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ እንደሆነ እና ከማዕከላዊው የባህር ኃይል 54 ሜትር ርቀት ላይ ባለው ሥፍራ ተቀምጦ እንደነበር ተነግሯል።
ይህ ተከላ በረጃጅሞቹ የባሲሊካ ማእከላዊ ማማዎች ላይ ትልቅ እመርታን ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ ከ150 ዓመታት በፊት የተጀመረው የሳግራዳ ፋሚሊያ ግንባታ መጠናቀቅ ታሪካዊ ወቅት ይሆናልም ተብሏል።
ይህ ባዚሊካ በግንባታው ወቅት በርካታ መሰናክሎች እና ፈተናዎች አጋጥመውት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ የህንፃው አርክቴክቱ አንቶኒ ጋውዲ ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት ባረፈበት ወቅት ታቅደው ከነበሩት 18 ማማዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ተሰርቶ እንደነበር እና ከዚያም በስፔን ተከስቶ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሥርዓት አልበኞች የቤተክርስቲያኑን የታችኛውን ክፍል በእሳት አቃጥለው በነበረበት ወቅት የወደፊቱን ግንባታ ለመምራት የተዘጋጁ እቅዶችን እና መዋቅሮቹን ማውደሙን ተነግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ በኮቪድ19 ወረርሽኝ ወቅት በርካታ የፋውንዴሽኑ አባላት የቱሪዝም ገበያው በመጥፋቱ ምክንያት ያበረክቱት የነበረው የገንዘብ ድጋፉ በማሽቆልቆሉ ግንባታው ቆሞ እንደነበረ ተገልጿል።
የሳግራዳ ፋሚሊያ ዋና ዳይሬክተር ዣቪየር ማርቲኔዝ መስከረም ወር ላይ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል የተቀረጸበት የቤተክርስቲያኑ የላይኛው ክፍል የህንፃው አርክቴክት ጋውዲ ሞት 100 ኛ ዓመት ጋር ተያይዞ በጎረጎሳዊያኑ 2026 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፥ በባሲሊካው የታችኛው ክፍል ውስጥ የተቀበረውን የአርክቴክቱን መቶኛ ዓመት ለማስታወስ በርካታ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል።