በሳውዲ አረቢያ 200 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ባለፈው ሳምንት አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው የድረገጽ ጋዜጣ የትግራይ ክልል ወጣቶች ጽህፈት ቤትን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው በሳውዲ አረቢያ ታስረው የሚገኙ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የግድያ ስጋት እንደተጋረጠባቸው ጠቅሶ፥ ወጣቶቹ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ያለምንም የሕግ ተከላካይ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ በሳውዲ አረቢያ ደቡባዊ ክፍል፣ አሲር ክልል አብሃ አካባቢ በሚገኘው "ከሚስ ሙሻይት" እስር ቤት እንደሚገኙ እና የታሰሩትም ከዕፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል ተከሰው መሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በሳዑዲ አረቢያ ቢያንስ 65 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዘ ክስ የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሂውማን ራይትስ ዎች ያስታወቀ ሲሆን፥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ሦስት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቀጣታቸውን ገልጾ የሌሎቹ ፍርድ ተፈጻሚነት ግን እንዲዘገይ መደረጉን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሚያዚያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በሳዑዲ አረቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ላይ የሞት ቅጣት መፈጸሙን አስታውቋል።
ከትግራይ ጦርነት የሚሸሹ ኢትዮጵያውያን
ሂዩማን ራይትስ ዋች እንደዘገበው እ.አ.አ. ከ 2020 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ወይም በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት በርካታ የአከባቢው ወጣቶች እንደተሰደዱ ጠቅሶ፥ በጅቡቲ እና በየመን አቋርጠው ወደ መዳረሻቸው ሳይደርሱ እና በ2023 እና 2024 መካከል በሳውዲ ፖሊሶች ሲሰሩ በነበሩበት የአብሃ ክልል ተይዘው ከመታሰራቸው በፊት ወጣቶቹ በታዋቂው እና በአደገኛው “የምስራቃዊ መንገድ” በኩል መሻገራቸውን ገልጿል።
ስደተኞቹ በጉዟቸው ላይ ገንዘብ ለማግኘት እና ሕይወታቸውን ለማቆየት በማሰብ በሳውዲ አረቢያ ህግ ክልክል የሆነውን ጫት ይዘው መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ጫት በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ውስጥ በብዛት የሚገኝ እና ቅጠሉ ሲታኘክ ከአምፌታሚን ጋር ተመሳሳይ የሆነ የአነቃቂነት ባህሪ ያለው የእጽዋት ዓይነት እንደሆነ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ሃገረ ስብከት ጥሪ
ይህ በእንዲህ እያለ የአዲግራት ካቶሊካዊት ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ መድህን፣ በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ 200 ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ህይወት ለመታደግ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል።
በአፍሪካ የካቶሊክ ዜና አገልግሎት በተዘገበው መሰረት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ ባስተላለፉት የድረሱልን መልዕክት የድሆች እና የተገለሉ ወገኖች ጩኸት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጆሮ ሊያገኝ እንደሚገባ ገልጸው፥ የዚህን ያህል በርካታ የሰው ህይወት በሞት እና በሽረት መሃል ተንጠልጥሎ እያለ ዝም ማለት ፈጽሞ እንደማይችሉ በመጥቀስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
ጳጳሱ አክለውም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ከሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር አስቸኳይ የዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ ሰብዓዊ ክብርን ከሚያዋርደው እና ህይወትን ከሚያጠፋው የካፒታል ቅጣት (የሞት ፍርድ) ይልቅ፣ ወጣቶቹ ስህተታቸውን አርመው እና ታንጸው ወደ ማህበረሰቡ ሊቀላቀሉ የሚችሉበት ሌላ አማራጭ የቅጣት እርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀው ተማጽነዋል።
“የአዲግራት ካቶሊካዊት ሃገረ ስብከት እረኛ እንደመሆኔ መጠን እንደ ሀይማኖት መሪ ብቻ ሳይሆን በልዑል አምላክ ምስል እና አምሳል የተፈጠረውን የእያንዳንዱ የሰው ነፍስ ጥልቅ ዋጋ ምስክር ሆኜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ለማሰማት እገደዳለሁ” ያሉት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ፥ “ሕይወት ከፈጣሪ የተሰጠች፣ የተቀደሰች፣ የማትደፈር እና ከተፀነሰችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተፈጥሮአዊ ፍጻሜዋ ድረስ ጥበቃ ሊደረግላት እንደሚገባ እምነታችን ስለሚያስተምረን ነው” ብለዋል።
ፍትሕ በምሕረት ይደገፋል
ብፁዕ አቡነ ተስፋ ስላሴ የህዝቦችን ሉዓላዊነት እና የሕግ የበላይነትን የማስከበር አስፈላጊነትን እንደሚያከብሩ ጠቅሰው፥ “ፍትሕ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው በምሕረት ሲደገፍ ነው” ሲሉ በአጽንዖት የገለጹ ሲሆን፥ “በእነዚህ 200 ሰዎች ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ሊጠገን የማይችል የሰው ህይወት መጥፋት እና በኢትዮጵያ ውስጥ በቀሩት ቤተሰቦች ላይ እጅግ አሳዛኝ መከራን የሚያደርስ መሆኑን አመላክተዋል።
ከሳውዲ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረግ
ጳጳሱ አክለውም የሞት ፍርዱ እንዲቀር እና ቅጣቱ እንዲቀንስ ለማድረግ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በአስቸኳይ ከፍተኛ ደረጃ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነት ያለባቸውን ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን አጥብቀው እንደሚጠይቁ ገልጸው፥ በመጨረሻም “ከሞት ቅጣት ይልቅ ለማገገም፣ ንስሃ ለመግባት እና የመቤዠት እድልን የሚሰጡ ሌሎች አማራጮችን ማበረታታት” አስፈላጊ መሆኑን አበክረው አሳስበዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ‘የሞት ቅጣት ተቀባይነት የለውም’ ማለታቸው
ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በዩናይትድ ስቴትስ ኢሊኖይ ግዛት ውስጥ የሞት ቅጣት የተሰረዘበት 15ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቺካጎ ለሚገኘው ለዴፖል ዩኒቨርሲቲ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት የሞት ቅጣትን አስመልክቶ የቤተክርስቲያንን አቋም ሲገልጹ “የሞት ቅጣት ሳይደርስባቸው የጋራ ጥቅምን መጠበቅ እና የፍትህ መስፈርቶችን ማሟላት ይቻላል” ማለታቸው ይታወሳል።
ከዚህም ባለፈ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “አንድ ሰው ከተፀነሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ ለእያንዳንዱ የሰው ሕይወት ቅድስና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ያለማቋረጥ ስታስተምር እንደኖረች ይታወቃል።