ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ “ወጣቶች ለማለም፣ ለማቀድ እና መልካምን ለማድረግ ጊዜው አልመሸም” ሲሉ ተናገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሊባኖስ የመጀመሪያ ሙሉ ቀን ጉብኝታቸው በብከርኬ ከወጣቶች ጋር የተገናኙ ሲሆን ዝግጅቱ የጀመረው ሁለት ተጨማሪ ጥያቄዎች ለቅዱስነታቸው ከመቅረባቸው በፊት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ባቀረቡት ምስክርነት እንደ ነበር ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሥፍራው ለነበሩት በርካታ ወጣቶች ንግግራቸውን የጀመሩት፥ “አሰላሙ አለይኩም” ወይም “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” የሚለውን ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስን ሰላምታ በማስቀደን እንደ ነበር ተደምጧል።
“የወጣቶች ጉጉት የእግዚአብሔርን ፍቅራዊ ቅርበት እና በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት እና ኅብረት ለሌሎች እንዲያካፍሉ የሚያደርግ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ስሜት የሚገልጽ ነው” ብለው፥ በተለይም ከሶርያ እና ከኢራቅ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የውጭ አገራት የመጡ ሊባኖሳውያን ወጣቶችን ተቀብለዋል።
“አሁንም ገና ጊዜ አለ”
ከንግግራቸው ቀደም ብሎ የቀረቡ የአንቶኒ፣ የማርያ፣ የኤሊ እና የዩኤል ምስክርነቶችን በማስመልከት ሲናገሩ፥ “በመከራ መካከል ድፍረት፣ በብስጭት ውስጥ ተስፋ እና በጦርነት ጊዜ ውስጣዊ ሰላም” የሚሉ ታሪኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሊባኖስ ታሪክ በውዳሴ እና በመከራ ጊዜያት የተሞላ ነው” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ በዚህ ታሪክ ውስጥ ወጣቶች ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታትተው፥ “ምናልባት በጦርነት የተበታተነ እና በማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት የተበላሸ ዓለምን በመውረሳችሁ ምክንያት ብታዝኑም እኛ አዋቂዎች የሌለን የተስፋ ስጦታ በውስጣችሁ አለ” ሲሉ ተናግረው፥ “ለማቀድ፣ ለማለም እና መልካምን ለማድረግ ጊዜው ገና አልመሸም” ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣቶች የአሁንም የወደፊትም እንደሆኑ እና ታሪክን መለወጥ የሚችሉ መሆናቸውን በማስታወስ፥ ክፋት ለክፋት መድኃኒት ሊሆን እንደማይችል፥ ይልቁንም መልሱ ፍቅር ሊሆን እንደሚገባ በማሳሰብ፥ የአራቱ ወጣቶች ምስክርነት ከእርቅ እና ከጋራ ዕርዳታ የሚመጡ አዲስ ትንቢቶች ናቸው” ብለዋል።
“ክርስቶስ የሰላም መሠረት ነው!”
“የወጣቶች አገር ሊባኖስ እንደገና ታብባለች” በማለት አፅንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ብሔራዊ ዓርማ የሆነውን የዝግባ ዛፍን በማስታወስ፥ የዛፉ ጥንካሬ ከሥሩ እንደሚገኝ እና የሊባኖስ ሕዝብ ታሪክም ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸው፥ ወጣቶች ለራስ ጥቅም ሳይሉ ኅብረተሰብን ለማገልገል የወሰኑት ሰዎች መልካም ሥነ-ምግባር እንዲላበሱ አሳስበዋል።
“ወጣቶች አገሪቱ የሚያስፈልጋት የተስፋ ምንጮች እንዲሆኑ” በማለት ጥሪ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሁለቱ ወጣቶች የጠየቁት ጥያቄ የወደፊቱን ጉዞ ለማቀድ እንደሚረዳ ጠቁመው የመጀመሪያው ጥያቄ በሰላም ቁርጠኝነት ጸንቶ ለመቆየት የሚያስችል ጠንካራ መሠረትን ማግኘት እና ይህ መሠረት ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው፥ “ሰላም እውነተኛ ሊሆን የሚችለው የፓርቲዎች ዓላማ ውጤት ካልሆነ ብቻ ነው” ብለው፥ የሰላም መሠረት የሆነው ይቅርታ ወደ ፍትህ ሊመራል እንደሚችል አስረድተዋል።
እውነተኛ ጓደኝነት የጊዜ ገደብ የለውም!
ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቀረበላቸው ሁለተኛው ጥያቄ፥ ግንኙነቶችን በእውነተኛ ፍቅር ላይ መመሥረትን የሚመለከት ሲሆን፥ ይህን በማስመልከት ሲናገሩ ለግል ፍላጎቶቻችን ቅድሚያ መስጠት እንደማይገባ እና ራስ ወዳድነት የጓደኝነት ወይም የወዳጅነት ማዕከል ከሆነ ፍሬ እንደሌለው አስረድተዋል።
“እውነተኛ ፍቅር ጊዜያዊ አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እውነተኛ ፍቅር የጊዜ ገደብ ሊኖረው እንደማይችል፥ “እውነተኛ ጓደኝነት ከራስ በፊት ሌላውን የሚያስቀድም እና ይህ አክብሮት የተሞላበት እና ሌሎችን የማየት መንገድ ለጠቅላላው ኅብረተሰብ እና ለመላው የሰው ልጅ ክፍት የሆነ ታላቅ አንድነትን ለመገንባት ያስችላል” ብለው፥ “ጠንካራ ጓደኝነት የሚገነባው በእያንዳንዱ ጥሪ ውስጥ ለጋራ መተማመን እና ለቤተሰብ መንፈሳዊ ሕይወት ባለው ዘላለማዊነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ተስፋ መቁረጥ አይገባም!
ፍቅር የእግዚአብሔር በዓለም ላይ መገኘት ትልቁ መገለጫ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ቸርነት ለእያንዳንዱ የሰው ልብ የሚናገር በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ እንደሆነ እና በጎ ማድረግ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የኢየሱስን እና የቅዱሳንን ሕይወት የሚገልጽ ታሪክ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚህ አደባባይ ላይ የተገኙትን ወጣቶች እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትንም ጨምሮ በፍትሕ መጓደል እና በመጥፎ ምሳሌዎች ተስፋ ለመቁረጥ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ብዙ ወጣቶች እንዲያስቡ አደራ ብለው፥ እነዚህ በርካታ ወጣቶች መንግሥተ ሰማያትን እና ፍትሐዊ ምድርን ለማግኘት የሚያግዙ አዳዲስ መንገዶችን ለመፍጠር በመሥራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ወጣቶችን የቅዱሳን ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ፣ ካርሎ አኩቲስ እና ቅዱስ ራፍቃ፣ ብፁዕ ያቆብ ኤል-ሃዳድ እና ቅዱስ ቻርቤል ያሉ በርካታ የሊባኖስ ቅዱሳን ምሳሌዎችን በማስታወስ፥
“ትኩረትን በሚከፋፍሉ ነገሮች በተሞላው ዓለም ውስጥ ወጣቶች ዓይኖቻቸውን ጨፍነው በየቀኑ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲመለከቱ በማበረታታት እግዚአብሔር ዝም ያለ ቢመስልም በዝምታ ውስጥ እሱን ለሚፈልጉት እንደሚናገር አፅንዖት ሰጥተዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ወጣቶች የመቁጠሪያ ጸሎትን የማድረስ አስፈላጊነትን በማጉላት፥ “ጌታ ሆይ የሰላም መሣሪያ አድርገኝ” የሚለውን የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሰላም ጸሎት በልባቸው እና በአእምሯቸው ውስጥ እንዲይዙት በማሳሰብ ይህም ክርስቲያናዊ ጉጉት በውስጣቸው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።
