የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት የፍልስጤም እና የእስራኤል ጦርነት  (AFP or licensors)

በጋዛ የዕርዳታ አቅርቦት መቀነሱ በነዋሪው የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ችግር ማስከተሉ ተገለጸ

እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ግብፅ ለማስገባት የራፋህ መስቀለኛ መንገድ ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኗን ባለስልጣናቱ አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለስልጣናቱ ረቡዕ ኅዳር 24/2018 ዓ. ም. እንዳስታወቁት፥ “እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ግብፅ ለማስገባት የራፋህ መስቀለኛ መንገድ ለመክፈት ዝግጅት ላይ ትገኛለች” ብለዋል።

ሰዓቱ በውል ባይገለጽም ነገር ግን መንገዱ መከፈቱ ለሕክምና እና ለሌሎች ዓላማዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን እንደሚፈቅድ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ባለስልጣናቱ እርምጃው የተኩስ አቁም ስምምነት ተገባራዊነትን ለማሳየት የተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣን፥ ከፍተኛ የዕርዳታ ክምችት ወደ ጋዛ እንዳይገባ አሁንም መታገዱን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች የዕርዳታ እና የሥራ ኤጀንሲ የሚዲያ አማካሪ የሆኑት አድናን አቡ ሃስና፥ ኤጀንሲው የምግብ፣ የመድኃኒት እና የክረምት መጠለያ አቅርቦቶችን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ድንኳኖች፣ ብርድ ልብሶች እና ልብሶች ያሉት ቢሆንም ነገር ግን እስራኤል ዕርዳታው ወደታሰበው አካባቢ እንዳይደርስ መከልከሉን ተናግረዋል።

ባለስልጣን ከፍተኛ የዕርዳታ ክምችት ወደ ጋዛ እንዳይገባ መታገዱን ይናገራሉ
ባለስልጣን ከፍተኛ የዕርዳታ ክምችት ወደ ጋዛ እንዳይገባ መታገዱን ይናገራሉ

አቡ ሃስና አሁን ጥቅም ላይ የሚገኙ ብዙ ድንኳኖች የተበላሹ በመሆናቸው ከነፋስ ወይም ከዝናብ የሚከላከሉ አለመሆናቸውን ገልጸው፥ ኤጄንሲው “UNRWA” ዕርዳታውን ወደ ሥፍራው ለማድረስ ስድስት ወራት ያህል ፈቃድ ሲጠብቅ መቆየቱን እና ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን የሚጎዳ “ወሳኝ የሰብዓዊ ሁኔታ” ቢሉትም እስራኤል ግን በቁጥር በጣም ትንሽ የዕርዳታ ቁሳቁሶችን መፍቀዷን ገልጸዋል።

ሁኔታዎች አሁንም አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሆኑ ተናግረው፥ ወደ 9,400 የሚጠጉ ህጻናት በአጣዳፊ የምግብ እጥረት፣ በጤና ሥርዓት መበላሸት እና በተበከሉ የውሃ ምንጮች እየተሰቃዩ እንደሚገኙ እና አሁን የክረምት ዝናብ እና ጎርፍ መባባሳቸውን አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደው ጦርነት “ሰው ሠራሽ ገደል” እንደፈጠረ እና መልሶ ግንባታው በአሥርት ዓመታት ውስጥ ከ70 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊያስወጣ እንደሚችል ተናግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት፥ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ሕይወትን በእጅጉ እንዳበላሹት እና በብዙ ዓይነት ድህነት ውስጥ የሚገኝ የጋዛን 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ለከባድ መከራ እንዲጋለጥ ማድረጋቸውን ተናግሯል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም የጋዛ ኤኮኖሚ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 እና 2024 ዓ. ም. በ87% መቀነሱን እና ይህም የነፍስ ወከፍ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ወደ 161 ዶላር ዝቅ እንዲል ማድረጉን እና ይህም በዓለም ላይ ካሉት ዝቅተኛ ኤኮኖሚዎቹ ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልጿል።

 

04 Dec 2025, 15:08