ፈልግ

ፓትርያርክ ፒዛባላ - የፋይል ፎቶ ፓትርያርክ ፒዛባላ - የፋይል ፎቶ  (REUTERS)

ፓትርያርክ ፒዛባላ ታጋቾችን መልቀቅ ወደ ጦርነቱ መጨረሻ የሚወስደን 'የመጀመሪያ ደረጃ' ነው አሉ

ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ሃማስ የተወሰኑ ታጋቾችን መልቀቁን እና የእስራኤል የፍልስጤም እስረኞችን መልቀቅ በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ያለው ጦርነት ማብቂያ ላይ እንደ አንድ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ሲሉ ካደነቁ በኋላ፥ ለጋዛ ሠላም በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እንዲድረግ እና አዲስ የፖለቲካ አመለካከቶች እንዲኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በርካታ ታጋቾችን መልቀቅ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል እየተካሄደ ላለው ጦርነት ማብቂያ የመጀመሪያ እርምጃ መሆኑን የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት የምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀው ሰሞኑን በተደረገው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ስለ ታጋቾች መለቀቅ እንዲሁም እስረኞች መፈታት አስመልክተው ምላሽ ሰጥተዋል ።

ጥያቄ፡- ሰሞኑን በተደረጉት ክንውኖች ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

መልስ፦ ከታጋቾች መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን ለማስለቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱ አወንታዊ እርምጃ ነው፥ ምክንያቱም እስካሁን ድረስ እንደ ብቸኛው አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃዎ ብቻ ነበሩ። ይልቁንም በዚህ መንገድ ውስጣዊም ሆነ ዓለማቀፋዊ ውጥረትን ለማርገብ የመጀመሪያ እርምጃ ተወስዷል። በተጨማሪም ከወታደራዊ መፍትሄዎች ይልቅ ሌሎች መፍትሄዎችን ተግባራዊ ማድረግ የምንጀምርበት መንገድ ነው፥ ግጭቱ እንዲያበቃ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ማለቴ ነው።

ጥያቄ፡- ስለ ታጋቾቹ መፈታት ዜና የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፥ የአብዛኛው በዜናው መደሰታቸው ነው የሚገልፁት። ግን አንዳንድ ተንታኞችም ድርድር መደረጉ በሆነ መንገድ ሽንፈትን ያመለክታል ይላሉ…

መልስ፦ እነዚህን “ጠመንጃ ነካሽ ፖለቲከኞች” ብለን እንጥራቸው፥ ምክንያቱም ሰላምን ሁሌ የሚያስቡት ከጦርነት ድል ጋር ብቻ እንደሆነ ነው። ነገር ግን ለግጭቱ መፍትሄ ሠላም ብቻውን ፍፁም ድል ሊሆን አይችልም። ይህ ሆኖም አያውቅም፥ ስለዚህም መፍትሄው በወታደራዊ እርምጃዎች ብቻ ሊተው እንደማይችል ግልጽ ነው።

ፖለቲካው ሁኔታውን መቆጣጠር እንዳለበት ግልጽ ነው፥ ከሁሉም በላይ የተለያዩ አመለካከቶችን ለሁሉም ያቀርባል፥ ምክንያቱም ወታደሩ እነዚህን ማቅረብ አይችልም፥ ስለዚህም ከዚህ ጦርነት በኋላ ለጋዛ የፖለቲካ አመለካከቶችን ለመጀመር ድርድር እና ታጋቾችን መልቀቅ የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። የሚያስፈልገውም ይህ ነው።

ጥያቄ፡- በሰሜናዊ የጋዛ ክፍል የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤቶቻቸው ለመመለስ እየሞከሩ እንደሆነ ዜና ሰምተናል። እኔ እንደማስበው አብዛኛዎች ቤቶች በጦርነቱ ወድመዋል፥ ይህ ምን ማለት ነው?

መልስ፦ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ የመሆን ዕድሉ አይኖርም። በርግጥ አንዳንዶች መመለስ ይፈልጋሉ፥ ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተጨናንቀው በሚኖሩበት በደቡብ ጋዛ መኖር ቀላል አይደለም። ስለዚህ ከዚያ መውጣት ይፈልጋሉ፥ ይሄንን በደንብ ተረድቻለሁ። በዚያች ትንሽዬ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚኖሩት ክርስትያኖቻችን እንኳን ይሄንን ሊቋቋሙት አይችሉም።

ነገር ግን ስለቀጣዮቹ አካሄዶች ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አመለካከቶች ወይም ግልጽነት እስከሌለ ድረስ ይህ አሁንም የማይቻል እና አደገኛም ሊሆን ይችላል።

ጥያቄ፡- ሽብርተኝነትን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል? የሐማስን ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?

መልስ፦ ቀላል አይደለም፥ ረጅም ጊዜ ቢወስድም ያንን ርዕዮተ ዓለም የሚመግብን ሁሉ ቀስ በቀስ፣ በትዕግስት ሥሮቹን ማስወገድ አለብን። ቅርንጫፎቹን መቁረጥ ምንም ፋይዳ የለውም ምክንያቱም እንደገና ሊያቆጠቁጡ ይችላሉና።

በመጀመሪያ ደረጃ ለፍልስጤማውያን አመለካከት ቦታ መስጠት አለብን። ይህንን ስል ብዙዎችን እንደማያስደስት አውቃለሁ፥ እስካሁን ያልተሰጣቸውን ሀገራዊ አመለካከት ሊሰጣቸው ይገባል።

ይህ ጦርነት ሁለቱ ህዝቦች አብረው ሊኖሩ እንደማይችሉ፥ ቢያንስ በአሁኑ ሰዓት እንደማይችሉ አንዱ ግልፅ ምስክር ነው። እስካሁን ከተደረጉት የበለጠ የተብራራ፣ ግልፅ የሆነ እና ትክክለኛ እይታ ሊኖራቸው ይገባል።

ከዚያም ሌላ እይታ አለ፥ ሐማስም ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ነው። ስለዚህ በጥላቻ ላይ ያልተማከለ ሃይማኖታዊ ውይይት ማዳበር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት በጣም አስፈላጊ ነው።

ጥያቄ፡- ምንም እንኳን ከእነዚያ ቦታዎች ርቀን የምንኖር ሰዎች ብንሆንም ፥ ግን ለነሱ ቅርበት እንዳለው ሰው፥ ምክንያቱም እነዚህ ቦታዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት ቦታዎች ናቸውና እንደ ክርስቲያን፣ አልፎም በአጠቃላይ እንደ ህዝብ ምን እናድርግ? በሕዝብ አስተያየት ደረጃ ምን ሊደረግ ይችላል?

መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ አማኞች በርትተው መጸለይ ይገባቸዋል፥ ይህ የመጀመሪያው ነገር ነው። ከዚያም ትክክለኛ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ሌላው መታየት ያለበት አስፈላጊ ገጽታ፥ በዓለም ላይ አንዱ በሌላው ላይ ጠንካራ የሆነ መከፋፈል መፈጠሩን አስተውያለሁ፥ በአንዴ ሁለቱንም ወገኖች መውደድ የማይቻል ይመስላል። እንደ ክርስቲያኖች አግላይ ባልሆነ መልኩ በንግግራችን ውስጥ ግልጽ መሆን አስፈላጊ ነው። እውነትን በመያዝ ነገሮችን በስማቸው መጥራት ይገባል፥ በተመሳሳይ ጊዜ ከሁሉም ጋር ግንኙነቶችን ክፍት ማድረግ እና ለሁሉም ማለትም ለሁለቱም ወገኖች እንደምንወዳቸው መንገር ያስፈልጋል።
 

27 Nov 2023, 12:47