በመካከለኛው ሱዳን በተባባሰው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሰደዳቸው ተገለጸ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሱዳን ጦር እና በፈጣን ደጋፊ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል በተካሄደው አሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈናቀሉ 14 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ስቃይ እየተባባሰ መሄዱ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ግጭቱ ተባብሶ በመቀጠሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መሰደዳቸው ተነግሯል።
በ 2015 ዓ.ም. ሱዳንን ለረጅም ዓመታት የመሩት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ በሱዳን ጦር ሃይሎች መሪ እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መሪ መካከል በተከሰተው የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ እንደተጀመረ የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ 120,000 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው ይገለፃል።
ባለፈው ሳምንት የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች የኤል ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ በሰሜናዊ ዳርፉር በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ እና የጦር ወንጀል ሪፖርቶችን ተከትሎ፥ በዚህ በማዕከላዊ ሱዳን ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት የአከባቢው እማኞች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት እንደገለጹት ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመላክተዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ዘገባ ከሆነ ከበርካታ የአከባቢው ከተሞች እና መንደሮች የተፈናቀሉት ሰዎች ከዓርብ እስከ እሑድ ባሉት ቀናት በሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ወደምትገኘው ባራ ከተማ አካባቢ መሰደዳቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ኮርዶፋን ከምዕራብ ዳርፉር ክልል ጋር በመሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግጭቱ ዋና ማዕከል መሆኗ ተመላክቷል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሱዳን ያለውን ሁከት አውግዘው አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ፣ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ውይይት እንዲደረግ፣ የሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲከፈቱ እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሥራዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሀገር የተከሰተው ቀውስ ከዓለም ትልቁ የሰብአዊ አደጋ እንደሆነ በመግለጽ፥ ተጠናክሮ እየቀጠለ ካለው ጥቃት በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ የሃገሪቱ ክልሎች ረሃብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስጋት ላይ መጣሉን አስጠንቅቀዋል።