የካሜሩናዊያን እና የቫቲካን ባንዲራዎች በያውንዴ ከተማ አደባባዮች ላይ ሲውለበለቡ የካሜሩናዊያን እና የቫቲካን ባንዲራዎች በያውንዴ ከተማ አደባባዮች ላይ ሲውለበለቡ  

ካሜሩናዊያን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት ለተከፋፈለው ሀገር 'ፈውስን እንደሚያመጣ' ያላቸውን ተስፋ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአራት የአፍሪካ ሃገራት እያደረጉት በሚገኘው ሃዋሪያዊ ጉብኝት ሁለተኛ መዳረሻ ሃገር የሆነችው አንዳንድ የካሜሩን ዜጎች ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት የብፁዕነታቸው ጉብኝት የተለያዩ ቡድኖች ‘አብረው እንዲኖሩ፣ እንዲተባበሩ እና እርስ በርስ እንዲስማሙ’ ሊያበረታታ ይችላል ማለታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የካሜሩን ከተማ በሆነችው ማዕከላዊ ያውንዴ በሚገኘው የንጉል ዛምባ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚኖሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ህፃናት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማዕከሉን እንደሚጎበኙ መስማታቸውን ተከትሎ ጊቢውን የማጽዳት ሥራ ላይ ተጠምደው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፥ ህፃናቱ እያጸዱት በነበረው የማዕከሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ምስል የያዙ ባነሮች መለጠፋቸው እና ብፁዕነታቸው ካሜሩን ከደረሱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የወላጅ አልባ ህፃናት ማዕከሉን እንደሚጎበኙ ተነግሮ እንደነበርም ተገልጿል።

በወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚኖሩት እና የማዕከሉ ትምህርት ቤት ውስጥ ዋና መምህር ሆነው የሚያገለግሉት እህት ክሪስታቤል በማዕከሉ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ህፃናት ከአስቸጋሪ የህይወት ጎዳና የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት “ታላቅ ደስታን” እንደሚፈጥር የገለጹ ሲሆን፥ ልጆቹ የሚወዳቸው ሰው መኖሩን እና በቤተክርስቲያን መሪዎችም ዘንድ ሳይቀር እንደሚታሰቡ ይሰማቸዋል ብለዋል።

የሰላም መልዕክት
የወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ ሠራተኞች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ ጉብኝት ትልቅ መጽናኛ እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰው ግጭት ሀገሪቱ አሁንም እየተናጠች መሆኑ ተነግሯል።

በአካባቢው የሚገኝ ንጓ ኮሊን ሱህ የተባለ ካቶሊካዊ ጋዜጠኛ እንደተናገረው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰላም መልዕክት ብዙ ፈውስ እንደሚያመጣ ያለውን እምነት ገልፆ፥ ብፁዕነታቸው ገለልተኛ ሰው እንደሆኑ እና ከፖለቲካ ይልቅ መንፈሳዊ መሪ እንደሆኑ፥ እንዲሁም በካሜሩን በሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ለማየት የሚጠብቀው ይሄንን እንደሆነ አስረድቷል።

ይህች አገር ለአሥር ዓመታት ያህል በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል በሚፈጠር ግጭት ስትሰቃይ የነበረች ሃገር መሆኗ የሚነገር ሲሆን፥ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ እና ደቡባዊ ምዕራብ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ‘አንግሎፎን’ ተብለው የሚጠሩት አብዛኛዎቹ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ‘ፍራንኮፎን’ ተብለው በሚጠሩት ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መገለል እንደሚደርስባቸው የሚሰማቸው ሲሆን፥ አንዳንዶች የተለየ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ብቻ የሚኖሩበት ግዛት ለመመስረት ሲሉ የትጥቅ ትግል መጀመራቸውም ይነገራል።

አቶ ሱህ ይሄንን አስመልክቶ እንደተናገረው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጉብኝታቸው ወቅት የሁለቱንም ህዝቦች ተወካዮች እንደሚያናግሩ ያለውን እምነት ገልፆ፥ “ሁሉም ሰው” በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሃዋሪያዊ ጉብኝት በጣም መደሰታቸውን የጠቀሰ ሲሆን፥ ፍራንኮፎኖች፣ አንግሎፎኖች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮች እና ሙስሊሞች በሙሉ የሮማው ጳጳስ ጉብኝት እነዚህ ህዝቦች በሰላም “አብረው እንዲኖሩ፣ እንዲተባበሩ እና እንዲስማሙ” ሊያበረታታቸው እንደሚችል ያለውን ተስፋ ገልጿል።

ችላ የተባለ መከራ
በሰሜናዊ የካሜሩን ክፍል በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩት እህት ክላውዲን ቦሎም በያኔዴ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት ላይ ለመገኘት አጭር የእረፍት ጊዜ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፥ “ከምርጫው በኋላ በአከባቢያቸው ያለው የፖለቲካ ሁኔታ አስከፊ” እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በርካታ ሰዎች ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ እና በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መቀጠል ከባድ መሆኑን አስረድተዋል።

“አብዛኛውን ጊዜ ካሜሩናዊያን እንደተረሱ ይሰማቸዋል” ያሉት እህት ክላውዲን፥ ችግሮቻቸው ለተቀረው ዓለም ምንም እንዳልሆኑ አድርገው እንደሚያስቡ፥ ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደሚመጡ በሰሙ ጊዜ በደስታ መሞላታቸውን እና ይህ ደግሞ እኛም ሰዎች መሆናችንን የሚያስታውሰን ነገር ነው ብለዋል።

17 Apr 2026, 14:00