ፈልግ

የሀብት ጠንቅ የሀብት ጠንቅ  (AFP or licensors)

የሀብት ጠንቅ

አንድ ሀብታም ሰው እርሻው ብዙ እህል አፍርቶ ተመለከተና “እህሌን የት አከማቻለሁ” ብሎ ተጨነቀ። ጥቂትም ከአሰበ በኋላ “የድሮ አሮጌ ጐተራዬን አፍርሼ በርሱ ምትክ ሌላ ሰፋ ያለ አዲስ እሠራለሁ፤ ከዚያም በኋላ ላለፉት ዓመታት ያከማቸሁትንና የዘንድሮውን ጭምር በአንድ ላይ ሰብሰቤ በዚህ ትልቁ ጐተራዬ እከተዋለሁ፤ ከዚያም ነፍሴን ለብዙ ዓመታት የሚበቃሽ እህል አለልሽ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበለሽ እላታለሁ” አለ፡፡ “እግዚአብሔርም አንተ ሞኝ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካንተ ልወስዳት ነው፤ የማይቀር ነው ትወሰዳለች ታዲያ ያቀማቸኸውን እህል ሁሉ ለማን ይሆናል”  (ሉቃ. 16፣21) የሚል በጣም አስፈሪ ቃል አሰማው።

በዚህ ምድር እስካለን ድረስ ብዙ እህልና ብዙ ገንዘብ ሰብስበን ሀብታሞች ለመሆን ከልባችን እንመኛለን፡፡ ገንዘብና እህል በብዛት ለማግኘት እንጥራለን ልባችንና አእምሮአችን ሀብት ወደ ማከማቸት ያደላል፡፡ የኑሮአችን ቀዳሚ ሐሳብና ትግል ገንዘብና ሀብት ማጋበስ ስለሚሆን ደም እስኪያልበን ድረስ ለፍተን ሀብታም ለመሰኘት እንጥራለን። ሰውዬ “ነፍስ ሆይ ለብዙ ዓመታት የሚበቃሽ ብዙ ሀብት እና እህል አለልሽ ከእንግዲህ ዕረፊ ብዬ ጠጪ ተደሰቺ” እያልን እናስደስታታን፡፡ ሕይወታችን ሁሉ የሚያስፈልገንን ያገኘን ሁነን ይሰማናል። የዚህን ዓለም ሀብት ለማግኘት ስንል በስንት እንቅልፍ እናጣለን። ምክንያቱም ያገኘነው ሀብትና ያከማማቸነውን ገንዘብ ስለማያረካንና የሀብትንና የገንዘብ ፍቅር ስለሚጸናወተን እንቸገራለን ባለን መጠን በቃን ተመስገን ማለት ያቅተናል።

ልባችን በሀብትና ምኞት ከተቃጠለ ስቃይና መከራ ይበዛበታል፡፡ ከመከራና ስጋት ጋር ደግሞ ዕረፍት እርካታ እንቅልፍ የለም፡፡ የሀብት ሐሳብ በልባችን ሥር ከሰደደ የእግዚአብሔር መንፈስ ከልባችን ይሸሻል፡፡ በሀብት ከተማረክን መንፈሳዊ ነገር እንንቃለን። ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች ማገለገል አትችሉም´ አንዱን ትወዳለህ ሌላውን ትጠላለህ፣ ገንዘብና እግዚአብሔርን በአንድ ጊዜ ልታገለግሉ አትችሉም” ይለናል (ማቴ. 6፣24 )። ሀብት ራሱ አምላካችን ከሆነ እውነተኛውን አምላካችን እግዚአብሔርን እንተዋለን በእርሱ ምትክ አላፊና ጠፊ ሀብትን ጨብጠን ለመኖር እንጥራለን። ገንዘብን ስናስብ አምላክንና ነፍስን የምናስብበት ጊዜ እናጣለን፡፡

እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ይናገረናለ እኛ ግን የሀብትና የገንዘብ ጫጫታ ስለሚበረታብን መስማት ያቅተናል፣ ሕሊናችን ቢወቅሰንም አናስተውልም። በሥጋ ረገድ እየበለጸግንና እየዳበርን ሀብት በሀብት ላይ እያከማቸንና ገንዘብ አጋብሰን ከፍ እንላለን። ነፍች ግን እየጐደለና እየቀነሰ ይሄዳል። “ሀብትም ወደ መንግሥተ ሰማያተ ሊገባ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደገና እላችኂለሁ ሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ይልቅ ግመል በርፌ ቀዳዳ መሹለክ ይቀላታል” (ማቴ. 19፣23 – 24 ) እያለ ኢየሱስ ይናገራል፡፡

መንፈሳዊ ጉዳይ ረስተን በሀብት ተውጠን ስነኖር በድንገት ሞት ይመጣብናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳንዘጋጅና ምንም በጐ ምግባር ሳንይዝ በአምላክ ፍርድ ፊት ቀርበን የሚገባንን ፍርድ እንቀበላለን፡፡ “ሀብታሙ ሰውዬ ሲሞት ወደ ገሃነ እሳት ወረደ ይለናል ወንጌል (ሉቃ. 17፣ 19-34)። ነቢዩ ዳዊት “ሀብት ቢመጣላችሁ ልባችሁ በትዕቢት አይወጠር” (መዝ. 49) እያለ ያስጠነቅቀናል።

ሀብት በመሠረቱና በባሕርዩ ክፉ አይደለም። ምክንያቱም የአምላክ ስጦታና ጸጋ ነው፡፡ መልካም ስለሆነ ደግሞ እንዲጠቅመን ተብሎ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነው። የሚጠቅመንም አምላክ እንደሚፈልገው አድርገን ስንጠቀምበት ነው፡፡ ልባችን በሀብት ላይ ብቻ ማተኰር የለበትም፡፡ ሕይወታችን አምላካችንና ዓላማችን ሀብት መሆን የለበትም፡፡ እግዚአብሔርን እና ነፍሳችንን ሊያስረሳን አይገባንም፡፡ ከሁሉ አስቀድመን ስለ አምላካችን ስለነፍሳችን በኋላ ደግሞ ስለ ሀብታችን እንድንቆረቆር ይገባናል፡፡ በልባችን ከሁሉ አስቀድሞ የአምላክ ፍቅር መንፈሳዊ ሐሳብ ሊነግሥ ያስፈልጋል፡፡

15 June 2022, 11:54