ጥቅምት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በታንዛኒያ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ በዳሬሰላም ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ተቃዋሚዎች እየተቃጠሉ የነበሩ ሕንፃዎች አከባቢ ሲሰበሰቡ ጥቅምት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በታንዛኒያ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ በዳሬሰላም ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት ተቃዋሚዎች እየተቃጠሉ የነበሩ ሕንፃዎች አከባቢ ሲሰበሰቡ   (AFP or licensors)

ሰላማዊ የነበረችዋ ታንዛኒያ በቅጽበት አለመረጋጋት ውስጥ መግባቷ ተነገረ

በታንዛኒያ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በተከሰተው ብጥብጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ ሀገሪቱ ወደ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ መግባቷም ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በታንዛኒያ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች የተቃዋሚ ደጋፊዎች ባለፈው ጥቅምት 26 የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሲሆን፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንገዶችን በመዝጋት፣ ጎማ በማቃጠል በመንገድ ላይ ያገኟቸውን የፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ፖስተሮችን በመቀዳደድ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ሰላማዊ በመሆኗ የምትታወቀው አፍሪካዊት አገር ሙሉ በሙሉ ወደ ትርምስ ውስጥ መግባቷ እየተነገረ ይገኛል።

ለህክምና ወደ ጣሊያን ሄዳ በሃገሪቱ ውስጥ በተከሰተው ብጥብጥ ምክንያት ወደ ሃገሯ መመለስ ያልቻለችው ጃኪ የምትባል የሃገሪቱ ነዋሪ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራት ቆይታ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በማተኮር እንደተናገረችው “ለእነዚህ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት… ዝም ማለት አንችልም” ብላለች።

በፍጥነት የተቀያየሩ ሁኔታዎች
ምርጫው ብዙ ጊዜ ለውጥ ለማድረግ እና የእያንዳንዱን ሰው ድምጽ ለማሰማት እንደ እድል ሆኖ የሚታይ ሲሆን፥ ሰላማዊ በሆነችው የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ታንዛኒያ ግን የሁከት መንስኤ ሆኗል።

የዋናው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በእስር ላይ በመሆናቸው እና ሌላኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ከምርጫው እንዲሰረዙ በመደረጉ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሳሚያ የማሸነፍ ዕድላቸውን እንዲሰፋ ሲል ዲሞክራሲን ዝቅ እያደረገ ነው በማለት ተቃዋሚዎች ይከስሳሉ።

በታንዛኒያ ያለው አማካይ ዕድሜ 18 አካባቢ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ እነዚህ ወጣት ሃይሎች የለውጥ ጎዳናን በመፈለግ ወደ ሰላማዊ ተቃውሞ መግባታቸው ይነገራል።

እ.አ.አ. በ2021 የፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሞትን ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚደንት ሳሚያ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ከምርጫ ከተገለሉ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቱን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ተገምቶ የነበረ ሲሆን፥ ሐሙስ ዕለት የምርጫ ኮሚሽኑ ሳሚያ በደቡብ ምዕራብ ምቤአ ግዛት 95 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ ማግኘታቸውን ይፋ ማድረግ ከጀመረ በኋላ የተቃዋሚዎች ቁጣ ጨምሮ ሃገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።

ይሄንን ተከትሎ በዳሬሰላም እና ዋና ዋና ከተሞች የሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን፥ የታንዛኒያ መንግሥት የተነሳው ሁከት እምብዛም ሰፊ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፥ የተጣለው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ግን እንዲራዘም ተወስኗል።

ምርጫው ፍትሐዊ አይደለም በሚል ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ ከወጡት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ፥ ወጣቶቹ ዋነኛ ተቃዋሚዎችን ከምርጫው በማገድ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አፍኗል ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ የነበራት ጃኪ ስለጉዳዩ ስትናገር የመንግስት ወታደሮች ወደ ሰዎች ቤት በመግባት ጥይት ሲተኩሱ እንደነበር በመግለጽ፥ በዚህም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ተናግራለች።

አብዛኞቹ ሆስፒታሎች መረጃ ለመስጠት ባይፈቅዱም፤ በዳሬ ሰላም የሚገኝ ሆስፒታል ካለፈው ሐሙስ አንስቶ በተጎጂዎች እንደተሞላ እና የተገደሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁሟል።

ታንዛኒያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ገዢው ፓርቲ ሲሲኤም የአገሪቱን ፖለቲካ እና መንበረ ሥልጣን ተቆናጦ የቆየ ሲሆን፥ ፕሬዝዳንት ሳሚያ በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያዋ ሴት የአገሪቱ መሪ ሆነው ሲሾሙ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸው እንደነበርም ይታወሳል።

ብቸኛዋ የፕሬዚዳንትነት እጩ ተወዳዳሪ ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን አሸናፊ መሆናቸው ከተገለጸ በኋላ የሃገሪቷ ሰላም መደፍረሱን የምትናገረው ጃኪ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መገደላቸውን፣ የታንዛኒያ ፍርድ ቤት ከ200 በላይ ሰዎችን በአገር ክህደት መክሰሱን እና ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ቅጣታቸው ሞት እንደሆነ መግለጹን ተናግራለች።

ድብቅ ሴራ መኖሩ
ጃኪ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ውጥረቶች እና ፍርሃቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን በማስታወስ፥ የምርጫው ብጥብጥ በድንገት እንዳልመጣ የጠቀሰች ሲሆን፥ በዚህም በርካታ የተለየ የፖለቲካ አቋም የነበራቸው ተወካዮች በጣም ኦፊሴላዊ ባልሆነ መንገድ እየተያዙ ወይም እየተገደሉ እንደነበር ገልፃ፥ “ሰዎች ተቀባይነት የሌለው ነገር እየተፈጸመ መሆኑን ቀስ በቀስ ይገነዘቡ ነበር” ስትል ተናግራለች።

እንደ አንድ ቤተ ክርስቲያን መቆም
ህብረተሰቡ አሁንም የምርጫውን መዘዝ እና ውጤት እየተጋፈጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ሰዓት ሊገደል ወይም ሊታሰር ስለሚችል “ማንኛውም ሰው ወይም ማህበረሰብ የራሱን አቋም መያዝ እንደማይችል በምሬት የገለጸችው ጃኪ፥ የአከባቢው ካህናት እንኳን ሳይቀሩ እውነትን ከተናገሩ ሞት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ገልፃለች።

የጥቃት ዛቻ ቢኖርም የምቤያ ሃገረ ስብከት ለተገደሉት፣ ለተጎዱት እና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅምት 30 የጸሎት ቀን እንዲሆን በማወጅ መስዋዕተ ቅዳሴ የተከናወነ ሲሆን፥ በዚህም መርሃ ግብር ላይ የዳሬሰላም ሊቀ ጳጳስ ጁድ ታዴዎስ በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ደም መፋሰሱን በግልጽ አውግዘዋል።

ነገር ግን ጃኪ አንድም የሰበካ ካህን የሚያስከትለውን መዘዝ በመገንዘብ በራሱ ምንም ማለት እንደማይችል በድጋሚ በመግለጽ፥ ይህም በመሆኑ ብፁዓን ጳጳሳቱ ስለ ምርጫው እና ስለተፈጠረው ሁከት ምላሽ ለመስጠት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁማ፥ በዚህ መንገድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን አብሮነት መግለጽ እንደሚችሉ የገለጸች ሲሆን፥ “ማንኛውም የመንግስት አካል አንድን ሰው ሊገድል ይችላል፥ ነገር ግን አንድን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ስለማይችሉ አንድ ላይ መልስ መስጠት የተሻለው አማራጭ ነው” ስትል ጃኪ ተናግራለች።

የታንዛኒያ እውነተኛ ገጽታ
የዳሬ ሰላም ሊቀ ጳጳስ በመስዋዕተ ቅዳሴው መግቢያ ላይ እንደተናገሩት ከምርጫው በኋላ በተከሰቱት ግጭቶች “በርካታ ህዝብ መቁሰሉን እና ሰብዓዊ ክብሩን መነፈጉን” አሳስበው፥ ሃገሪቷ ክብሯን ከማጣቷም ባለፈ “በጅምላ” የተገደሉ ሰዎችን አጥታለች ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ጁድ ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ተቃውሞዋቸውን በመግለፃቸው በጥይት መመታት ቅጣት መሆን እንደሌለበት አሳስበው፥ አንዳንዶቹም በቤታቸው ውስጥ እያሉ መገደላቸውን ጠቁመው፥ ‘ይህ ድርጊት የታንዛኒያን እውነተኛ ገጽታ በጥቂቱም ቢሆን አያንጸባርቅም’ ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ ምንም ማብራሪያ የሌለው፣ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ተግባር ነው ሲሉ አስምረውበታል።

ጃኪ በበኩሏ ታንዛኒያ በሰላማዊ ባህሏ ታዋቂ እንደነበረች በመግለጽ፥ እ.አ.አ. በ1961 ዓ.ም. ሀገሪቱ ከብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ነፃ ስትወጣ እንኳን በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላማዊ መንገድ እንደነበር አስታውሳ፥ ወዳጃዊ፣ ትብብር እና መተጋገዝ እውነተኛ የታንዛኒያ ገጽታ መሆኑን በመግለጽ፥ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ወደ 147 የሚጠጉ ነገዶች አብረው መኖር እና መነጋገር የሚችሉ ህዝቦች እንደሆኑ አስረድታለች።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ ይህን አስቸጋሪ እንዳደረገው የገለጸችው ጃኪ፥ ታንዛኒያ ‘በጣም መቁሰሏን’ እና የዘንድሮው ምርጫ ክፍፍል መፍጠሩን ተናግራለች።

ድምፃቸው ላልተሰማው ድምጽ መሆን
የአጥቢያ ቤተክርስትያን ለደም መፋሰሱ ከሰጠችው ምላሽ ባሻገር፣ ከቫቲካን የመጣው ድምጽ በታንዛኒያ ስላለው አስከፊ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ባደረጉት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ወቅት “ህዝቡ ከማንኛውም ዓይነት ሁከት እንዲርቅ እና የውይይት መንገድን እንዲከተል” ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት “በዓለም ላይ ያልተሰሙትን ድምጾችን” ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለሚያመጣ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጃኪ ገልጻለች።

ይህ የተስፋ መልእክት የአብሮነት ምልክት እና በአመፅ ውስጥ ለሚኖሩ የታንዛኒያ ህዝቦች ማበረታቻ እንደነበር ገልፃ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግር “ቤተ ክርስቲያን ከታንዛኒያ ህዝብ ጋር እንዳለች” እና “ብቻቸውን እንዳልሆኑ” ያረጋግጥላቸዋል ብላለች።

ቀጣዩ ጊዜ ምን መሆን አለበት?
ጃኪ በመጨረሻም ወደፊት መደረግ ስለሚገባው ነገር ስትናገር ‘ምንም እንኳን አዲስ ምርጫን ተስፋ ማድረግ ባይቻልም’ ነገር ግን የማህበረሰቡን እምነት መልሶ ለመገንባት እና የትብብር እድሎችን ለመፍጠር እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ገልፃ፥ ‘የሰዎች መብት የሚከበርበት እምነት እና እውቀት መመለስ አለበት’ ብላለች።

12 Nov 2025, 13:29