ግንቦት 14 ከምስራቅ አቢያተ ክርስቲያናት የወጡ ዘገባዎች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዚህ ሳምንት ከምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት የወጡ አንኳር ዜናዎች መካከል የኒቂያ ጉባኤ ከተካሄደ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ዓመት መሙላቱን አስመልክቶ ልዩ ዝግጅት መካሄዱ ተገልጿል።
የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የኒቂያ ጉባኤ 1700 ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል በቅድስት መንበር የተከበረ ሲሆን፥ እንደሚታወቀው በ 325 ዓ.ም. የተካሄደ የኒቂያ ጉባኤ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ የክርስቲያናዊ ህብረት ጉባኤ እንደሆነ ይታወቃል።
በዚህም ዓመት የመታሰቢያ በዓሉን አስመልክቶ በርካታ የክርስቲያናዊ ህብረት በዓላት እየተከበሩ የሚገኙ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ይህን በዓል ለማክበር፥ አሁን ላይ ቱርክ ተብላ የምትጠራውን ኒቂያ ከቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ጋር በጋራ ሆነው ሊጎበኙ አቅደው እንደነበር ይታወሳል።
ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ሊቀ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ ፓትርያርኩን በሮም ተቀብለው ያነጋገሯቸው ሲሆን፥ አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ ቱርክ ጉብኝት ለማድረግ እንዳሰቡም ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑድ ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ከዓለም ዙሪያ ከመጡ ምዕመናን፣ የልዩ ልዩ አገራት መሪዎች እና የቤተ እምነት ተወካዮች በተገኙት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት አገልግሎታቸውን የሚጀምሩበት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ የኒቂያ ጉባኤ 1,700 ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስታወስ፥ በክርስቲያኖች መካከል ያለው አንድነት በእምነት ውስጥ ያለው አንድነት ብቻ ሊሆን እንደማይችል አጽንዖት ሰጥተው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስነት ምርጫ የተካሄደው ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት ለማክበር በምትዘጋጅበት ወቅት እንደሆነ እና ይሄ ጉባኤ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች የሚጋሩትን የእምነት መግለጫ መሠረታዊ ደረጃን እንደሚወክል ገልጸው ነበር።
የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ር.ሊ.ጳ. ሊዮ 14ኛን መቀበላቸው
እሑድ፣ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በሮም በተካሄደው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሃዋሪያዊ ሥራ ማስጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከምሥራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ በርካታ ፓትርያርኮች እና ብጹአን ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን፥ ተሳታፊዎቹ ብጹእነታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራቸውን ህብረት እንደሚያስቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ አብዛኛዎቹም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሊባኖስ የሚያደርጉትን ጉብኝት በጉጉት እንደሚጠብቁ የተናገሩ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የላቲን ካቶሊኮች ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳስ ይሆናሉ በማለትም ገልጸዋል።
ሞንሲኞር ጎልኒሽ በአርሜኒያ
ከዚህም በተጨማሪ ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የሎቬር ዲ ኦሪየንት ድርጅት ማለትም ከ 160 ዓመታት በላይ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በምስራቅ አውሮፓ እና በህንድ እንዲሁም በአጠቃላይ በ 23 ሃገራት ውስጥ ለሚገኙ ምሥራቃውያን ክርስቲያኖችን እየረዳ የሚገኘው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሞንሲኞር ፓስካል ጎሊኒሽ በአርሜኒያ ከሚገኘው የሬቫን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ሲሆን፥ በኋላም በአርሜኒያ የፈረንሳይ አምባሳደር እና ከአርሜናዊው የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ጋር በመሆን በአርሜኒያ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ሃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኋላ፥ በሎቬር ዲኦሪየንት ስም የመታሰቢያ ሃውልቱ አከባቢ ዛፍ መትከላቸው ተገልጿል።
ሞንሲኞር ጎልኒሽ በመጨረሻም የዘር ማጥፋት ወንጀልን በጽኑ እንደሚያወግዙ በመግለጽ፥ ድርጅታቸው ለአርሜኒያ ህዝብ ያለውን የማያወላውል ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።