ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ ኢየሱስን መመልከት የቤተሰብ ጥሪ

በቤተሰቦች ውስጥና መካከል የወንጌል መልእክት ሁልጊዜ ማስተጋባት ይኖርበታል፤ የዚያ መልእክት ፍሬ ነገር፣ ማለትም ስብከተ ወንጌል፣ ‹‹እጅግ ውብ፣ ምርጥ፣ እጅግ ማራኪና እጅግም አስፈላጊ” ነው፡፡ ይህ መልእክት “የስብከተ ወንጌል ሁሉ እምብርት ነው”፡፡ “በተለያዩ መንገዶች ደጋግመን መስማት የሚገባንና በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሁል ጊዜ ማወጅ ያለብን” ቀዳሚና እጅግ አስፈላጊ አዋጅ ነው፡፡ በእርግጥ “ከዚያ መልእክት ይበልጥ ብርቱ፣ መሠረታዊ፣ የተረጋገጠ፣ ትርጉም ያለውና ጠቢብ የሆነ አንዳችም ነገር የለም”፡፡ ስለሆነም፣‹‹ክርስቲያናዊ ሕንጸት ሁሉ ወደ ስብከተ ወንጌል ይበልጥ ጠልቆ መግባትን ያካትታል”።

ስለ ጋብቻና ቤተሰብ የምናስተምረው ትምህርት በዚህ የፍቅርና የደግነት መልእክት የተቀሰቀሰና የተለወጠ መሆን አለበት፤ ያለበለዚያ ደረቅና ምውት ትምህርት ከመጠበቅ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ምሥጢርን ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚቻለው ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ በሰጠውና ሁልጊዜም በመካከላችን በሚኖረው በክርስቶስ በተገለጠው በአብ ዘላለማዊ የፍቅር ብርሃን ብቻ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ዓይኔን የብዙ የፍቅር ታሪኮች ማእከል ወደ ሆነው ወደ ሕያው ክርስቶስ ለመመለስና በዓለም ቤተሰቦች ሁሉ ላይ የመንፈስ እሳት እንዲወርድ ለመለመን እወዳለሁ፡፡

ይህ አጠር ያለ ምዕራፍ ቤተክርስቲያን ስለ ጋብቻና ቤተሰብ የምታስተምረውን ትምህርት ያጠቃልላል፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ፣ እምነታችን ስላሳየን ብርሃን የሲኖዶሱ አባቶች የተናገሩትን ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ እነርሱም ከኢየሱስ ምሳሌ በመነሣት ‹‹እርሱ የተዋወቃቸውን ወንዶችና ሴቶች እንዴት ባለ ፍቅርና ርኅራኄ ይመለከታቸው እንደ ነበር፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሲሰብክ ሳለ  የእነርሱን እርምጃዎች እንዴት ባለ እውነት፣ ትዕግሥትና ምሕረት ይከታተል እንደ ነበረ›› ገልጸዋል፡፡ እኛም የቤተሰብን ወንጌል ለመለማመድና ለማስተላለፍ ከፈለግን፣ ጌታ   ዛሬም ከእኛ ጋር ነው፡፡

ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ያድሳል፣ ይፈጽማል

ጋብቻን እንደ መጥፎ ነገር ከማየት በተቃራኒ፣ ‹‹እግዚአብሔር የፈጠረው ማንኛውም ነገር መልካም እንደሆነ›› (1 ጢሞ. 4፡4) አዲስ ኪዳን ያስተምራል፡፡ ጋብቻ የጌታ ‹‹ስጦታ›› ነው (1 ቆሮ. 7፡7)፡፡ ከዚህም አዎንታዊ ግንዛቤ በመነሣት፣ አዲስ ኪዳን የእግዚአብሔርን ስጦታ የመጠበቅን አስፈላጊነት በአጽንኦት ያስረዳል፡-  ‹‹ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን›› (ዕብ. 13፡4)፡፡ ይህ መለኮታዊ ስጦታ ወሲባዊነትንም ያካትታል፡- ‹‹እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ›› (1 ቆሮ. 7፡ 5)፡፡

የሲኖዶሱ አባቶች እንዳመለከቱት፣ ኢየሱስ ‹‹እግዚአብሔር ስለ ወንድና ሴት ያለውን ዕቅድ አስመልክቶ ሲናገር፣ በሁለቱም መካከል ያለው ኅብረት የማይፈርስ መሆኑን አረጋግጦአል፤ እንዲያውም ‹ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም› (ማቴ. 19፡ 8) አለ፡፡ ጋብቻ የማይፈርስ መሆኑ፣ ‹ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው› (ማቴ. 19፡6) መባሉ፣ በሰው ላይ እንደ ተጫነ ቀንበር ሳይሆን፣ በጋብቻ ለተጣመሩ የተሰጠ ‹ስጦታ›› እንደ ሆነ መቆጠር አለበት፡፡… የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር ሁልጊዜ በሰብአዊ ጉዞአችን አይለየንም፣ እርሱ በጸጋው እልኸኛ ልብን ይፈውሳል፣ ይለውጣል፣ በመስቀል መንገድ ወደ መጀመሪያው አkሙ ይመልሰዋል፡፡ አራቱ ወንጌላውያን ጋብቻ የእግዚአብሔርን የመጀመሪያ ዕቅድ የሚያድስ የመገለጥ ሙላት የሆነውን የጋብቻን ትርጉም ያወጀውን … የኢየሱስን ምሳሌ በግልጽ አሳይተዋል (ንጽ. ማቴ. 19፡3)›› ፡፡

‹‹ሁሉንም ነገር ከራሱ ጋር ያስታረቀው ኢየሱስ ጋብቻንና ቤተሰብን ወደ መጀመሪያ መልካቸው መለሳቸው (ንጽ. ማቴ. 10፡ 1-12)፡፡ ጋብቻና ቤተሰብ በክርስቶስ ተበዥተዋል (ንጽ. ኤፌ. 5፡ 21-32)፣ እውነተኛ ፍቅር ሁሉ በሚፈልቅበት በቅድስት ሥላሴ ምሥጢር መልክ ታድሰዋል፡፡ በፍጥረት የተጀመረውና በድኅነት ታሪክ የተገለጸው የተክሊል ቃል ኪዳን ሙሉ ትርጉሙን የሚያገኘው በክርስቶስና በቤተክርስቲያኑ ነው፡፡ ክርስቶስ በቤተክርስቲያኑ አማካይነት፣ ለጋብቻና ለቤተሰብ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመመስከርና የሱታፌ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ጸጋ ይሰጣቸዋል፡፡ የቤተሰብ ወንጌል፣ ወንድና ሴት በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ከተፈጠሩበት ጊዜ አንሥቶ  በዘመን መጨረሻ በበጉ ጋብቻ በክርስቶስ የቃል ኪዳን ምሥጢር እስኪፈጸም ድረስ፣ በመላው ዓለም ታሪክ ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል (ንጽ. ራእይ 19፡9)›› ፡፡

የኢየሱስ ምሳሌ ለቤተሰብ

ክርስቲያን መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል፡፡… እርሱ ይፋ አገልግሎቱን የጀመረው በቃና ዘገሊላ በተካሄደ የሰርግ በዓል ላይ ባደረገው ተአምር ነው (ንጽ. ዮሐ. 2፡ 1-11)፡፡ የየዕለት ወዳጅነቱን ከአልአዛርና ከእህቶቹ (ንጽ. ሉቃ. 10፡38) እንዲሁም ከጴጥሮስ ቤተሰብ ጋር አሳለፈ (ንጽ. ማር. 8፡14)፡፡ ለሚያለቅሱ ወላጆች ራራላቸው፣ ልጆቻቸውንም ከሞት አስነሣላቸው (ንጽ. ማር. 5፡41፤ሉቃ.7፡14-15)፡፡ በዚህ ዐይነት የኪዳን ተሐድሶ የሚያካትተውን እውነተኛ የምሕረት ትርጉም አሳየ (ንጽ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ዲቨስ እን ሚዜሪኮርዲያ፣ 4)፡፡ ይህንንም ከሳምራዊት ሴት  (ንጽ. ዮሐ. 1፡ 14-30 ) እና በምንዝር ከተያዘችው ሴት ጋር  (ንጽ. ዮሐ. 8፡ 1-11) ካደረጋቸው ጭውውቶችና በዚሁ ወቅት በኢየሱስ ነፃ ፍቅር የተነሣ ሴቶቹ ኃጢአተኞች መሆናቸውን እንዲረዱ ሕሊናቸው ቀሰቀሰ››፡፡

በቤተልሔም ቤተሰብ ውስጥ የቃል ሥጋ መሆን፣ በባሕርዩ የዓለምን ታሪክ ለወጠ፡፡ እኛም ወደ ኢየሱስ ልደት ምሥጢር፣ ቃሉ በማሕጸንዋ ውስጥ በተፀነሰ ጊዜ ማርያም ለመልአኩ መልእክት ወደ ሰጠችው ‹‹እሽታ››፣ እንዲሁም ለኢየሱስ ስም ያወጣለትና ማርያምን የተንከባከባት ዮሴፍ ወደገለጸው ‹‹አዎን›› መግባት አለብን፡፡ እረኞች በከብቶች በረት አጠገብ የተሰማቸውን ሐሤት፣ የሰብአ ሰገልን ስግደትና ኢየሱስ ከወገኖቹ ጋር ስደትን፣ መከራንና ውርደትን የተካፈለበትን ወደ ግብጽ የተደረገ ስደት እናሰላስል፡፡  የዘካርያስን መንፈሳዊ ተስፋና እርሱም መጥምቁ ዮሐንስ በተወለደ ጊዜ የተሰማውን ደስታ፣ በቤተመቅደስ ለስምዖንና ለሐና የተፈጸመውን የተስፋ ቃል፣ የሕጻኑን የኢየሱስን ጥበብ የሰሙ የሕግ መምህራን የተሰማቸውን ግርምት እናሰላስል፡፡ ከዚያም ኢየሱስ በእጁ እየሠራ የተዳደረባቸውን፣ የአበው እምነት በመንግሥቱ ምሥጢር ፍሬ እስከሚያፈራ ድረስ  የወገኖቹን እምነት አውቆ የእምነቱንም መገለጫዎችና  መደበኛ ጸሎቶች የደገመባቸውን እነዚያን ሠላሳ ዓመታት እናስታውስ፡፡ የቤተሰብን የሕይወት ውበት የሚያንጸባርቅ የኢየሱስ ልደት ምሥጢርና የናዝሬት ምሥጢር ይህ ነው፡፡ የአሲዚውን የፍራንቸስኮስን፣ የሕጻኑ ኢየሱስ ቴሬዛንና የቻርልስ ደ ፉኮን ትኩረት የሳበውና ክርስቲያን ቤተሰቦችን በተስፋና በሐሤት መሙላቱን የማያkርጠው ምሥጢር ይህ ነው፡፡

"የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ የኖረበት የፍቅርና የታማኝነት ቃል ኪዳን፣ እያንዳንዱን ቤተሰብ የሚቀርጸውንና የሕይወትና የታሪክ ውጣ ውረዶችን በተሻለ መልኩ እንዲሁም የሚያስችለውን መርሆ ያሳያል፡፡ ከዚህም በመነሣት፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ ድክመት ቢኖርበትም እንኳ፣ በዓለም ጨለማ ውስጥ ብርሃን ሊሆን ይችላል፡፡ ‹ናዝሬት የቤተሰብ ሕይወትን ትርጉም፣ የፍቅር ሱታፌውን፣ ቀላልና ምቾት የለሽ ውበቱን፣ የተቀደሰና የማይጣስ ባሕርዩን ያስተምረናል፡፡ የእርሱ ትምህርት ምን ያህል ጣፋጭና የማይተካ፣ በማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ ደግሞ  ሚናው ምን ያህል መሠረታዊና ወደር የሌለው እንደ ሆነ ያስተምረን› (ጳውሎስ 6ኛ፣ በናዝሬት የተደረገ ንግግር፣ እ.አ.አ. ጥር 5፣ 1964)"፡፡

ምንጭ፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 57-64 ላይ የተወሰደ መሆኑን እንገልጻለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

23 September 2023, 17:38