ከስደተኞች ካምፕ እስከ ታላቁ የዓለም ቴኳንዶ ውድድር የበቃ የዮርዳኖስ ታዳጊዎች ቡድን
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከግንቦት 27 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ሮም የጎረጎሳዊያኑን የ 2026 ዓ.ም. ታላቁን የዓለም ቴኳንዶ ሻምፒዮን የምታስተናግድ ሲሆን፥ በዚህ ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ስፖርተኞች መካከል በዮርዳኖስ በሚገኘው እና በአሁኑ ወቅት 60,000 የሚጠጉ ሰዎችን አስጠልሎ በሚገኘው የአዝራቅ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ስምንት የ10 አመት እድሜ ያላቸው ታዳጊ አትሌቶች እንደሚገኙበት ተገልጿል።
እነዚህ ታዳጊዎች በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በጣሊያን ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ድጋፍ እና በቴኳንዶ ለሰብዓዊነት ፋውንዴሽን ተነሳሽነት ከስደተኞች ካምፕ የመውጣት እድል እንዳገኙ እና ይህ የታዳጊዎች ቡድን በ 2026 ታላቁ የዓለም ቴኳንዶ ውድድር አካል በሆነው እና ታዳጊዎቹን ለሻምፕዮንነት ለሚያቀርበው የ‹ኪም እና ሊዩ› ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ እ.አ.አ. በ 2028 በሎስ አንጀለስ በሚዘጋጀው የበጋ ኦሎምፒክ ላይ እንዲሳተፉ ያስችላቸዋል ተብሏል።
የታዳጊ አትሌቶቹ ቡድን በሮም በሚኖራቸው ቆይታ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር እንደሚገናኙ፣ እንዲሁም የከተማዋን ባህላዊ እና ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት እድል እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
የቴኳንዶ ለሰብዓዊነት ፋውንዴሽን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን በቴኳንዶ እና በሌሎች የትምህርት መሳሪያዎች በኩል ለመርዳት የቅድስት መንበር ኦፊሴላዊ የስፖርት ድርጅት እና ማኅበር አንዱ አካል የሆነው ‘አትሌቲካ ቫቲካና’ አባል የሆነበት ከዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን፥ በዚህም ተነሳሽነት ማብቃትን፣ ሰላምን፣ ዘላቂ እድገትን እና የኦሎምፒክ እሴቶችን እንደሚያበረታቱ ተነግሯል።
የኦሎምፒክ እሴቶች ተጨባጭ መገለጫ
የጣሊያን ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት አንጀሎ ቺቶ የታዳጊዎቹ ተሳትፎ ፈጣን እና ጥልቅ ስሜትን መቀስቀሱን ጠቁመው፥ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ከተነገራቸው ጊዜ ጀምሮ ያለማመን እና የጉጉት ስሜት ውስጥ መግባታቸውን እንዲሁም በየዕለቱ የመሄጃቸውን ቀን በተስፋ የመጠበቅ ብርቱ ፍላጎት ውስጥ መግባታቸውን ለጣሊያኑ ጋዜጣ ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ገልጸዋል።
“እነዚህ ተነሳሽነቶች በተጨባጭ ድርጊቶች እና እውነተኛ ልምምድ እንጂ ብቻውን ሊገለጽ በማይችለው የኦሎምፒክ እሴቶች ተጨባጭ መገለጫን የሚወክሉ ናቸው” ያሉት ፕረዚዳንቱ፥ ይህም ማለት በትጋት መስራት፣ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በቀጥታ መሳተፍ በተለይም በጦርነት እና በመድልዎ በጣም የተጎዱትን ህፃናት በመርዳት እና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል አስተዋፅዖ ማድረግ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚህ ዓመት 10ኛ የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የቴኳንዶ ለሰብዓዊነት ፋውንዴሽን ፕሮጀክት በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ ተስፋ መስጠቱን አቶ አንጀሎ አስረድተው፥ ከዮርዳኖስ ሌላ ፋውንዴሽኑ በሩዋንዳ እና በቱርክ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ገልጸዋል።
አቶ አንጀሎ በማከልም በዮርዳኖስ ያሉ የመስክ ተሞክሮዎች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች የሚያውቁ፥ ነገር ግን ስፖርትን በማጥናትና በመለማመድ የተሻለ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት የሚተጉ ታዳጊ ወንዶች እና ልጃገረዶች ያላቸውን ልዩ ቁርጠኝነት ይመሰክራሉ ብለዋል።
ኢፍትሃዊነት እያደገ በመጣበት እና የማያቋርጥ ግጭት በሚታየበት በአሁኑ ዘመን ስፖርቶች አሁንም የግንኙነት እና የማብቃት ቦታ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ የገለጹት የጣሊያን ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አንጀሎ ቺቶ በመጨረሻም፥ ‘ቴኳንዶ ከሥነ ምግባር እና ከእሴቶቹ ጋር ዛሬ ግልጽ የሆነ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ’ ጠቁመው፥ እውነተኛ ስኬት በመድረኩ ላይ መቆም ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ቢሆን ይህንን እንዲያደርግ እድል እንደሚሰጥ በመግለጽ አጠቃለዋል።