ፈልግ

በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ጽድቅ መጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ጽድቅ መጣ  (AFP or licensors)

በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ጽድቅ መጣ

ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት ምን እንደነበረ ከልደቱ በኋላ ምን እንደሆነ ሁሉም ነገር የተሻለ ለውጥ አግኝቶአል።

1ኛ/ ከልደቱ በፊት ቅዱስ ጳውሎስ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ” (ኤፌ. 5፣8-10) ይለናል። ቀድሞ በኃጢአት ጨለማ ነበርን በሰይጣን ተገዝተን ነበር። በጥጋባችን ከእግዚአብሔር ተለይተን ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ከገባንበት ተነሥተን ወደ ላይ ለመውጣት አቅም አጣን። የኃጢአት ሸክም ከበደን። የኃጢአት ጠንቅ ብርቱ በመሆኑ በእርሱ ምክንያት የአምላክ ፍቅርና ጸጋ አጠፋን። የጽድቅን መንገድ ረስተን ፊታችንን ወደ ኃጢአት መንገድ አቀናን። ወደ መጥፎ ምግባር አዘነበልን። ይህ አሰከፊ ኑሮ በአባታችን በአዳም ሰበብ መጣብን፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

2ኛ/ ከልደቱ በኋላ ይህ የጨለማ ከባድ ሁኔታ በክርስቶስ መምጣት ብርሃን ተወገደ። “ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ አሁን ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችሁ” (ኤፌሶን 5፡11) ይለናል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ በአዳም በደል በአዳም ጥፋት ጉዳት ቢመጣብን በተቃራኒው ደግሞ በክርስቶስ ደኀንነትና ጸጋ መጣልን። ቅዱስ ዮሐንስ ስለክርስቶስ መምጣት ጥቅም ሲናገር “ህግ በሙሴ በኩል ተሰጠን ደግና ጽድቅ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጠን” (ዮሐ. 1፣16-17) ይላል፡፡

ኢየሱስ ራሱ የጸጋዎች ሁሉ ባለቤት ወደ እኛ ሲመጣ ይህን ትልቅ ሰማያዊ ሀብት ይዞልን መጣ፡፡ ወደ ምድር ሲወርድ ከእርሱ ጋር ጽድቅ አብራ ወረደች፡፡ ልደቱ የጸጋዎችን መዝገብ የጽድቅን መንገድ ከፈተልን፡፡ ክርስቶስ በሥጋ ሲወለድ እኛ በፀጋው እንደገና ተወለድን፡፡  አዳም ኃጢአትን አመጣ፡፡ ይህም ከአምላካችን አጣላን፣ ከእርሱ አራራቀን በታተነን፣ ኑሮአችን የወደቀና የተባረረ ሆነ፣ ሞትና ኩነኔ አስከተለብን፣ አስከፊ ስደት አወረደብን፡፡ ክርስቶስ ግን ደኀንነት ሰጠን በጸጋ ደኀንነት ከኃጢአት ጨለማ ወደ አምላክ ብርሃን ከኃጢአት ሰንሰለት ወደ ነጻነት መንፈስ ተሻገርን፡፡ ጸጋው ከእርግማን ልጆች የምሕረት ልጆች አደረገን፡፡ ወደ ፊጣሪያችን መለሰን ከእርሱ ጋር አስታረቀን፡፡ የኃጢአት ልብስ አወለቀልን፣ አስወገደልን፣ የጽድቅን ንጹሕ ሸማ አለበሰን፡፡ የጽድቅን መንፈስ አጐናጸፈን፡፡

በዚህ ሁኔታ የልደቱ ጸጋ አንጽቶንና ቀድሶን የእግዚአብሔር ልጆች አደረገን የኃጢአትንና የጥፋትን ዘመን ለውጦ የምሕረትንና የደኀንነት ዘመን ለመጀመር አበቃን፡፡ ኃጢአት ምን እንደሆነ እንዴት አድርገን ልንጠላው እንደሚገባን አስተማረን፡፡ የነፍሳችንን ጠላቶች ድል መትተን የምናሸንፍበት ሰማያዊ ኃይልና ብርታትን ሰጠን፡፡ መንፈሳዊ ሀብታችንና ክብራችንን በዚህ በልደቱ ያመጣልን ጸጋና ጽድቅ ናቸው፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችንና ለብርታታችን ጸጋውና ጽድቁ የግዴታ ያስፈልገናል፡፡ ያለ ስጦታው በመንፈስ ልንኖር አንችልምና ተግተን እንጠብቀው፡፡ ይህንን እንዳናጠፋ ከክርስቶስ እንዳንለይ እንጠንቀቅ፡፡

10 January 2022, 12:06