ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “በዓመፅ፣ በግዳጅ ስደት እና በበቀል የሚመሠረት ሕይወት የለም” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው የጋዛን ሕዝብ ለመርዳት ቆርጠው ከተነሱት ሰዎች እና በመላው ቅድስት አገር ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ መሪዎች ጋር በመሆን፥ “በዓመፅ፣ በግዳጅ ስደት እና በበቀል የሚመሠረት ሕይወት የለም” ሲሉ በድጋሚ አሳስበዋል።
“ሰዎች ሰላም ያስፈልጋቸዋል!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ አክለውም “ስቃይ ውስጥ የሚገኙ የጋዛ ነዋሪዎችን ከልብ የሚወዱ በሙሉ ለሰላም ይሠራሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥር አራተኛ ይህን አስተያየታቸውን የሰጡት፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሑድ መስከረም 12/2018 ዓ. ም. ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ሲሆን፥ ለጋዛ ሰርጥ ሕዝብ አጋርነታቸውን ለሚገልጹ የተለያዩ ካቶሊካዊ ማኅበራት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበዋል።
“ውድ ወዳጆቼ ሆይ! በዚያች በተሰቃየች ምድር ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አጋርነታቸውን የሚገልጹትን እና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ያሉ የሌሎች ብዙ ሰዎች ተነሳሽነትን አደንቃለሁ” ብለዋል።
የእስራኤል በጋዛ ከተማ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ቀጥሏል
የጋዛ የጤና ባለሥልጣናት በመግለጫቸው፥ የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ እና በግዛቱ በሙሉ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ዓ. ም. ቢያንስ 60 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል። የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት በጋዛ ከተማ በጀመረው የመጨረሻ ጥቃት፥ ረጃጅም ሕንጻዎችን እና ከመሬት በታች ያሉ ጉድጓዶችን እያወደመ እንደሚገኝ ታውቋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፥ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ከተማ ማዕከላዊ እና ምዕራባዊ ክፍል ተጨማሪ ቦታዎችን ለመያዝ በሚል ተስፋ ምሥራቃዊ የከተማ ዳርቻዎችን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
የእስራኤል መንግሥት፥ ከወሩ መጀመሪያ አንስቶ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ጋዛን ለቀው መውጣታቸውን ሲናገር ነገር ግን ጋዛን የሚቆጣጠረው የሃማስ ታጣቂ ቡድን፥ 300,000 የሚሆኑ ነዋሪዎች ብቻ መሰደዳቸውን አስታውቆ፥ በሃማስ ወይም በሌሎች የፍልስጤም ቡድኖች ተይዘው የሚገኙ ቁጥራቸው ከሃምሳ የማይበልጡ የእስራኤል ታጋቾችን ጨምሮ ከ900,000 በላይ የሚሆኑት አሁንም ጋዛ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።
ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤል በጋዛ ላይ ወረራ ከጀመረች በኋላ ከ65,000 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ ሲነገር፥ ሃማስ በደቡብ እስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት 1200 የሚጠጉ ሲቪሎች ሲሞቱ ወደ 250 የሚጠጉ ንፁሃን ዜጎች እና ወታደሮች መታገታቸው ይነገራል።
የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ ክብር ሊጠበቅ እና ሊከበር ይገባል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለሰላም በሚያቀርቡት ጥሪ ላይ ያላቸውን ወጥ አቋም አሳይተዋል። እሑድ መስከረም 4/2018 ዓ. ም. የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት፥ ከገዛ መሬታቸው በግዳጅ እንዲሰደዱ ተደርገው ተቀባይነት በሌለው ሁኔታ ጋዛ ውስጥ በፍርሃት ለሚኖር የፍልስጤም ሕዝብ ያላቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ “አትግደል” ብሎ ወዳዘዘው እና ሁሉን ቻይ ወደሆነው እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታቸውን በማቅረብ የሰው ልጆች በሙሉ ይህን ትዕዛዝ በተግባር እንዲመሰክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
“የተኩስ አቁም ስምምነት አንዲደረግ፣ ታጋቾች እንዲፈቱ፣ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ በድርድር እንዲገኝ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ያቀረቡትን ጥሪ በማደስ፥ “የሰላም እና የፍትህ ጎህ እንዲቀድ” ሁሉም ሰው በጸሎቱ እንዲጸና አደራ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ከጣሊያን ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት ነጋዲያን ሰላምታቸውን አቅርበው፥ እንዲሁም ካኬፕ ቨርዴ፣ ከአንጎላ፣ ከፖላንድ፣ ከስፔን፣ ከፖርቱጋል እና ከታንዛኒያ ለመጡ ነጋዲያንም ሰላምታቸውን አቅርበዋል።
በሮም ትምህርታቸውን ለሚጀምሩ የኢየሱሳውያን ማኅበር ካህናት እና ለቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል ማኅበር ካኅናትም ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በጣሊያ ከቬሮና ከተማ ለመጡት መዘምራን ሌሎች መዘምራንም አቀባበል በማድረግ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአልዛይመርስ በሽታ የሚሰቃዩን ሰዎችን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙትን ምዕመናን እና እንግዶችን በሙሉ በማመስገን ለሁሉም የተባረከ ዕለተ ሰንበትን ተመኝተውላቸዋል።
