ሊባኖስ እንደገና አለመረጋጋት ውስጥ መግባቷ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክርስትና እምነት ተከታይ ያለባት ሊባኖስ በእስራኤል እና በሔዝቦላህ መካከል የሚደረገው ጦርነት ምክንያት በድጋሚ አለመረጋጋት ተጋርጦባታል።
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ ላይ በፈጸመው ጥቃት የሔዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣንን መግደሏ የተነገረ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦር ከወራት በኋላ በደቡባዊ ቤይሩት ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመርያው ነው ቢባልም ይሄንን ተከትሎ ሃገሪቱ ዳግመኛ አለመረጋጋት ውስጥ መግባቷ እየተነገረ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ ዕለት የበጀት ቅነሳን እና በሊባኖስ የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሃይል (UNIFIL) ስልጣንን ለአንድ ዓመት ብቻ እንዲራዘም መወሰኑን በመጥቀስ ትልቁን የሰላም አስከባሪ ሃይል ቅነሳ ትግበራውን በደቡባዊ ሊባኖስ ማስጀመሩን የገለጸ ሲሆን፥ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ህዳር 2017 ዓ.ም. ከተፈረመ በኋላ ስምምነቱን ከ10,000 ጊዜ በላይ በመጣስ ከ300 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ባለፈው ወር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ እና በፈረንሳይ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሰዎች እና ተቋማት ማጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
በስምምነቱ መሰረት እስራኤል በጥር ወር ላይ ከደቡባዊ ሊባኖስ አጠቃላ መውጣት የሚጠበቅባት ሲሆን፥ ነገር ግን ሠራዊቱ በከፊል ብቻ በመውጣት አምስት የድንበር ምሽጎችን ይዞ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የሊባኖስ ባለስልጣናት ስምምነቱ በአመዛኙ ለስም ብቻ የተደረገ መሆኑን በመግለጽ፥ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ5,000 በላይ የመሬት፣ የአየር እና የባህር ጥሰቶች ሪፖርት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን በደቡባዊ ሊባኖስ ቢያንስ አምስት ቦታዎችን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ የምትገኘው እስራኤል፤ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታቆም እና ከአገሪቱ ለቅቃ እንድትወጣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የሶሪያ እና የፍልስጤም ስደተኞችን የምታስተናግደው ሊባኖስ እ.አ.አ. በ 2019 ዓ.ም. ከጀመረው ጥልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር እየታገለች የምትገኝ ሲሆን፥ ይህም ሃገሪቱ የዋጋ ንረት፣ ድህነት እና ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል ተብሏል።