ኪየቭ በሚገኘው የነጻነት አደባባይ በጦርነቱ ለወደቁት የዩክሬን ወታደሮች የተደረገ ጊዜያዊ መታሰቢያ ኪየቭ በሚገኘው የነጻነት አደባባይ በጦርነቱ ለወደቁት የዩክሬን ወታደሮች የተደረገ ጊዜያዊ መታሰቢያ   (AFP or licensors)

በዩክሬን ውስጥ ለአራት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ ተነገረ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ አራተኛ ዓመቱን ቢደፍንም እስካሁን መቋጫ ያልተገኘለት ውጊያው አሁንም ድረስ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ዩክሬናውያን በውድመት፣ በፍርሃት እና በጽናት ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ በአሜሪካ አሸማጋይነት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በአቡዳቢ የተደረገው ሌላ ዙር የሰላም ንግግርም ያለ ውጤት መጠናቀቁ እና እየተደረጉ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ለውጥ እንዳላመጡ ቢታወቅም በዚህ በተያዘው አራተኛው ዓመት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁለቱ ሃገራት ወደ ሰላም ጥረቱ እንዲመለሱ ጥሪ የሚያደርጉበት ዓመት መሆኑ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእነዚህ አራት ዓመታት ባዶ የሆኑ ከተሞች፣ የተለያዩ ቤተሰቦች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት እና የተፈናቀሉበት፣ ረሃብ፣ ብርድ፣ ፍርሃት፣ ተቃውሞ እና የሃገር ፍቅር የታዩበት ዓመታት እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፥ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረችበት ቀን ጀምሮ ይህ በዩክሬን የዕለት ተዕለት ህይወት እንደሆነ እና ዬትኛውንም ዓይነት ጦርነትን መልመድ ባይቻልም ጊዜያት ግን እያለፉ እንደሆነ ተነግሯል።

ከጦርነት ጥፋት በስተቀር ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማይገኝ ቢታወቅም፥ ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ህዝቡ የሰላም እና የእድገት ህልሙ ተሟጦ እንዳላለቀ ይነገራል።

የፈራረሱ ሕንፃዎች፣ ከምድር በታች መጠለያዎች እና ምሽጎች የሚታዩባቸውን ከተሞችን ማየት የተለመደ ነገር እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ በአውሮፓ ሃገራት መካከል የነበረው የተለመደ ጦርነት በአንድ ወቅት የማይታሰብ እና የተረሳ መስሎ የነበረ ቢሆንም፥ በአሁኑ ወቅት ግን በአህጉሪቱ ፀረ-ጥቃት፣ ቅስቀሳዎች፣ ጥምረት፣ የኃይል ቀውሶች እና ግድያዎች የተለመዱ ነገሮች መሆናቸው ይገለፃል።

በአሁኑ ወቅት ስቃይ እና ሀዘን በድል እና በበቀል ስልቶችን የታገቱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከሽምግልና ሙከራዎች እና የሰላም ጉባኤዎች ይልቅ የጦር መሳሪያ ጋጋታው አከባቢውን እንደተቆጣጠረው ይገለፃል።

ባለፈው እሑድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ በድጋሚ ስለ እውነታው በግልጽ በመናገር “በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ በርካታ ቤተሰቦች መለያየታቸውን፣ በርካታ ውድመት መድረሱን እና በርካታ የማይነገር መከራ መድረሱን” ጠቁመው ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።

ለኒውክሌር የጦር መሣሪያ ያለውን እይታዎችን ከፍ ያደረገው እና በዚህም ምክንያት መላውን ዓለም ለጥፋት ሊዳርግ የሚችለው ይህ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ተፈጥሮ ካለው የአውሮፓ ውድቀት ጋር የሚያጋፍጥ መሆኑን፥ እንዲሁም ጦርነቱ ሮበርት ሹማን እና ኮንራድ አድኒዮርን ከመሳሰሉ የአንድነት መስራች ከሆኑት አባቶቻቸው ካሰቡት የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የሰብአዊነት አድማስ የራቀ እንደሆነ ተገልጿል።

በአሜሪካ አደራዳሪነት በአቡዳቢ የተካሄደው ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግርም ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፥ የድርድሩ ውጤት እና ሒደት ባይገለጽም፤ ዜሌንስኪ ጉዳዩን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በተናገሩበት ወቅት “ዩክሬን እንድትስማማ ግፊት እየተደረገባት ያለውን የግዛት ጉዳይን ጨምሮ "አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሆነው ቀርተዋል" ማለታቸው ይታወሳል።

ከሳምንታት በኋላ ሩሲያ እና ዩክሬን በጄኔቫ ያደረጉት የመጀመሪያ ቀን ድርድር ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል "ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን" የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጠቁመው የነበረ ሲሆን፥ ዊትኮፍ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁለቱንም ወገኖች ለድርድር በማቅረብ ረገድ ያገኙት ስኬት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል” ካሉ በኋላ፥ “በዚህ አስከፊ ግጭት ውስጥ የሚፈሰውን ደም ለማስቆም” የሚደረገው ጥረት ውስጥ በመሳተፋቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ጽፈዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው ከሩሲያ ጋር ሲነጻጸር አገራቸው ብዙ ነገሮችን እንድትተው እየተጠየቀች መሆኑን በማንሳት ተችተዋል።

ሩሲያ አሁን በእጇ ስር ስለሆነው እና እስከ መጨረሻው ተላልፎ እንዲሰጣት ስለጠየቀችው ከ 20 በመቶ በላይ የሚሆነው የምሥራቃዊ ዩክሬን ግዛት እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ መሬቶች እንዲሁም የተኩስ አቁምን እስካስገኘ ድረስ ይህ ጥያቄ ምክንያታዊ መሆን አለመሆኑን የተጠየቁት ዜሌንስኪ፥ ይህንን ጉዳይ የሚመለከቱት በተለየ መንገድ መሆኑን እና በቀላሉ የመሬት ጉዳይ አድርገው እንደማይመለከቱት ገልጸው፥ መሬቱን አሳልፎ መስጠት የህዝቡን አቋም እንደማዳከም፣ በዚያ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦቻቸውን እንደመካድ እንደሚቆጠር ጠቁመው፥ “አከባቢውን ለቆ መውጣት ማኅበረሰባችንን እንደሚከፋፍል እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።

በአንዳንዶች ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳየ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ትጥቅ ብቸኛው አማራጭ መንገድ እንዳልሆነ እና ይህ አካሄድ በእርግጥም በጣም አደገኛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ሰላም በጉልበት የሚገኝ ነገር ሳይሆን ሰላም የሚጠበቀው በውይይት፣ በግንኙነት፣ በመከባበር፣ በዲፕሎማሲ እና በባለብዙ ወገንተኝነት አካሄድ እንደሆነ ተነግሯል።

ፖለቲካ በተሟላ እና በትክክለኛ መልኩ ከተተገበረ በሰላም አብሮ ለመኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር፣ ሰብዓዊነትን እንደሚያስቀድም እና የጋራ ጥቅምን እንደሚያገለግል የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ ምክንያት ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚውል እና በራሱም የሃይል አካሄድን በፍጹም እንደማያበረታታ ይገለፃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ደጋግመው እንደተናገሩት የዓለምን የጦር መሳሪያዎች በአስቸኳይ ዝም ማሰኘት እና ከጦር መሳሪያ ነፃ የሆነ ሰላምን ለመገንባት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ለበርካታ ጊዜያት ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው በመጀመሪያ በራሳችን ውስጥ ያሉትን የጦር መሳሪያዎች መፍታት እንደሚገባ እንዲሁም ጥላቻን እና በሌላው ዘንድ እምነት ማጣትን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

ይህ አራተኛ ዓመት ሲታወስ ወደ ሌላ ቦታ እንዳንመለከት እና አሁን ያሉት አጠቃላይ የዩክሬን ህፃናት የሳይረን፣ የቦምብ፣ የግጭት እና የእጦት ድምጽ ብቻ እየሰሙ እንዳያድጉ ሰላምን መገንባት እንደሚገባ ጥሪ የሚደረግበት ዓመት እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ የስቃይ ጊዜያት ተስፋ አሁንም በህይወት እንደሚኖር፥ አንድነትና መረዳዳት እንዲሰፍን በየመስኩ የሚያግዙ፣ የሚያድኑ እና የሚደክሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሥራ እንደሚደግፍ የተገለጸ ሲሆን፥ ሰላም ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን ሂደት እንደሆነ፣ አንዳንዴም በፖለቲካ ድፍረት የተሞላ ፍጽምና በጎደለው ድርድር ላይ የተመሰረተ ሂደት እንደሆነም ጭምር ይገለፃል።

በአሁኑ ሰዓት ሩሲያ ሰፊውን የምሥራቅ ዶንባስ ግዛት ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ተቆጣጥራ የምትገኝ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሞስኮ ቀሪውም የግዛቱ ክፍሎች ተላልፈው እንዲሰጧት የምትፈልግ ቢሆንም ዩክሬን ግን ይህንን ሐሳብ በጽኑ እየተቃወመች ትገኛለች።

ይህ አራተኛ ዓመት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጦርነቱን “መምራት” አቁሞ ወደ ሰላም ግንባታ፣ መተማመንን፣ አብሮ መኖርን እና የጋራ ትውስታን የሚያጎለብትበት ዓመት እንዲሆን ተስፋ ሊደረግበት ይገባል ተብሏል።

25 Feb 2026, 13:05