ፈልግ

ካናዳ ውስጥ የሚገኙ የአገሩ ነባር ተወላጆች ካናዳ ውስጥ የሚገኙ የአገሩ ነባር ተወላጆች   (AFP or licensors)

አቡነ ፖይሰን፥ በካናዳ ከነባር ተወላጆች ጋር የሚደረግ የእርቅ ሂደት በፍሬያማነት መቀጠሉን አስታወቁ

በካናዳ ከአገሬው ነባር ተወላጆች ጋር ወደ እርቅ ለመድረስ እየተደረገ ያለው ረጅም ጥረት ጠቃሚ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑን የካናዳ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ራይሞንድ ፓይሰን አስታወቁ። አቡነ ፓይሰን ይህን ያስታወቁት የጳጳሳቱ ጉባኤ በኦንታሪዮ ግዛት ኪንግ ከተማ ባደረገው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካናዳ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በኦንታርዮ ክፍለ ሀገር ባካሄዱት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ውይይት ካደረጉባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹ፥ በአገሪቱ እየተስፋፋ በመጣው “ኤውታናሲያ” ወይም ነፍስን በህክምና ድጋፍ በፈቃድ ማጥፋት፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ከጥቃት መከላከል፣ በመጪው የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ውይይት ስለሚደረግበ ሲኖዶሳዊነት እና የካናዳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በባሕር ማዶ በምታበረክታቸው የልማት ድጋፎች ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

የካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ራይሞንድ ፓይሰን ሰኞ መስከረም 14/2016 ዓ. ም. ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ ከካናዳ ነባር ተወላጆች ጋር በተለይም የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስመልከት እየተካሄደ ባለው የእርቅ ሂደት እና በቅርቡ በሮም የሚካሄደውን የሲኖዶስ 16ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በማስመልከት ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

ከአገሬው ነባር ተወላጆች ጋር መተማመን ያለበት ዘላቂ ግንኙነት ማጠናከር

አቡነ ፖይሰን ለጉባኤው ባደረጉት የመጀመሪያ ነጥብ ንግግራቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ ወር 2022 ዓ. ም. በካናዳ ባደረጉት የይቅርታ ጥያቄ ሐዋርያዊ ንግደት መሠረት በማድረግ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲደረግ የቆየው የእርቅ ጥረት ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁመው፣ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ንግደታቸው ወቅት የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ለአገሬው ነባር ተወላጆች በግል እና በቡድን ሆነው በሚያበረክቷቸው ሐዋርያዊ አገልግሎቶች መካከል አዲስ ተነሳሽነትን እንዲያሳዩ ማበረታታቸው ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በተለይም በጉጉት የተጠበቁት እና በእርቅ ላይ ያተኮሩ አራት የብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክቶች ለአገሬው ቀደምት ነዋሪዎች ማለትም ለኢኑይት እና ለሜቲስ ሕዝቦች እንዲሁም በካናዳ ለሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይፋ መሆናቸውን አቡነ ፖይሰን አስታውሰው፥ ይህም ለሚቀጥሉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ነባር ተወላጆቹ ጋር መተማመን ያለበት ግንኙነትን ለማጠናከር ማዕቀፍ ሆኖ እንደሚያገለግል ያላቸውን እምነት ገልጸዋ።

ለአገሬው ነባር ተወላጆች የተደረገ 11 ሚሊዮን ዶላር የእርቅ ድጋፍ

የካናዳ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የእርቅ ጥረትን ለመደገፍ በሚል ዓላማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. ባቋቋመው የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩል እስካሁን 11 ሚሊየን የካናዳ ዶላር መሰብሰቡን ብጹዕ አቡነ ፖይሰን ገልጸው፥ ይህም ብጹዓን ጳጳሳቱ ከሁለት ዓመት በፊት 30 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ቃል የገቡት የአምስት ዓመት ዕቅድ አካል መሆኑን አስረድተዋል። አቡነ ፖይሰን አክለውም፥ “የበለጠ አበረታች የሆነው፥ ከሀገረ ስብከቶች ድጋፍን በማግኘት በአገር ውስጥ ተወላጆች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የሚያሳዩት የፍስሃ ፍሬ ነው” ብለዋል ።

በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሥርዓት መሠረት ጉዳት ከደረሰባቸው ጋር የተጀመረውን የእርቅ ሂደት የሚያግዝ ሌላ አዲስ ድጋፍ የማሰባሰብ መመሪያ በካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል ዘንድሮ መውጣቱን ብጹዕ ፖይሰን ገልጸው፥ ይህም ካናዳ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ከነባር ተወላጆች ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ይፋ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የራሳቸውን ፖሊሲዎች በሀገረ ስብከቱ ማኅደር ውስጥ እንዲያዘጋጁ ለመርዳት እንደሆነ አስረድተዋል።

ቫቲካን 'የግኝት ዶክትሪን' ውድቅ ማድረጓ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና የሰው ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በጋራ የሰጡትን ወሳኝ መግለጫ ያስታወሱት የካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ፖይሰን፥ አውሮፓውያኑ የአገሬው ነባር ተወላጆች ባሕል እና አስተዳደር ለማጥፋት ለዘመናት እንደ ምክንያት ይጠቀሙበት የነበረውን “የግኝት ዶክትሪን” ውድቅ ማድረጋቸውን ገልጸው፥ በዚህ ረገድም ትሩፋቱም የአካዳሚክ ሲምፖዚየም ርዕሠ ጉዳይ እንደሚሆን ግምታቸውን ተናግረዋል።

ብጹዕ አቡነ ፖይሰን በመጨረሻም፥ በዚህ የፈውስ እና የእርቅ ሂደት ወቅት ቁልፍ ቃል ‘ማጀብ’ የሚል እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው፥ "ከእኛ ጋር በኅብረት መጓዝ ለሚፈልጉ እንደ ክርስቲያን እና እንደ ሐዋርያዊ እረኞች ልናቀርብ የምንችለው ርኅራኄ እና የጸሎት ድጋፍ ነው” ብለው፥  ይህ ጉዞ በእውነተኛ ነፃነት እና በዘላቂ ተስፋ እንዲጠናቀቅ፥ ዛሬ ለተጎዱት ብቻ ሳይሆን ለመጭው ወጣት ትውልድም እንደሚሆን አስረድተዋል።

በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚወያይ መጪው የሲኖዶስ ጉባኤ

የካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ፖይሰን በሪፖርቱ መጨረሻ ላይ፥ በሮም የሚካሄደውን 16ኛው የሲኖዶስ ጉባኤ በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ ጉባኤውን አራት የካናዳ ብጹዓን ጳጳሳት እና በቫቲካን የተመረጡ ጳጳስ ያልሆኑ ሌሎች አራት ካቶሊኮች እንደሚካፈሉት በመግለጽ፥   ስምንቱ ልዑካን ወደ ሮም ለመጓዝ በሚዘጋጁበት በዚህ ወቅት፥ ለቤተ ክርስቲያን እና ለምእመናን የሚጠቅም ሃሳብ በጥበብ እና በማስተዋል እንዲያበረክቱ በጸሎት መደገፍ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

“ኤውታናሲያ” እና የልጆች ጥበቃ ከመወያያ ርዕሶች መካከል ናቸው

የካናዳ ብጹዓት ጳጳሳት እስከ መስከረም 17/2016 ዓ. ም. ድረስ በሚያደርጉት ብስብሰባ ላይ ትኩረት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 የጸደቀው እና በሕክምና እርዳታ ነፍስን የማጥፋት “ኤውታናሲያ” ሕጋዊነት እንዲራዘም የተደረገውን ክለሳ በማስመልከት ውይይት አካሂደዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 2024 ዓ. ም. ሥራ ላይ እንደሚውል የሚጠበቀው ይህ ሕግ በብዙ ሰዎች ላይ የአእምሮ ሕመምን እንዳስከተለ ጳጳሳቱ ተናግረው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 እና 2021 መካከል ከ30,000 በሚበልጡ ካናዳውያን አዕምሮ ውስጥ የሞት ስሜት እንዲጨምር ማድረጉን ጳጳሳቱ ገልጸዋል።

ይህን ርዕሠ ጉዳይ በተመለከተ በጳጳሳቱ ጉባኤ ውስጥ በሊቀ ጳጳስ አቡነ ክርስቲያን ሌፔን የሚመራ የቤተሰብ እና የሕይወት ቋሚ ኮሚቴ፥ ከ ‘ኤውታናሲያ’ ይልቅ አስቸኳይ የማስታገሻ እንክብካቤን ለማስፋፋት የሚያግዝ የፓናል ውይይት አዘጋጅቶ እንደ ነበር ታውቋል።

 

28 September 2023, 14:00