ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሊባኖስ ወጣቶች ጋር በብከርኬ አደባባ ሲገናኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሊባኖስ ወጣቶች ጋር በብከርኬ አደባባ ሲገናኙ  (@Vatican Media)

የሊባኖስ ወጣቶች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉብኝት በሊባኖስ ሰላምን የሚያመጣ እንደ ሆነ ገለጹ

የሊባኖስ ወጣቶች በብከርኬ በሚገኘው የማሮናውያን አንጾኪያ ፓትሪያርካዊ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ላይ ኅዳር 22/2018 ዓ. ም. ተገናኝተው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር የነበራቸውን ጊዜ በማስመልከት አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶቹ ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ በርካታ ቀውሶች ባጋጠማት ሊባኖስ ውስጥ እንደ ወጣት ሰው ሕይወት ምን እንደሚመስል አብራርተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአገራችን ውስጥ ችግሮች ካጋጠሙን በኋላ አዲስ ዓይነት ሰላም እና ደስታ ሊሰጡን እንዲሁም እንደ ታላቅ ወንድም ታናሽ ወንድሙን ሊጎበኘው እንደመጣ በመካከላችን ተገኝተዋል” ብለዋል።

የ24 ዓመቱ ራልፍ ሳርኪስ ሰኞ ኅዳር 22/2018 ዓ. ም. በቤሩት አቅራቢያ በሚገኘው የማሮናውያን አንጾኪያ ፓትሪያርካዊ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከ15,000 ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው በዚህ መንገድ ገልጿል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ለመገናኘት ወደ ቤሩት ከመጡ የሊባኖስ ወጣቶች መካከል ጥቂቶች
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ለመገናኘት ወደ ቤሩት ከመጡ የሊባኖስ ወጣቶች መካከል ጥቂቶች

አደባባዩ እና በዙሪያው ያሉት ቦታዎች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ እና የሊባኖስን እና የቅድስት መንበርን ባንዲራዎች በማውለበለብ በደስታ በተሞሉ ወጣቶች ተሞልተው እንደ ነበር ተመልክቷል።

ከመላው ሊባኖስ የመጡ ወጣቶች፥ በተለይም ባለፉት አሥርት ዓመታት የሴዳር ምድር ያጋጠሟትን የተለያዩ ጉዳዮች በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አበረታች ቃላትን እስኪነግሯቸው ድረስ እየጨፈሩ እና እያጨበጨቡ ይጠብቁ እንደ ነበር ተመልክቷል።


እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2019 ዓ. ም. ካጋጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ ጀምሮ እስከ 2020 የቤሩት ወደብ ፍንዳታ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የተለያዩ ግጭቶች ድረስ የሊባኖስ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለመገንባት ተቸግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ወጣቶች እነዚህን ችግሮች በግልጽ ተመልክተው ዛሬ በሊባኖስ ወጣት መሆን ከባድ እንደሆነ በአንድ ድምፅ ተናግረዋል። ሆኖም የተረጋጋች ሊባኖስን ለመገንባት ባላቸው ፍላጎት እና የተሻለ የወደፊት ሕይወት ላይ የማይናወጥ አቋም እንዳላቸው፣ ብዙዎችም ተስፋን እና ጥንካሬን ለማግኘት ወደ እምነታቸው እንደሚሳቡ ታውቋል።

የወደፊት ሕይወትን መገንባት አለመቻል

“ዋና ዋና ችግሮች የጀመሩት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2020 ዓ. ም. የተከሰተው የቤሩት ፍንዳታ እንደ ነበር የገለጸው ራልፍ ሳርኪስ፥ በዚህ አደጋ ብዙ ጓደኞቹን እንዳጣ፣ ብዙዎችም አገሪቱን ለቀው መውጣታቸውን እና ከነዚህ መካከል አንዱ ወንድሙ እንደ ሆነ ተናግሯል።

እርሱም አገሪቱን ለቅቆ መሄድ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት ጥርጣሬ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም በመጨረሻ ለመቆየት መወሰኑን አስረድቷል። “የኢየሱስ ክርስቶስ እቅድ እኔ በሊባኖስ እንድቆይ እንደሆነ አምናለሁ” ያለው ራልፍ ሳርኪስ፥ ጌታ እዚህ እንድቆይ እና የራሴን ተልዕኮ እንድፈጽም እየመከረኝ እንደሆነ ይሰማኛል” ሲል ተናግሯል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ለመገናኘት ወደ ቤሩት ከመጡት ወጣቶች መካከል በከፊል
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ለመገናኘት ወደ ቤሩት ከመጡት ወጣቶች መካከል በከፊል   (@Vatican Media)

“በዚህ ዕድሜ ሌሎች ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት ለማስተካከል እየሠሩ ይገኛሉ” ያለችው የ24 ዓመቷ ጃኒስ ጎሱብ፥ ነገር ግን ይህ አስቸጋሪ እንደሆነ ምክንያቱም እቅድ ባወጡ ቁጥር በአገሪቱ ውስጥ ዘወትር አንድ ችግር የሚከሰት በመሆኑ የወደ ፊት ሕይወት መገንባት እጅግ ከባድ እንደሆነ አጋርታለች

እንደ ራልፍ እራሷን በሌላ ቦታ ማግኘት የማትፈልገው የ24 ዓመቷ ወጣት ጃኒስ ጎሱብ፥ ሊባኖስን እንደምትወድ፣ የሕዝቦቿን ማኅበራዊ ሕይወት እንደምትወድ፣ ቤተሰቧን እና ጓደኞቿን እንደምተወዳቸው ገልጻ፥ በአገሯ እንድትቆይ የሚያደርጋት ይህ እንደሆነ አስረድታለች።

ከእምነት ጥንካሬ ማግኘት

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ችግሮች ለመቋቋም የሚያግዛቸው እምነታቸው እንደሆነ ታውቋል። በተጨማሪም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ይህንን የሚያጠናክር መሆኑ ተነግሯል።

“እኛ እንደ ሊባኖስ ክርስቲያኖች ያስፈልጋል” ሲል ያስረዳው ወጣት ራልፍ፥ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ እኛን ሲጎበኘን ማየት አስፈላጊ ነው” ብሎ፥ “በሊባኖስ እና በመላው ዓለም ያሉ ወጣቶች በሙሉ ጌታን በእውነት እንዲፈልጉ እና የሚያስፈልገን ብቸኛው ተስፋ እርሱ ነው” ሲል አስረድቷል።

ሊባኖሳዊው ወጣት ራልፍ ሳርኪስ
ሊባኖሳዊው ወጣት ራልፍ ሳርኪስ

“በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ብዙ ወጣቶቻችን እምነታቸውን እያጡ እንደሆነ፣ ነገር ግን እኛ ሊባኖሳውያን ነን፣ ክርስቲያኖች ነን፣ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ ከእርሱ ጋር የማይቻል ነገር የለም” ሲል ተናግሯል። ስብሰባውን ለማዘጋጀት የበኩሉን ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው የሊባኖስ ስካውት አባል ወጣት ራልፍ በተጨማሪም “በሊባኖስ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ ሰላም እንደሚያስፈልጋቸው እና “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህንን ሰላም ሊያስተምሩን የመጡ መሆናቸውን ገልጾ፥ “እኛም የሰላም ዋና ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” ሲል ተናግሯል።

ሊባሶናዊት ወጣት ማሪ-ላይን ኤል ሃይክ
ሊባሶናዊት ወጣት ማሪ-ላይን ኤል ሃይክ

የ25 ዓመቷ ወጣት ማሪ-ላይን ኤል ሃይክ ተስፋ ከእምነት እንደሚገኝ አፅንዖት በመስጠት፥ “በሊባኖስ ወጣት መሆን ከባድ ቢሆንም ወጣቶች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ ስንሰበሰብ ዘወትር ደስ ይለኛል” በማለት አስረድታለች። ሊባኖስ ታላቅ አገር ብትሆንም በሊባኖስ ሕይወት ከባድ እንደሆነ እና በሊባኖስ ጸንቶ ለመኖር ጠንካራ እምነት የያስፈልግ ምሆኑን በማስረዳት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝትም ሁልጊዜ ጠንካራ እምነት ሊኖረን እንደሚገባ የሚያሳይ እና የተሻሉ ቀናት እየመጡ መሆናቸውን የሚገልጽ እንደሆነ ተናግራለች።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አርተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ብዙ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ወጣት ጃኒስ አፅንዖት ሰጥታ፥ “ሁሉም ሰው አንድ ሆኖ ማየት ደስ ይላል” ብላ፥ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊሞችም ጭምር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝትን በደስታ እና በአክብሮት መቀበላቸውን ገልጻ፥ “ይህም ሁላችንም አብረን የመኖር ተስፋን ይሰጠናል” በማለት ተናግራለች።

 

03 Dec 2025, 16:53