የጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ሰንበት ዘጥምቀት - አስተርእዮ 1ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ
የዕለቱ ንባባት፡-
1. ገላ. 4፥21–31
2. 1ጴጥ. 2፥1-8
3. ሐዋ. 5፥17-28
4. ሉቃ 2፥42-52
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ። በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር። አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።
እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም። ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር። ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።
የእለቱ አስተንትኖ
በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘጥምቀት - አስተርእዮ 3ኛ ሰንበትን እናከብራለን።
በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ መልእክቶቹ እና ወንጌሉ አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።
በዛሬው የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት በእግዚአብሔር እና በቃሉም ተስፋ በማድረግ ኃይልም እንዳለው እንድንረዳ ዘንድ የሚያመለክት ቅዱስ ቃሉን ያካፍለናል። እርሱም ሕይወት ይሰጠናል። ሣራ ምንም እንኳ የዘጠና ዓመት ሴት ብትሆንም በእግዚአብሔር ቃል ይሰሐቅን ልትወልድ ቻለች። በተመሳሳይ መንገድ የገላትያሰዎች በእግዚአብሔር ቃል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተወልደዋል (ቁ. 29)። እነርሱም በተፈጥሮ የሥጋ ልጆች በመሆን ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ የሰማይቱ ኢየሩሳሌም ዜጎች፥ የአብርሃም እውነተኛ ልጆች ሆነዋል።
ዛሬ እኛ ክርስቲያኖች በክርስቶስ የምናምን ይነፃይቱ ሴት የሣራ ልጆች ነን። እኛ የተስፋው ልጆች ነን ቁ.(28)። የእግዚአብሔር ስጦታ በሆነው በጸጋው የእርሱ ልጆች ነን። በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማመን በተቀበልነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእርሱ ልጆች ሆነናል። ሮሜ. 8፥14 “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚኖሩ ሁሉ፥ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።” ገላ. 3፥26 “በክርስቶስ ኢየሱስ ባላችሁ እምነት የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና”
በሁለተኛው መልዕክት ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደ አዲስ እንደተወለደ ሕፃን ማለትም የእናቱን ጡት ወተት እንደሚመኝ ሁሉ፥ እኛ የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብና ለመረዳት፥ በተረዳነውም መሠረትም ለመኖር፥ በብርቱ መመኘት ይኖርብናል። ደኅንነታችንም እውን ልናደርግ የምንችለው ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው በማለት ምክሩን ይለግሣል።
ከሁሉ በፊት ግን በቁጥር 1 ልይ የተጠቀሱትን ኃጢአቶች ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራል። ምክንያቱም ልባችን በክፉ ነገር ከተሞላ፥ ለመንፈሳዊ ወተት ፍላጎት አይኖረንምና ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብ የእግዚአብሔርን ምሕረት፥ ቸርነትንና ሌሎች በረከቶቹንም “እንቀምሳለን”። የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብና ለቃሉም በመታዘዝ ራሱ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ደረጃ እንደርሳለን፤ ጸጋውንም እንቀበላለን። ስለዚህም መጸሐፍ ቅዱስን ስናነብ በቃሉ አማካይነት እግዚአብሔርን ለማወቅ ፍቅሩንም “ለመቅመስ” እናንበው። መዝ. 34፥8 “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፥ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ብሩክ ነው!”።
ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሕያው ድንጋይ በማለት ይገልጸዋል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተመረጠና ዋና የማእዘን ድንጋይ ነው (ቁ. 7)። ይህን ድንጋይ ከሕንፃው ከወጣነው ሕንፃው መቆም ስለምይችል ይፈርሳል። እግዚአብሔር ከሞት አስነስቶታልና ክርስቶስ ሕያው ድንጋይ ነው (ሮሜ. 6፥9)። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስም ደግሞ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ብሎታ (1ቆሮ.15፥45)። ይሁን እንጂ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም ሕያው የሆነው፤ ወደ እርሱ የመጣነውን እኛንም ሕያው አድርጎናል። የራሱ መኖሪያዎች እንድንሆን እግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤት ሆነን ለመታነጽ ይሠራናል (ኤፌ. 2፥18-22) እኛ ራሳችን የእግዚአብሔር ቤቶች ነን።
የዛሬው የወንጌል ክፍል ሕጻኑ ኢየሱስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከወላጆቹ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለፋሲካ በዓል እንደሔደ እና ከበዓሉም በኋላ እሱ በቤተ መቅደስ እንደቀረ፣ ወላጆቹም ከሦሰት ቀናት ፍለጋ በኋላ እንዳገኙት የሚተርክ ነው። ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ማርያም ይህ የእግአብሔር አደራ አለባቸውና እንደገና ወደኋላ ተመልሰው መፈለግና ማገኘት ግድ ሆኖባቸው ነበር።
እኛም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር አደራ አለብን፤ ልጁን ልኮልናል፣ ብዙ በረከትን በእቅፋችን ውስጥ አስቀምጧል፣ጸጋን ሰጥቶናል፤ ይህን ክቡር የሆነውን የአምላክ ስጦታ እንዴት ነው የያዝነው? ኢየሱስ ከሕይወታችን የራቀ ሲመስለንስ እንዴት ነው ወደ ፍለጋ የምንወጣው? የት ነው ኢየሱስን የምንፈልገው?
ለኢየሱስ ያለን ፍቅር እሱን ለመፈለግ በምናደርገው ጥረት እና በምንደክመው ድካም ይለካል። ከሁሉ በማስቀደም ኢየሱስን ለመፈለግ ስንነሳ ራሳችንን ማዘጋጀት ይገባናል ምክንያቱም ይህ ጉዞ ተጀምሮ ግማሽ መንገድ ላይ የሚተው አይደለም። ከኢየሱስ ወላጆች ይህን ጽናት ነው እንደ አብነት መውሰድ የሚገባን። እነሱ እንደሚያገኙት አምነው ነው የወጡት። በመጨረሻም የፈለጉትን አገኙ። እግዚአብሔር በቅን ልብ ለሚፈልጉት ጊዜውን ጠብቆ ይገለጣል፣በልባቸውም በመገኘት ደስ ያሰኛቸዋል፤ ይህን አምላክ በተረጋጋ ልብ እና መንፈስ መፈለግ፣ፍለጋውም በእምነት እና በተስፋ የታገዝ ሊሆን ይገባዋል። በትንሹም በትልቁም ማጉረምረም እና ማማረር ሳይሆን እንደነዚህ ሁለት ቅዱሳኖች በትዕግስት በመጽናት መጓዝ ነው፣ክርስቶስን የራስ እስከ ማድረግ ድረስ መትጋት፣ ለጸሎት እና ከእግዚአብሔር ጋር ለሚያገናኙን መንፈሳዊ ሰዓታትና መንፈሳዊ ተግባራት ታማኝ መሆን።
ቀላልና የተመቻቸ ሕይወት የለመደች ነፍስ ግን በመንፈስ እንቅልፋም ትሆናለች፤ ድካምን፣ተጋድሎን፣ መስዋዕትነትን የምትጠላ፣ መስቀልንም የምትጸየፍ ከሆነ ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው ማጉረምረም ብቻ የሚቀናት ነፍስ ኢየሱስን ማግኘት አትችልም፣የክርስትናው መንገድ ይከብዳታል።
አምላካችን ግን ራሱንም ሆነ በእኛ ላይ ያለውን ዕቅድ፣ፍቃዱንም የሚገልጽልን ተግዳሮቶችን በትዕግስት መቀበልና ማስተናገድ ስንችል ነው፤ እሳት ሸክላን እንደሚያጠነክር ፈተናም ነፍስን፣ እምነትን፣ ክርስትናን ያጠነክራል፤ በዚህ በእምነት ጉዞ፣ በየዕለቱ ክርስቶስን የበለጠ ለማግኘትና የራሳችን ለማደረግ በምንደክመው ድካም ፈተና እንዳይገጥመን የምንሻና የምንመኝ ከሆነ መንገድም ምርጫም ተሳስተናል፤ ይህን ስላወቁ ነው ዮሴፍና ማርያም እነዚያን ፈታኝ ቀናት በትዕግስትና በእምነት የኖሯቸው፤ በዚህ በፈተና መንገድ በመራመዳቸው የበለጠ በእምነት ጠንካሮች ሆኑ። ስለዚህ ማንም ሳይፈተን አይቀርም፤ እንኳን እኛ ክርስቶስ ራሱ መስቀልና ፈተና በበዛበት መንገድ ነው የተጓዘው፤ “ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” እስከማለት ደረሶ ነበር፤ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን እዚያ ላይ አላቆመም፣ ጉዞውን አላቋረጠም “ያንተ ፍቃድ ይሁን” ብሎ እስከ መጨረሻው የመስቀል መስዋዕትነት ራሱን አቅርቧል። ምክንያቱም የመጣው በአባቱ ቤት ለመገኘትና የአባቱን ፍቃድ ለመፈጸም ነው።
ስለዚህ ኢየሱስን ስንፈልግ እንደ ዮሴፍና ማርያም እምነትንና ትዕግስትን ስንቅ አድርገን ነው። ተራ እና ቀላል መንገድንማ እምነት የሌላቸውም ሰዎች ሊጓዙት ይችላሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት መኖር ለማን ያዳግተዋለ? ይህ ተራና ቀላል መንገድ ግን ክስትናውን አያጣፍጠውም። እነዚህ የኢየሱስ ወላጆች ባለፉበት መንገድ ማለፍና ወደ ቅድስና ለመድረስ ግን አድካሚውንና ተራራማውን መንገድ በትዕግስት፣በእምነትና በተስፋ መጓዝ የግድ ነው - ክርስቶስን ለማግኘትና ከእርሱ ጋር ለመወገን፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መልስም የምንማረው ትልቅ ትምሕርት አለ። እርሱ ከወላጆቹ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አታወቁምን?” ነበር ያላቸው ከአባቱ የተቀበለውን ተልዕኮ ሲያመለክት፤ በወንጌልም “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ፈልጉ” ነውና የተባለው (ማቴ 6፥33) ። በእንዲህ ያለ መንፈስ፣ በየዋህ ልብና በክርስቲያናዊ ፍቅር የሚመላለስ አማኝ እንደ ብላቴናው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በጥበብና በጸጋ እንዲሁም በሞገስ ያድጋል፣ ጣፋጭ የሆነ የክርስትና ሕይወትን መኖር ይችላል፣ ከእግዚአብሔርም ጋር በቅርብ ይተዋወቃል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእከቱ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል የሚለን” (ያዕ 4፥8) ።
ይህንንም ለማድረግ በቅድስና ሕይወት በመኖር ምሳሌ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን የሰማነውንም የእግዚአብሔር ቃል በሕወታችን ለመተርጎም እንድንችል ልባችንን ያነሳሳልን፡፡