በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ በቱርሙስ አያ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው አዲሱ የእስራኤል ሰፈራ በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ በቱርሙስ አያ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው አዲሱ የእስራኤል ሰፈራ  

የጋዛ ቀውስ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት እስራኤል ሶስት የእርዳታ ተልዕኮዎችን ማገዷን የተባበሩ መንግስታት ድርጅት ገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋዛ ውስጥ እያከናወነ ከሚገኘው የእርዳታ ሥራዎች መካከል ባለፈው ሳምንት የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የተሰማሩ ቡድኖቹ ስምንት የሰብአዊ ተልዕኮዎችን ለማስተባበር ሞክረው አምስቱ ብቻ ሙሉ ለሙሉ መመቻቸታቸውን ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በጋዛ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ቡድኖቹ ስምንት የሰብአዊ ተልዕኮዎችን ለማስተባበር ሞክረው አምስቱ ሙሉ በሙሉ እንደተመቻቹ እና በካን ዮኒስ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ ላይ ለመድረስ የተደረገውን ጥረት ጨምሮ ሦስቱ በእስራኤላውያን ባለስልጣናት መከልከላቸው ተገልጿል።

ከተሳኩ ተልዕኮዎች መካከል ከከርም ሻሎም እስከ ከሬም አቡ ሳሌም ማቋረጫ ድረስ የምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶችን መሰብሰብ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ቡድኖች በኪሱፊም እና በከረም ሻሎም የሚገኙ የእርዳታ ቀሳቁስ ማከማቻ ስፍራዎች ላይ የሰብአዊ ጭነት ሥራዎችን እንደሚቆጣጠሩ ተነግሯል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ በጋዛ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አራት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት እንደተናገሩት የሰብአዊ ድጋፎች ማሻሻያው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ህይወቶችን ማዳኑን እና ረሃብን ለማስቀረት መቻሉን ቢጠቁሙም፥ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በስፍራው የሚስተዋሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ከባድ እንደሆኑ እና በእስራኤል በኩል የሚደረጉ የመዳረሻ ገደቦች የተቋሙን የእርዳታ እንቅስቃሴዎችን እያደናቀፉ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደዘገበው 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች - በግምት በጋዛ ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ፍልስጤማውያን ሁለቱ - በግዛቱ ውስጥ በሚገኙ 1,000 የሚሆኑ የተፈናቃይ መጠሊያ ጣቢያዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በድንኳን ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኝ ያመላከተ ሲሆን፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በጦርነቱ ምክንያት በወደሙ ሕንፃዎች ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ እና ህንፃዎቹም የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ገልጿል።

የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በጥር ወር ብቻ ከ85,000 በላይ ለሚሆኑ ቤተሰቦች ድንኳን፣ የዝናብ ልብሶችን፣ ፍራሾችን፣ የተለያዩ አልባሳትን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማከፋፈላቸውን እንደቀጠሉ ይፋ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ ክልል ውስጥ፣ አንድ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለስልጣን እስራኤል ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ እየፈጸመች ያለውን የአስተዳደር ቁጥጥር መስፋፋትን ያወገዙ ሲሆን፥ ይህ አካሄድ ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያደናቅፍ ገልጸዋል።

የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ በአሜሪካ አሸማጋይነት ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የተፈረመውን የኦስሎ ስምምነቶችን በመቀየር በክልሉ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲተገበር የቆየው የስልጣን ክፍፍል ላይ የተደረጉ ዋና ዋና ለውጦችን ባለፈው ሳምንት ማጽደቁ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ የእስራኤል መንግስት እርምጃ ሃገሪቷ በወታደራዊ ወረራ የያዘችውን ስልጣን በማራዘም በፍልስጤም በሚተዳደሩ ዞኖች ውስጥ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ጨምሮ ቀደም ሲል በፍልስጤም ተቋማት የሚተዳደሩ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ካቢኔው እስራኤል “የቅርስ ስፍራዎች” በማለት የገለፀቻቸውን ቦታዎች ‘የውሃ፣ የአካባቢ እና የአርኪኦሎጂ ሀብቶችን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን’ በመጥቀስ ሰፊ ስልጣንን ለእስራኤል መስጠቱ ተነግሯል።

የሄብሮን ከተማ ተጠባባቂ ከንቲባ የሆኑት አስማ አል ሻራባቲ ለብሪታኒያ ሬዲዮ እንደተናገሩት አዲሱ ማዕቀፍ ለስም በፍልስጤማዊያን ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች እንኳን ፍልስጤማዊያን ባለስልጣናትን ከእቅድ እና ከልማት ውሳኔዎች እንደሚያገል ገልጸዋል።

17 Feb 2026, 15:47