“ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ ፍቅር ይቅር ይላል”
በልባችን ውስጥ ክፉ ፈቃድ ሥር እንዲሰድ ካደረግን፥ ወደ ጥልቅ ቅሬታ ሊወስደን ይችላል። ፍቅር “በደልን አይቆጥርም፣ አይናደድም።” የንዴት ተቃራኒ የሌሎች ሰዎችን ድክመቶች ለመረዳትና እነርሱንም ይቅር ለማለት በሚሻ አዎንታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ይቅርታ ነው። ኢየሱስ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃ. 23፡ 34) አለ። እኛ ግን ትልልቅ ክፋትን እያሰብን፥ ማናቸውንም ክፋት እያሰላሰልንና ስሕተቶችን ይበልጥ እየፈለግን ስንሄድ፥ ንዴት እየጨመረና ሥር እየሰደደ ይሄዳል። ስለዚህ በባል ወይም በሚስት በኩል የሚፈጸም ማንኛውም ስሕተት ወይም ጥፋት የፍቅር ግንኙነትንና የቤተሰብ መረጋጋትን ሊጎዳው ይችላል። ሁሉም ችግር እኩል መስሎ ሲታየን አንድ ከበድ ያለ ችግር አለ ማለት ነው። በዚህ ዓይነት በሌሎች ድክመት ላይ አላስፈላጊ ጭካኔ ወደማሳየት ሥጋት ውስጥ ልንገባ እንችላለን። መብቶቻችን እንዲከበሩ ያለን ተገቢ ምኞት ክብራችንን በአግባቡ በማስጠበቅ ፈንታ ወደ ቂም በቀል ጥማት ይለወጣል።
ስንበደል ወይም ችላ ስንባል ይቅር ማለት ይቻላል፤ አስፈላጊም ነው። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ቀላል ነው የሚል ማንም ሰው የለም። በእውነቱ “የቤተሰብ አንድነት የሚጠበቀውና የሚጠራው በታላቅ የመሥዋዕትነት መንፈስ ነው። በመሠረቱ ለመረዳት፣ ለመታገስ፣ ይቅር ለማለትና ዕርቅ ለማውረድ የእያንዳንዱንና የሁሉንም ሰው ዝግጁነትና ለጋስ ግልጽነት ይጠይቃል። ራስን ብቻ መውደድ፣ አለመስማማት፣ ውጥረትና ግጭት የራሱን ኅብረት በኃይል እንደሚያጠቃና አልፎ አልፎም ክፉኛ እንደሚያቆስል፥ በዚህም ሳቢያ በቤተሰብ ውስጥ በርካታና የተለያዩ የክፍፍል ዓይነቶች እንደሚፈጠሩ የማያውቅ ቤተሰብ የለም”።
ዛሬ ሌሎች ሰዎችን ይቅር ማለት መቻል ራሳችንን የመረዳትና ይቅር የማለት አስደሳች ልምድ እንደሆነ እንገነዘባለን። ብዙውን ጊዜ ስሕተታችን ወይም ከምንወዳቸው ሰዎች የሚደርስብን ነቀፌታ በራስ መተማመናችንን ሊያሳጣን ይችላል። በመሆኑም ከሌሎች ሰዎች እንርቃለን፤ መወደድን ልንጠላና የእርስ በርሳችንን ግንኙነቶች ልንፈራ እንችላለን። ሌሎችን መውቀስ ያላግባብ ያስደስተናል። ስለዚህ ባለፈው ታሪካችን ላይ መጸለይን፣ ራሳችንን መቀበልን፣ ከነድክመታችን መኖርን እንዲሁም ለሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ይኖረን ዘንድ ራሳችንንም ይቅር ማለትን መማር ያስፈልገናል።
ይህ ሁሉ የሚያሳየው እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር ይቅር መባላችንን፣ በራሳችን በጎ ምግባር ሳይሆን በጸጋው መጽደቃችንን ነው። ከራሳችን ጥረት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውን፣ ሁልጊዜ በሮችን የሚከፍተውን፣ የሚያሳድገውንና የሚያበረታታውን ፍቅር አውቀናል። የእግዚአብሔር ፍቅር በነጻ የተሰጠ መሆኑን፣ የአብ ፍቅር በገንዘብ ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንደማይችል አምነን ከተቀበልን፥ እኛም ቢበድሉን እንኳ ለሌሎች ሰዎች ገደብ የሌለው ፍቅር ልናሳይና ይቅር ልንላቸው እንችላለን። ያለበለዚያ የቤተሰብ ሕይወታችን ከእንግዲህ የመግባባት፣ የመደጋገፍና የመጽናናት ሥፍራ መሆኑ ቀርቶ የማያቋርጥ ውጥረትና እርስ በርስ የመነቃቀፍ ቦታ ይሆናል።
ፍቅር ከሌሎች ጋር ይደሰታል
በሰዎች ክፉ መደሰት በሰው ልብ ውስጥ የመሸገ አሉታዊ ስሜት ነው። በሌሎች ሰዎች ላይ በደረሰ በደል የሚደሰቱ ሰዎች ያላቸው መርዘኛ አስተሳሰብ ነው። “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል” የሚለው አገላለጽ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። በሌላ አነጋገር፥ እኛ በሌሎች በጎ የምንደሰተው ክብራቸውን ስናይና ለችሎታቸውና መልካም ሥራዎቻቸው ዋጋ ስንሰጥ ነው። ሁልጊዜ ሰውን ከሰው ለሚያወዳድሩና ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር እንኳ ለሚፎካከሩ ይህን ማድረግ ስለማይሆንላቸው በሌሎች ውድቀት በስውር ደስ ይላቸዋል።
አፍቃሪ ሰዎች ለሌሎች በጎ ሲያደርጉ ወይም ሌሎች ሲደሰቱ ሲያዩ፥ እነርሱ ራሳቸው ደግሞ በደስታ ይኖራሉ። በዚህም መንገድ ለእግዚአብሔር ክብርን ይሰጣሉ። ምክንያቱም፥ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳልና” (2 ቆሮ. 9፡7)። ጌታችን በተለይ በሌሎች ደስታ ሐሤት የሚያደርጉ ሰዎችን ይወዳል። በሌሎች በጎ መደሰትን ካላወቅንና በራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ ብናተኩር፥ ራሳችንን ለደስታ አልባ ሕይወት እንዳርጋለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንዳለው፥ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” (የሐዋ. 20፡ 35)። ስለዚህ ቤተሰብ ከአባላቱ አንዳቸው መልካም ነገር በሚገጥመው ጊዜ ሁሉ ሌሎችም አብረው እንደሚደሰቱ የሚያውቁበት ቦታ መሆን አለበት።
ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል
ጳውሎስ ስለ ፍቅር ያቀረበውን ዝርዝር “ሁሉ” በሚሉ አራት ስንኞች ያጠቃልላል። ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። እዚህ ላይ የሚያሰጋውን ነገር ሁሉ መቋቋም የሚችለውን የፍቅርን ፀረ ባህላዊ ኃይል እናያለን።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው፥ “ፍቅር ሁሉን ይታገሣል” ይህም ክፋትን መቋቋም ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው። አንደበትን ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው። ግሡ ከሌላው ሰው በደል ጋር በተያያዘ “የራስን ሰላም መጠበቅ” ሊባል ይችላል። ፍርድ ከመስጠት መቆጠብን፣ ብርቱና ጨካኝ የውግዘት ስሜት መቆጣጠርን ያመለክታል። “አትፍረዱ፣ አይፈረድባችሁም” (ሉቃ. 6፡ 37)። በተለምዶ አንደበታችንን ከምንጠቀምበት ሁኔታ በተቃራኒ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ወንድሞችና እህቶች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ” (ያዕ. 4፡ 11) ይለናል። ሌላውን ሰው መወንጀል፣ ራሳችንን ንጹሕ የማድረጊያና ስለምናደርሰው ጉዳት ግድ ሳይኖረን ቅሬታንና ቅናትን መተንፈሻ መንገድ ይሆናል። ሐሜት ኃጢአት መሆኑን ብዙውን ጊዜ እንዘነጋለን፤ የሌላውን ሰው መልካም ስም ክፉኛ የሚጎዳና ያንን ስም ማደስ የማያስችል ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመ ከባድ በደል ይሆናል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚያትተው፥ “ምላስ የክፋት ዓለም ናት፣ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች” (ያዕ. 3፡ 6)፤ “የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት” (ያዕ. 3፡ 8)። “ምላስ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች ለመርገም” (ያዕ. 3፡ 9) ስታገለግል ፍቅር ደግሞ የሌሎችን፣ የጠላቶችን ጭምር መልካም ስም ይጠብቃል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጠበቅ ስንሻ ይህን የፍቅርን ልዩ ትእዛዝ ከቶ መርሳት የለብንም።
በፍቅር የተሳሰሩ ጥንዶች ስለ እርስ በርሳቸው በጎ ይነጋገራሉ። የአጋራቸውን ድክመትና ስሕተት ሳይሆን በጎ ጎኑን ለማሳየት ይጥራሉ። በማናቸውም ወቅት ስለ እርስ በርሳቸው ክፉ በመናገር ፈንታ ዝም ይላሉ። ይህም በሌሎች ሰዎች ፊት ብቻ የሚደረግ አይደለም። ከውስጣዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ድርጊት ነው። በብልጠት “የሌሎችን ችግሮችና ድክመቶች አናይም” ከማለት ይልቅ እነዚያን ድክመቶችና ስሕተቶች ሰፋ ባለ አገባብ ማየትና እነዚህ ድክመቶች የትልቁ ሥዕል አካል መሆናቸውን መገንዘብ ነው። ሁላችንም የብርሃንና የጨለማ ውስብስብ ድብልቅ መሆናችንን መገንዘብ አለብን። ሌላው ሰው እኔን ከሚያናድዱ ጥቃቅን ነገሮች ድምር ውጤት ይበልጥብኛል። ዋጋ እንሰጠው ዘንድ ፍቅር የግድ ፍጹም መሆን የለበትም። ሌሎች ሰዎች የተቻላቸውን ያህል ከነድክመታቸውና ዓለማዊነታቸው ይወዱኛል። ፍቅር ፍጹም አለመሆኑ ግን ሐሰት ነው ወይም እውነት አይደለም ማለት አይደለም። ውስንና ዓለማዊ ቢሆንም እውነት ነው። እኔ ብዙ ነገር የምጠብቅ ከሆነ ሌላው ሰው ይህ እንዳይሆን ይነግረኛል። ምክንያቱም እርሱ እንደ እግዚአብሔር ሊሆንልኝ ወይም ፍላጎቴን ሁሉ ሊያሟላልኝ አይችልም። ፍቅር ከጉድለት ጋር አብሮ ይኖራል። “ሁሉን ይታገሣል”፤ ሰላሙንም ከሚወዱት ሰው ጉድለት ያስቀድማል።
ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ፥ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 104-112 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ