ፈልግ

የመጋቢት 10/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘደብረ ዘይት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 10/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘደብረ ዘይት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  (©khanchit - stock.adobe.com)

የመጋቢት 10/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘደብረ ዘይት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” (ማቴዎስ 24፡12)

የእለቱ ምንባባት

1.     1ተሰ 4፡13-18

2.     2ጴጥ 3፡7-14

3.     ሐዋ.ሥ. 24፡1-21

4.     ማቴ 24፡1-35

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የዓለም መጨረሻ ምልክቶች

ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲህ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” አላቸው። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለ ሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው።

“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ። ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።

አሠቃቂው መከራ

“እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተነገረው፣ ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል። በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤ በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። ‘በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል። ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ። እነሆ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።

“ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ እበረሐው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ።

የሰው ልጅ ክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት

“ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ‘ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኃይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ።

የጌታ መምጫ ጊዜ ምልክት

“ከበለስ ዛፍ ይህን ትምህርት ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ። እንደዚሁም እነዚህን ሁሉ ስታዩ፣ እርሱ በደጅ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።

የእለቱ የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

 

የተወደዳችሁ ወንድቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘደብረ ዘይት ወይም ደግሞ እኩለ ጾም የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን። የዕለቱም ወንጌል በዋነኛነት ጌታ በዳግም ምጽአቱ የሚከሠቱትን ሁኔታዎች በልዩና በጣም ትእይንታዊ በሆነ መልኩ ገልጾ የሰው ልጆች ደግሞ ምድርና ሁለንተናዋ በሚናወጡበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ በእርሱ እምነት በመጽናት መኖር እንደሚገባቸው ያሳየናል።

በዚህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁለተኛ ጊዜ በግርማ መለኮት እንደሚመጣ የዓለምም ፍጻሜ እንዴት እንደ ሚሆን ለሐዋርያት በደብረ ዘይት ማስተማሩን እንዲሁም በክብር ያረገውን ጌታ ለሚጠባበቁ ዋጋቸውንም ላልተቀበሉትም ፍርዳቸውን ሊከፍል የምድርን ሥርዓት ሊሽር ሰማይና ምድርን አሳልፎ ለወዳጆችቹ መንግሥቱን ሊያወርስ የቅዱሳንንም እንባ ከዓይናቸው ሊያብስ፣ ኃጢያትን ሊወቅስ፣ ጻድቃንን ሊያወድስ መመጣቱን እያሰበች ቤተ ክርስቲያን ፈጣሪዋን ታመልካለች በዚህ በዓምስተኛው የጾም ሳምንት።

በድጋሚ የእዚህ ዓመት የፋሲካ በዓል በጣም ቀርቡዋል። ለፋሲካ በዓል በምንዘጋጅበት በአሁኑ ወቅት እግዚኣብሔር በመለኮታዊ ጥበቃው ይህንን የዓብይ ጾም ወቅት መዘጋጃ ይሆነን ዘንድ በመስጠት “በምስጢራት የታጋዘ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ” ይጋብዘናል። ይህ የዓብይ ጾም ወቅት እኛ ወደ እግዚኣብሔር በሙሉ ልባችን፣ ማንኛውንም ዓይነት የሕይወት አካሄዳችንን ወደ እርሱ እንድንመልስ ዘንድ ይጠራናል ይህንንም ለውጥ እንድናደርግ ያበቃናል።

በእዚህ መልእክት በዚህ አመት እንደገና መላውን ቤተ ክርስትያን በእዚህ በዓብይ ጾም ወቅት በሚገኘው ጸጋ በመታደስ፣ በደስታና በእውነት ውስጥ መኖር ይችሉ ዘንድ ለማገዝ እሻለሁ። ይህንንም ለማድረግ ያስችለኝ ዘንድ ይህንን መስመር የምጀመረው ኢየሱስ ከማቴዎስ ወንጌል 24፡12 ላይ በተጠቀሰው “ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” በምለው መሪ ቃል ነው።

እነዚህ ቃላት የመጡት ኢየሱስ ሰለ መጨረሻው ጊዜያት በሰበከበት ወቅት ነበር። እነዚህ ቃላት የተስበኩት በኢየሩሳሌም ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በኢየሱስ ላይ የሚደርሰው መከራ ከሚጀምርበት ሥፍራ ነው። ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈልጎ ኢየሱስ ታላቁ መከራ እንደሚመጣ እና አማኝ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል ራሱን እንዲያዘጋጅ በማሰብ፣ ታላቅ የሆነ መከራ እንደ ሚገጥማቸው፣ ሀሰተኛ ነቢያት ሰዎችን በተሳሳተ መንግድ እንደ ሚመሩዋቸው ለማሳሰብ ፈልጎ የነበረ ሲሆን፣ እናም የወንጌል ዋናው ማዕከል የነበረው ፍቅር በበርካታ ሰዎች ልብ ውስጥ ቀዝቅዞ እንደ ነበረ ለማመልከት ፈልጎ ነው።

ሐሰተኛ ነብያት

እስቲ የቅዱስ ወንጌልን ክፍል እንመልከት እና እነዚህ ሐሰተኛ ነብያት የሚባሉት እነማን እንደ ሆኑ እንገነዘብ። እንደ “አታላይ እባብ” ሆነው በመቅረብ  የሰው ልጆችን ስሜት በመጫን፣ የእነርሱ አስተሳሰብ ባሪያ በማድረግ ወደ ፈለጉበት ቦታ የሚመሩዋቸው ሰዎች ናቸው። በጣም በርካታ የሆኑ የእግዚኣብሔ ልጆች በጊዜያዊ ደስታ እየታለሉ እውነተኛ ደስታን ስያጡ እንመለከታለን።  ስንት እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን ናቸው የገንዘብ ትርፍ ባሪያ ብቻ የሚያደርጋቸውን እና የፍጆታ ቁሳቁሶችን ብቻ ማስገኘት የሚችለውን ሐብት እያለሙ የሚኖሩ ስንቶች ናቸው! ስንቶች ናቸው ራሳቸው ተጨማሪ ነገር የማያስፈልጋቸው፣ ራሳቸው በራሳቸው ሙሉ የሆኑ ሰዎች አድርገው በመቁጠር የሚኖሩ ፣ነገር ግን በመጨረሻ በብቸኝነት መንፈስ ውስጥ ገብተው የምሰቃዩ ሰዎች ስንት ናቸው!

ሐሰተኛ ነብያት ብዙም ጊዜ ለመከራዎች ሁሉ ባዶ የሁኑ እና የማይጠቅሙ ቀላል እና ፈጣን የሆኑ መፍትሄዎችን በማቅረብ የምያታልሉ “ቀማኞች” ናቸው። በአደገኛ አደንዣዥ ዕጾች፣ ተጋላጭ ለሆኑ ጾታዊ ግንኙነቶችን በፍጥነት፣ ነገር ግን አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመሮጥ ሂደት ወስጥ ስንት ወጣቶች ይወሰዳሉ! ግንኙነታቸው ፈጣን የሚመስል እና ቀጥተኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምያዩት እውነተኛ ባልሆነ "ምናባዊ" ህይወት ውስጥ የሚኖሩ ስንቶቹ ናቸው! እነዚህ አጭበርባሪዎች እውነተኛ ዋጋ የሌላቸው ነገሮች በሚያሽከረክሩበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ እጅግ ውድ የሚባሉ ለምሳሌም እንደ  ክብር፣ ነፃነት እና ፍቅር የመሳሰሉ የሰው ልጆች እሴቶችን ይሰርቃሉ። በውጫዊ ገጽታችን እንድንኩራራ ይገፋፉናል፣ በመጨረሻም ያታልሉናል። በእዚህም በፍጹም መገረም የለብንም። የሰውን ልብ ለማስደመም በዩሐንስ ወንጌል 8፡44 እንደ ተጠቀሰው “ሐሰተኛ እና የሐሰትም አባት” በመሆን  ክፉን ነገር እንደ መልካም ሐሰትን ደግሞ እንደ እውነት አድርገው ያቀርባሉ። ለዚህም ነው እያንዳንዳችን ወደነዚህ ሐሰተኛ ነብያት ውሸቶች እየተጓዝን እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለመመልከት ወደ ልባችን እንድንመለከት የምጋብዘው በእዚሁ ምክንያት ነው።

ውስጣችንን በጥልቀት መመርመርን እና መልካሙን እና ዘላቂውን ምልክት በልባችን ውስጥ መተው እንድንችል መማር አለብን ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እና ለእኛ ጥቅም ሲባል ጭምር ነው።

የቀዘቀዘ ልብ

በውስጣችን ያለው ፍቅር “እንዴት ሊቀዘቅዝ ቻለ?” በማለት ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። ይህም በውስጣችን ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ መሄዱን የምያሳይ ምልክት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በውስጣችን ያለውን ፍቅር የሚያበላሸው “ለገንዘብ ያለን ፍቅር” ሲሆን ይህም በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10 ላይ እንደ ተጠቀሰው “የክፋት ሁሉ ሥር መሰረት” ነው። ከእዚያም በመቀጠል ከእግዚኣብሔር እና እርሱ ከሚስጠን ሰላም መራቅ እንጀምራለ፣ እግዚኣብሔር በቃሉ እና በምስጢራቱ ከሚሰጠን ምቾት በመራቅ፣ የራሳችንን ምቾት እንፈልጋለን። በማህጸን ውስጥ ያለ ሕጻን፣ አዛውንቶች እና በሽተኞች፣ ስደተኞች፣ በመካከላችን የሚኖሩ፣ ግን ለእኛ ባዕድ የሆኑ ሰዎች፣ ከእኛ እኩል እንደ እኛ ምኖር ያልቻሉ ጎረቤቶቻችን ከእዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወጣ ባለ መልኩ የሚያስቡ ሰዎችን ሁሉ ለእኛ አደገኛ እንደ ሆኑ በማሰብ መጠራጠር እንጀምራለን።

ተፈጥሮ በራሷ ይህንን እየቀዘቀዘ ያለውን ፍቅር ትረዳለች። መሬታችን በእኛ እንቢተኛነት ተመርዛለች፣ በቸልተኝነት እና የራስን ጥቅም ብቻ በማሳደድ ተበዝብዛለች። በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ለአስገዳጅ ስደት የተዳርጉ ስደተኞችን በሚያመላልሱ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ጀልባዎች ምክንያት በሰጠሙ ባሕር ተበክሉዋል። በእግዚኣብሔር እቅድ መሰረት ለእርሱ የሚቀርበው ዝማሬ ያምያርግበት/የሚያልፍበት/ወደ ላይ የሚወጣበት ሰማይ በራሱ ሞትን በሚያፍጥኑ በራሪ ነገሮች (አውሮፕላኖች) ተጨናንቁዋል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ፍቅር ራሱ በጣም እየቀዘቀዘ መጥቱዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ፍቅር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን በአንጻሩም ራስ ወዳድነት፣ መንፈሳዊነትን ማጉደፍ፣ መጪው ጊዜ ጨለማ እንደ ሆነ ማሰብ ሁሉንም ነገር ለራሳችን ብቻ ለማጋበስ ማሰብ እርስ በራሳችን ያለአግባቡ መወዳደር መፎካካር፣ ቆንጆ መስለን ለመታየት ብቻ በመፈለግ ዓለማዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን  መቀራመት ከቀን ወደ ቀን ለሐዋሪያዊ  ተልዕኮ ያለን ፍላጎት እየቀነሰ መምጣት እነዚህ እና እነዚህ ምልክቶች ናቸው።

ታዲያ ምን ማድረግ አለብን?

ምን አልባት ቀደም ሲል የጠቀስኩዋቸውን ፍሬ ሐሳቦች በውስጣችሁ እና በሁለንተናችው የተረዳችሁት ይመስለኛል። ነገር ግን እናታችን እና አስተማሪያችን የሆነችው ቤተ ክርስቲያን መራራ ከሆነ የእውነት መድኃኒት ጋር በመቀናጀት፣ በእዚህ የዐብይ ጾም ወቅት በጸሎት፣ ምጽዋት በመስጠት እና በጾም የሚገኘውን ጸጋ እንድንቀበል ትጋብዘናለች።

ለጸሎት ያለንን ጊዜ ከፍ በማድረግ ለጸሎት ተጨማሪ ጊዜን በመስጠት በምስጢር የምንሰራቸውን ምስጢራዊ ውሸቶቻችን እና እራስን የማታለል ተግባሮቻችን ከልባችን ውስጥ እናስወግዳለን፣ ከዚያም እግዚአብሔር የሚያቀርበውን መጽናኛ እናገኛለን። እርሱ አባታችን በመሆኑ የተነሳ ሕይወታችንን በምልአት እንድንኖር ይፈለጋል።

ምጽዋት መመጸውት ከስግብግብነት ነፃ ያደርገናል እናም ጎረቤቶቻችንን እንደ ወንድም ወይም እህት አድርገን እንድንመለከትም ይረዳናል። ያለኝ ነገር ሁሉ የእኔ የብቻዬ አይደለም። ክርስትቲያን እንደ መሆናችን መጠን፣ የሐዋርያትን መልካም ምሳሌ በመከተል እና ያለንን ከሌሎች ጋር በመካፈል የቤተ ክርስቲያናችንን ተጨባጭ ምስክርነት እና ኅብረት መግለጽ እንዴት ደስ ያሰኛል። በእዚህ ረገድ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች የሚውል ምጽዋዕት እንዲሰበስቡ የጻፈላቸውን የማበረታቻ መልእክት መጥቀስ እፈልጋለሁ (2ቆሮ.8፡10)። በእዚህ የዐብይ ጾም ወቅት በትክክል ልናደርገው የሚገባው ጉዳይ ይህ ነው፣ ብዙ ሰዎች ምጽዋዕትን ሰብስበው ቤተ ክርስቲያንን እና የተቸገሩ ሰዎችን ማረዳት ይኖርባቸዋል። ሆኖም የእኛን እርዳታ ከሚማጸኑ ሰዎች ጋር በየቀኑ ስንገናኝ፣ እንደ እነዚህ ያሉ ተማጽኖዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጡ እንመለከታለን። ምጽዋዕት በምንሰጥበት ወቅት ሁሉ የእግዚኣብሔርን መለኮታዊ ጥበቃ ከሁሉም ጋር እንቋደሳለን ማለት ነው። እግዚአብሔር በእኔ በኩል አንድ ሰው ዛሬ ቢረዳ ነገ እኔን ሲቸግረኝ ደግሞ እንዴት አይረዳኝ? እግዚአብሔር በተሻለ ሁኔታ ደግ የሆነ ማንም ሰው የለም።

ጾም ለቁጣ ወይም ለረብሻ ያለንን ዝንባሌ ያዳክመዋል፣ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ እንድንላቀቅ በማድረግ ለእድገታችን ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል። በአንድ በኩል ችግረኞች እና ረሃቦችን ለመቋቋም እንድንችል ያደርገናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ለእግዚአብሔር  ያለንን መንፈሳዊ ረሃብ እና ጥማት ይገልጻል። ጾም እንድንነቃ ያደርገናል። ይህም የእራሳችንን ፍላጎት ማርካት የሚስችለንን እግዚአብሔርን የመታዘዝ ምኞታችንን ያድሳል።

የምኖረው ለምንድነው ብሎ የማይጠይቅ ሰው ምናልባት ገና መኖርን አልጀመረም ማለት ይቻላል። ለዚህና ለዚያ ነው ማለቱ ባይቻልም ግን በጉዞ ላይ መሆናችንና ወደ አንድ አቅጣጫ ሕይወታችን እያለፈች መሆኑን ማንም አይክድም። ታዲያ እየተጓዙ ወዴትና ለምን ያለማለት ካለምጓዝ አይተናነስም። ከክርስቲያናዊ እይታ አንጻር የዚህን መልስ በሁለተኛው የጴጥሮስ መልእክት ውስጥ እናገኛለን፦ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚመስላቸው ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ እንጂ ማንም ሰው እንዳይጠፋ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሣል”። ለንስሐ ማለት ይበልጥ ወደ አምላካችን እንድንቀርብ ማለት ነው። ይህ እውነት በተቃራኒው እየሆነብን ይመጣል፤ በዕድሜ ይበልጥ ባደግን ቁጥር ይበልጥ ከእግዚአብሔር ማለትም ከእምነታችንና ከቤተ ክርስቲያናችን እየራቅን ስንመጥ ይስተዋላል። ይህ ዓይነት ጉዞ ግን መለመድና መቀጠል እንደሌለበት እናስተውል። ይህ እንግዲህ ለምን እንኖራለን የሚለውን ካመላከተን እንዴት የሚለውም ከዚያ የተለየ አይደለም።

በወንጌሉም ቢሆን ማእከላዊ መልእክቱ በዓለም ፍጻሜ ሊሆን ያለው የመብረቅና የምድር መናወጥና የመአት ጋጋታን መተረክ ሳይሆን እንዴት መኖር እንዳለብን መናገር ነው፦ “በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሀይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። …ከክፋት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል።” ይላል። ሃይማኖትን መካድ፣ ሌላውን አሳልፎ መስጠት፣ እርስ በእርስ መጣላት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ…ዛሬ የሌሉ ነገሮች ናቸው ካልን ስህተት ሊሆን ይችላል። የራሳችን ሕይወት ውስጥ ገብተን መልሱን እናርመው። ስለዚህ እንዴት መኖር አለብን ካልን ሀይማኖታችንን ባለመካድ፣ ሌላውን አሳልፎ በመስጠት ሳይሆን ለሌላው ራሳችንን አሳልፈን በመስጠት፣ እርስ በርሳችን በመፋቀር…መሆኑን አውቀን ይህን የጾም ወቅት እናትርፍበት።

“ስለዚህ ወዳጆች ሆይ!...ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ሥሩ” (2ጴጥ.3:14)። የተከበራችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዚህ የጾም ወቅት ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ ጌታ በሚመጣበት ወቅት ተዘጋጅተን እንዲያገኘን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማልጅነቷ ትርዳን። አሜን!

አቅራቢ አባ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
18 March 2023, 14:23