ፈልግ

መስቀል መዳኛችን ነው መስቀል መዳኛችን ነው  (ANSA)

የመስቀል ክብረ በዓል

የመስቀል በዓል በዓመት ሁለትጊዜ ይከበራል፤ አንደኛው በመስከረመ 17 ቀን የሚከበር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መጋቢት 10 ቀን ይከበራል፡፡ ይህ ሁለተኛው በዓል ተረክቦተ መስቀል ይባላል፡፡ ዕፀ መስቀል በንግሥት እሌኒ ትጋት በኢየሩሳሌም እንደተገኘ በታሪክ ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያው በዓል መስቀል ክቡር ይባላል፡፡ ዕፀ መስቀልን ከወሰዱት አረማውያን እጅ ወደ ክርስቲያኖች እጅ እንደተመለሰ ከታሪክ ማህደር ይታወሳል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በተለይ ግን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዕፀ መስቀል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን ሲገባ ሕዝባችን በታላቅ ክብርና ሥነ-ሥርዓት እንደተቀበለው የሚተወስ በዓል ነው፡፡ «ዮም መስቀል ተሰብሐ ለአኃው አብርሃ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ፡- ዛሬ መስቀል ከበረ፣ ለወንድሞች አበራ፣ ቤዛችን፣ ኃይላችንና የነፍሳችን መድኃኒት፡፡

የመስቀል በዓል የደኀንነታችንን ታሪክ ያሳስበናል፣ ስለእኛ የሞተውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስታውሰናል፡፡ ደኀንነታችን በመስቀል ነው የተገኘው፡፡ ጌታችን ከኃጢአት ሊያድነን ሲፈልግ በሌላ ቀለል ያለ መንገድ ከሚያድነን ይልቅ በባርነት ከውርደትና ስቀይ በተሞላበት መንገድ በመስቀል አዳነን፡፡ በፍቅራችን ተስቦ መለኮታዊ ማዕረጉን ተገፎ፣ ውርደትና ድህነትን ተቀብሎ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ደሙን አፈሰሰ፣ ስለ ኃጢአታችን ካሣ ተላልፎ (ተሰጠ)፡፡

መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በእንጨት መስቀል ተሰቅሎ ሕይወቱን ለሰማያዊ አባቱ ከሰዋ በኋላ እኛ ከሰይጣን ባርነት ነጻ ወጥተናል፡፡ የመንፈስ ነጻነትን ተጐናጽፈናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ ለመሸጋገር አብቅቶናል፡፡ በመስቀል ለመንፈሳችን የሚያስፈልግ ሰማያዋ ተስፋ፣ ደስታ፣ ሰላምና ኃይል መጣለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመስቀል ስለተገኙ ፍሬዎች፣ ደህንነትና ሌሎችም ጸጋዎች እያሰበ «ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ ይል ነበር፡፡ 

እኛም እንዲህ ብለን እንመስክር፣ ምክንያቱም መስቀል ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እንመኘው የነበረ ደህንነታችንን አምጥቶልናል፤ መንፈሳዊ ሀብትና ክብር ሰጥቶናል፡፡ ይኸውም በፍጹም የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው፡፡ በመንፈሳችን ተደስተን «ክርስቶስ ሆይ በተቀደሰ መስቀልህ ዓለምን ያዳንክ አንተ ነህና እንሰግድልሃለን፣ እናመሰግንህማለንእያልን ኢየሱስን እናመስግነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም ስለሚወደን ከባድ በሆነ ብርቱ ሥቃይ ሊያድነን ፈለገ፡፡ እርሱ ቅዱስ ሕይወቱን አሳልፎ እስኪሰጠን ከመጠን በላይ እንደወደደን እኛም እምንወደው ከሆንን መስቀሉን ተሸክመን እርሱን መከተል አለብን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ በመስቀል ላይ ከመስቀሉ በፊት «ከጌታ አካላት ክፍል ክብር የተቀበልክ ጣፋጭ መስቀል ሆይ፣ ክቡርና ብሩህ ዛብ፣ በንጉሥ ካባ የተሸለምክ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን እያለ ሊያሰቃው ተዘጋጅቶ የነበረውን ዕፀ መስቀል በደስታ ተቀበለው፡፡    

እኛም በሕይወታችን የሚገጥመንን መስቀል እንደዚህ ባለ የእምነት መንፈስ ልንቀበለው ይገባናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ «ሊከተለኝ የሚወድ ሁሉ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ(6) ይለናል፡፡ በእውነት የእርሱ ተከታዮች ከሆንን መስቀሉን ተሸክመን ልንከተለውና በመስቀል መንገድ የማለፍ የእምነት ግዴታ አለብን፡፡ አለበለዚያ ግን የእርሱ አይደለንም፡፡ መዳን ቀላል እንዳልሆነ እንገንዘብ፡፡ ሕይወታችን ጨለማ፣ ስቃይ፣ መከራ የሞላበትና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ከተሰማን የክርስቶስን መስቀል እናስብ ያን ጊዜ ብርሃንና ኃይልን እናገኛለን፡፡ በክርስቶስ መስቀል ፈተናን ለማሸነፍ የሚረዳን በጽድቅ መንገድ የሚመራን ጸጋ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ዘወትር በጋለ መንፈስ መስቀሉን እናስብ የዘለዓለማዊ ሕይወትና ቀጥተኛ መንገድም ይህ ብቻ ነው፡፡

 

28 September 2023, 10:40