ፈልግ

የእግዚአብሔር መላአክ ማርያምን ስያበስር የሚያሳይ ምስል የእግዚአብሔር መላአክ ማርያምን ስያበስር የሚያሳይ ምስል  

እግዚአብሔር በምልአት በማርያም ውስጥ ስላደረ ኃጢአት በማርያም ውስጥ ምንም ቦታ አልነበረውም!

የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 16/2015 የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል። በካቶሊክ ቤተክርስቲያ ስርዓተ አምልኮ ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍተኛ የሆነ ቦታ እንደሚሰጣት ይታወቃል። በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶግማ ወይም የማይሻር የማይለወጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ ማርያምን የሚመለከቱ 4 ዶግማዎች ይገኛሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ብቻ ሳትሆን እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በባሕርዩ አምላክ በመሆኑ” (ፊል 2፡6) የተነሳ “የእግዚአብሔር እናት ናት” የሚለው ማርያምን በተመለከተ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶግማ ውስጥ የተካተተ የእምነት አስተምህሮ ሲሆን (Mary Mother of God) ዓመታዊ በዓሉም በፈረንጆቹ አዲስ አመት መጀመርያ ላይ ይከበራል፣ በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር በእየአመቱ በታኅሳስ 22 ዓመታዊ በዓሉ በድምቀት የከበራል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በእየአመቱ በኅዳር 28 ዓ.ም. የሚከበረው የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል ሲሆን ይህ “የጽንሰታ ማርያም” በዓል ማርያም “ያለአዳም ኃጢአያት የተጸነሰች ናት፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር የልጁ እናት እንድትሆን አስቀድሞ የመረጣት በመሆኑ የተነሳ እኛ ሰዎች ሁላችን ይዘነው የምንወለደው እና ምስጢረ ጥምቀት በምንቀበልበት ወቅት ከሚደመሰሰው (ከሚሰረየው) ኃጢአት ነጻ ሆና እንድትወለድ እግዚአብሔር አድርጓታል” የሚለው በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው ዶግማ (Immaculate conception) ነው።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የጸነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካይነት ነው፣ እርሱንም የወለደችው በድንግልና ነው፣ ከወለደችሁም በኋላ እንኳን ለዘልዓለም ድንግል ሆና ትኖራለች” የሚለው 3ኛው ዶግማ ነው (The Perpetual Virginity of Mary) (ሉቃስ 2፡22-40)።

በአራተኛ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ በክብር ያረገችበትን ሁኔታ የሚገልጽ ዶግማ ሲሆን ይህ “የፍልሰታ ማርያም” በዓል ተብሎ የሚጠራው እና በሀገራችን የቀን አቆጣጠር በእየዓመቱ በነሐሴ 16 የሚከበረው በዓል ነው፣ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድር ላይ የነበራት ቆይታ ካበቃ በኋላ በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ ተወሰደች” በማለት ማርያም በነፍስ እና በሥጋ ወደ ሰማይ መፍለሷን የሚያመልክት ቀኖና ነው (The Assumption of Mary into heaven)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች እንግዲህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የተመለከቱ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እመነት ውስጥ የተካተቱትን አራቱ ዶግማዎች ይህንን ያህል በጭሩ ካስተዋወቅናችሁ ቀድም ሲል በመግቢያችን ላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርነው እ.አ.አ በመጋቢት 25/2023 በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በደመቀ ሁኔታ የተከበረውን የሚገኘውን የጽንሰታ ማርያም ዓመታዊ በዓል አስመልክተን ያዘጋጀነውን አስተንትኖ እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣ መልካም በዓል ይሁንላችሁ!

ዛሬ የጽንሰታ ማርያምን ውበት እናሰላስላለን። በሉቃስ ወንጌል 1፡26-38 ውስጥ የተጠቀሰው የማርያም ብስራት ታሪክ ዛሬ እያከበርነው የሚንገኘው በዓል ምን እንደሆነ ለመገንዘብ እንድንችል ይረዳናል፣ በተለይም ደግሞ የመልአኩ ገብረኤል ሰላምታ ይህንን በዓል በላቀ ሁኔታ እንድንገነዘብ ያደርገናል። እርሱም በሰውኛ ቋንቋ ለመተርጎም የሚያዳግቱ ቃላትን በመጠቀም “ፀጋ የተሞላሽ” በማለት ይጀመራል። ማርያም ብሎ በስሟ ከመጥራቱ በፊት “ፀጋ የተሞላሽ” በማለት በመጀመር በዚህም በእግዚአብሔር የተሰጣትን አዲስ ስም ይፋ አደረገ፣ ይህም ወላጆቿ ከሰጧት ስም የበለጠ ዋጋ እንዳለው አሳየ።  እኛም “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ!” እያልን ነው የምንጠራት።

ታዲያ “ጸጋ የሞላሽ” ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ማርያም በእግዚአብሔር ሕልውና የተሞላች ናት ማለት ነው። እግዚአብሔር በምልአት በውስጧ ስላደረ ለኃጢአት ምንም ቦታ በውስጧ የለም ማለት ነው። ዓለማችን በተለያዩ ክፉ በሆኑ ነገሮች ተበክሎ ባለበት በሁኑ ወቅት ይህ በጣም ትልቅ የሆነ ነገር ነው። እያንዳንዳችን ውስጣችንን ብንመለከት የጨለሙ ጎኖቻችንን መመልከት እንችላለን። ከማርያም በስተቀር ሁሉም ታላላቅ ቅዱሳን የሚባሉ ሳይቀሩ ኃጢያተኞች ነበሩ። ሁል ጊዜ የሰው ልጆች የልምላሜ መገለጫ የሆነች፣ በኃጢአት ያልተበከለች፣ ያለአዳም ኃጢአት የተጸነሰች፣ ሙሉ በሙሉ “እንዳልከኝ ይሁንልኝ” በማለት ወደ ዓለም በመምጣት እና ለዓለም አዲስ ታሪክ የፈጠረውን እግዚአብሔርን በውስጧ በማኖር የታዘዘች እርሷ ብቻ ናት።

ሁል ጊዜ “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ!” በምንልበት ውቅቶች ሁሉ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ይህንን ታላቅ ነገር በሕይወቷ ያከናወነውን እግዚአብሔርንም እናመሰግናለን። “ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ” በምንልበት ወቅት ይህንንም የምንለው ለየት ባለ እና ክብር በተሞላው መልኩ ነው። እርሷ ሁል ጊዜ ወጣት እንደ ሆነች አድርገን ነው የምንቆጥረው ምክንያቱ ኃጢአት አላስረጃትምና ነው። እኛን ልያስረጀን የሚችል አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይህም የውስጥ እርጅና ነው፣ በእድሜ ማርጀት ሳይሆን ከኃጢአት የሚመጣ እርጅና። እኛን የሚያስረጀን ኃጢአት ነው፣ ምክንያቱም ኃጢአት ልባችንን ስለሚበክል ነው። ልባችንን ይዘጋል፣ ልባችንን ያፈርሳል፣ ልባችን እንዲሰቃይ ያደርጋል። ነገር ግን በጸጋ መሞላት ከኃጢአት ነጻ ያደርጋል። ማርያም ሁሌም ወጣት ናት የምላችሁ በዚሁ ምክንያት ነው።

ቤተክርስቲያን ዛሬ (በኅዳር 28/2012 ዓ.ም) ይህንን የማርያም ውብት እና ንጽሕና በማሰላሰል ላይ ተገኛለች። የእርሷ ወጣትነት በእድሜዋ እንደ ማይለካ ሁሉ እንደዚህም የእርሷ ውበት በውጫዊ ገጽታዋ አይለካም። የሉቃስ ወንጌል 1፡26-28 ላይ የተጠቀሰው ቃል የሚገልጸው ይህንኑ ነው፣ በጣም ትሁት ከሆነ ቤተሰብ የተገኘች፣ በትህትና በናዝሬት ትኖር የነበረች፣ በሰዎች ዘንድ ብዙ የምትታወቅ ሴት እንዳልነበረችም ያስረዳናል። መልአኩ ገብርኤል ወደ እርሷ መምጣቱን እንኳን ማንም ሰው አያውቅም ነበረ፣ ምናልባትም በዚያን ወቅት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ስላልነበሩ ይሆናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያ የተደላደለ ኑሮ አልነበራትም ነበር፣ በአንጻሩ ግን ጭንቀትና በፍርሃት ተሞልታ ነበረ፣ በሉቃስ ወንጌል 1፡29 “ማርያም በመልአኩ ንግግር በጣም ደንግጣ” እንደ ነበረ ይናገራል፣ መልአኩ ገብርኤል ከእርሷ ተለይቶ በሄደበት ወቅት ችግሮቹዋም ተባብሰው ነበር።

ነገር ግን ይቺህ “ጸጋ የተሞላች” ሴት ውብ የሆነ ሕያወት ኖራላች። ታዲያ የእዚህ ምስጢር ምን ይሆን? ይህንንም ለመረዳት አሁን ለአንድ አፍታ መልአኩ ገብርኤል ያበሰራትን ብስራት መመልከት ያስፈጋል። ብዙ ሰዓሊያን የመልአኩ ገብርኤልን እና የማርያምን ግንኙነት በስዕል ስያስፍሩ ማርያም ከመልአኩ ፊት ለፊት ቁጭ ብላ ትንሽዬ መጽሐፍ በእጃ እንደ ያዘች የሚያሳይ ስዕል ስለዋል። ይህ መጽሐፍ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህም ማርያም እግዚአብሔርን ማዳመጥ ተለማምዳ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ትተዋወቅ ነበር። ታዲያ የማርያም ሕይወት ምስጢር ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ ለእርሱ ልብ ቅርብ ነበረች፣ የእርሱን ሥጋ በማህጸኑዋ አሳደረች። ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ በመኖር፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከእርሱ ጋር ትወያይ ነበረ፣ ይህ ድርጊቷ የማርያም ሕይወት ያማረ እንዲሆን አድርጎታል። የምያልፈው ውጫዊ ውበት ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር የሚጠቁም ልብ ሁልጊዜ ሕይወትን ውብ ያደርጋል። ዛሬ በደስታ ይችህን “ጸጋ የተሞላች” እንመልከት። ሁልጊዜ ወጣት ሁነን መኖር እንድንችል ትረዳን ዘንድ “ኃጢአትን እብየው አልፈልግህም!”በማለት በአንጻሩም ለእግዚአብሔር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ውብ የሆነ ሕይወት እንድንኖር እርሷ በአማላጅነቷ ሁላችንንም ትርዳን አሜን።

 

25 March 2023, 15:57