ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የእግዚአብሔር ስጦታዎችን የበለጠ ፍትሃዊ ዓለምን ለመፍጠር እንጠቀም” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ መስከረም 11/2018 ዓ. ም. ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድርሰዋል። ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ቀደም ብሎ ከሉቃ. 16:1 - 13 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለምዕመናኑ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች የበለጠ ፍትሃዊ እና ትክክለኛ ዓለምን ለመፍጠር እንጠቀም” ሲሉ አሳስበዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ ያደረጉት አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ መልካም ሰንበት እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ! ከሉቃ. 16: 1-13 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው ወንጌል ላይ የተጠቀሰው ምሳሌ በቁሳዊ ነገሮች አጠቃቀም ላይ እና ከምንም በላይ ውድ የሆነውን ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን እንድናሰላስል የሚደርገን ነው።

በምሳሌው ውስጥ አንድ ባለ ሃብት ለአስተዳደሩ ገንዘብ ያዥ የሚሆን ሰው ይፈልግ እንደ ነበር አይተናል። በዚህ ምሳሌ ውስጥ ጠቃሚ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል ቀርቦልናል። እኛ የሕይወታችን ወይም የንብረቶቻችን ጌቶች አይደለንም። ያለን ሁሉ ለራሳችን ጥቅም፣ ለነፃነታችን እና ለኃላፊነታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን ስጦታ ነው። ራሳችንን፣ ንብረቶችን እና የምድርን ሃብቶችን እንዴት አድርገን እንዳስተዳደርን በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች ፊት፣ በኅብረተሰብ እና በተለይም ከእኛ በኋላ በሚመጡት ሰዎች ፊት የምንጠየቅበት ቀን ይመጣል።


በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ገንዘብ ያዥ የራሱን ትርፍ ብቻ ይፈልግ ነበር። የሰበሰበውን የገንዘብ መጠን የሚያሳውቅበት ቀን ሲደርስ እና የሥራ ቦታው ሲወሰድበት የወደፊት ሕይወቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ ይኖርበታል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ መካከል የቁሳቁስ ዕቃዎችን ማከማቸት ዋጋ እንደሌለው ይገነዘባል። ምክንያቱም የዚህ ዓለም ብልጽግና የሚያልፍ ነው። ይህ ገንዘብ ያዥ በበኩሉ አንድ ድንቅ ሃሳብ አሰበ። ተበዳሪዎችን ጠርቶ ወደ እርሱ የሚገባውን ገንዘብ መጠን ትቶ ተበዳሪዎቹ ያለባቸው ዕዳ ምን ያህል እንደሆነ መቁጠር ጀመረ። በዚህ መንገድ ቁሳዊ ሃብትን ቢያጣ ነገር ግን እሱን ለመርዳት እና ለመደገፍ ዝግጁ የሆኑ ጓደኞችን ያገኛል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የምሳሌውን ፍንጭ በመውሰድ ‘የዓመጻ ገንዘብ ሲያልቅ በዘለዓለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ አማካይነት ወዳጆችን ለራሳችሁ አብጁ’ በማለት አጥብቆ ይመክረናል (ሉቃ. 16: 9)።

በእርግጥ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የገንዘብ ተቆጣጥሪ ሐቀኝነት የጎደለውን የዚህን ዓለም ሃብት እያስተዳደረ ቢሆንም ራስ ወዳድነቱን ትቶ ጓደኞችን ማፍራት ችሏል። እኛ በወንጌል ብርሃን የምንመራ ደቀ መዛሙርት ለዚህ ዓለም እና ለራሳችን ሕይወት እውነተኛ ሃብት የሆነውን፥ ከእግዚአብሔር፣ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት እንዴት ልንጠቀምበት ይገባናል።

ውድ ወዳጆቼ፥ ምሳሌው እኛ ራሳችንን እንድንጠይቅ ይጋብዘናል። እግዚአብሔር በአደራ የሰጠንን ንብረቶችን፣ የምድርን ሃብቶች እና ሕይወታችንን እንዴት እያስተዳደርን እንገኛለን? የራስ ወዳድነት መንገድ መከተል፣ ከምንም በላይ ሃብትን ማስቀደም እና ስለራሳችን ብቻ ማሰብ እንችላለን።

ራስ ወዳድነት እኛን ከሌሎች በማግለል በመካከላችን የውድድር መርዝን ያሰራጫል። ይህም ብዙ ጊዜ ግጭት እና ጦርነት እንዲፈጠር ያደርጋል። ይልቁንም ያለን በሙሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ አድርገን ልንወስድ ይገባል። ያለንን ሃብት እንደ ደግነት መሣሪያ አድርገን በመጠቀም፥ በመካከላችን የወዳጅነት እና የአብሮነት መረቦችን ለመፍጠር፣ ለጋራ ጥቅም የምንሠራበት እና የበለጠ ፍትሃዊ፣ ትክክለኛ እና ወንድማማችነት የሰፈነበት ዓለምን መገንባት እንችላለን።

ቸር እግዚአብሔር በስጦታነት የሰጠንን ሃብት ፍትሃዊ፣ ኃላፊነት ባለበት እና መልካም በሆነ መንገድ ማስተዳደር የምንችልበትን የጥበብ ጸጋ ማግኝት እንድንችል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በጸሎት እንጠይቅ።”

22 Sep 2025, 17:17