ፈልግ

በፓተርሰን ሀገረ ስብከት ውስጥ ከሚገኙት የፔሩ ምዕመናን መካከል ጥቂቶቹ በፓተርሰን ሀገረ ስብከት ውስጥ ከሚገኙት የፔሩ ምዕመናን መካከል ጥቂቶቹ   (©Joe Gigli and Yoel Gonzalez, Diocese of Paterson)

ከፔሩ ውጭ የሚገኝ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ በር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ መመረጥ የተሰማውን ደስታ ገለጸ

ከላቲን አሜሪካዊቷ አገር ፔሩ ውጭ በተለይ በአሜሪካ ከተሞች ፓተርሰን እና ኒው ጀርሲ የሚገኙት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፔሩ ምዕመናን፥ በፔሩ ውስጥ ባገለገሉት አሜሪካዊው ተወላጅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጥ እጅግ መደሰታቸውን አባ ጄኖ ሲልቫ፥ የመጥምቁ ዮሐንስ ካቴድራል መሪ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአሜሪካ ፓተርሰን ኒው ጀርሲ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፔሩ ማኅበረሰብ እንደሚገኝ ሲነገር፥ የምዕመናን ማኅበረሰቡ በአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጥ የተሰማው ደስታ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። ምዕመናኑ በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኝ የሕጻናት መጫወቻም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ተሰይሞ አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል።

ይህን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የገለጹት፥ በፓተርሰን ሀገረ ስብከት የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ካቴድራል መሪ፣ የሀገረ ስብከቱ ልዩ ፕሮጄክቶች ረዳት አስተባባሪ እና በቫቲካን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተሿሚ የሆኑት አባ ጄኖ ሲልቫ ናቸው።

አባ ጄኖ ሲልቫ ከዜና አገልግሎቱ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፥ በፓተርሰን ሀገረ ስብከት የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፔሩ ማኅበረሰብ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጣቸውን ሲሰሙ እጅግ የተደሰቱ መሆናቸውን ተናግረው፥ በማከልም ከአሜሪካ እና ከቫቲካን ባንዲራዎች ጋር በካቴድራሉ መግቢያ ላይ ከቆመው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምስል ጋር ፎቶግራፍ በመነሳታቸው ደስታ እና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በፓተርሰን፣ ኒው ጀርሲ ግዛት ውስጥ ያለው ትልቁ የፔሩ ዲያስፖራ

በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘው የፓተርሰን ሀገረ ስብከት በዓለም ላይ ትልቁ የፔሩ ዲያስፖራ የሚኖርበት እንደሆነ አባ ጄኖ ሲልቫ ተናግረው፥ ​​የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ካቴድራል የሚገኘው ‘ትንሿ ሊማ’ ወይም ‘ትንሿ ፔሩ’ ተብላ ከምትታወቅ አካባቢ እንደሆነ አስረድተዋል።

ምዕመናኑ ምስጋናቸውን ለማቅረብ ወደ ካቴድራሉ እየመጡ ስለ ነበር፥ ድጋፍ እና ማበረታቻ እንዲሆናቸው በማለት ከፓተርሰን ጳጳስ አቡነ ኬቨን ስዌኒ ጋር በተለይም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምርጫን ምክንያት በማድረግ በዓሉን በመስዋዕተ ቅዳሴ ለማክበር መወሰናቸውን አባ ጄኖ ሲልቫ ተናግረዋል።

የፓተርሰን መኮንኖችም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል

ወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያረፉበት እና እረኛ እንደሌለው በጎች የተሰማንበት ነበር” ያሉት አባ ጄኖ ሲልቫ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አዲስ እረኛ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት በኩል የታዩበት መንገድ ትኅትና እና ቅድስና የታየበት አበረታች ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

በምርጫው ወቅት ከፓተርሰን ከተማ እና የአካባቢው መኮንኖች ቡድን ጋር እንደ ነበሩ የገለጹት አባ ጄኖ ሲልቫ፥ በዕለቱ ሁሉም መኮንኖች አንድ ላይ ሆነው ወደ ቢሯቸው መምጣታቸውን አስረድተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሰገነት ላይ ቆመው በጣሊያንኛ ቋንቋ ከተናገሩ በኋላ በስፓኒሽ ሲናገሩ ሁሉም መኮንኖች ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስም እንጠራዋለን”

አባ ጄኒ ሲልቫ በካቴድራሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ብቸኛው የሳር ቦታ፥ ልጆች በየቀኑ ጭቃ እና ድንጋይ እያመጡ የሚጫወቱበት እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን ወደ ፊት ገንዘብ በማሰባሰብ ልጆች የሚጫወቱበት ደህና ሥፍራ ለማድረግ ማሰባቸውን እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስም የሚጠራ የመጀመሪያው መጫወቻ ሥፍራ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

“ምዕመናን ካቶሊክ በመሆናቸው ኩራት ይሰማቸዋል”

ከፔሩ በመጣ አሜሪካዊ ማኅበረሰብ መካከል ማገልገል ታላቅ ኩራት እንደሆነ የገለጹት አባ ጄኖ ሲልቫ፥ “አሁን ደግሞ ከርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው ጋር ብዙ ግንኙነት ያለው መሆን አለበት” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ምርጫን ተከትሎ ምዕመናኑ በካቶሊካዊነታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው፥ “የዚህ ምስጢራዊ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆኔ እኔም እጅግ ክብር ይሰማኛል” ብለው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እስካሁን የተናገሩትን በመስማት በሁሉም መንገድ መመሰጣቸውን፥ በአሜሪካ ኒው ጀርሲ፥ በፓተርሰን ሀገረ ስብከት የሚገኝ የመጥምቁ ዮሐንስ ካቴድራል መሪ አባ ጄኖ ሲልቫ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

 

27 May 2025, 16:06