ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፥ "ሕጎችና ክፉውንና ደጉን መለየት"
የግለሰብ ድርጊቶች ከአጠቃላይ ሕግ ወይም ደንብ ጋር ይጣጣማሉ ወይስ አይጣጣሙም ብሎ ማሰብ ነገሮችን አቅልሎ ማየት ይሆናል፣ ምክንያቱም በሰው ተጨባጭ ሕይወት ውስጥ ነገሮችን ለይቶ ለማወቅና ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆንን ለማረጋገጥ ይህ በቂ አይደለም። ስለዚህ የቅዱስ ቶማስ አኳይናስ አስተምህሮ ሁልጊዜ እንድናስታውስና በሐዋርያዊ እውቀታችን ውስጥ ማዋሃድን እንድንማር ከልብ አደራ እላለሁ። ‹‹ አጠቃላይ መርሆች አስፈላጊ ቢሆኑም፣ ወደ ነገሮች ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ ጠልቀን በገባን ቁጥር፣ የበለጡ ጉድለቶች ያጋጥሙናል።… ድርጊትን በተመለከተ እውነት ወይም ተግባራዊ ታማኝነት የሚሠራው ለሁሉም ዝርዝር ጉዳዮች ጭምር ሳይሆን ለአጠቃላይ መርሆች ነው። ለዝርዝር ጉዳዮች ያለው ታማኝነት በሁሉም ዘንድ እኩል አይታወቅም።… ወደ ዝርዝሩ ይበልጥ ጠልቀን ስንገባ መርሁ ይቀራል››። አጠቃላይ ደንቦች ከቶ ችላ የማይባል ወይም የማይተው በጎ ነገር ማስቀመጣቸው እውነት ቢሆንም፣ በአቀራረጻቸው ለልዩ ሁኔታዎች ሁሉ የተሟሉ ሊሆኑ አይችሉም።… ከዚሁ ጋርና በዚሁ ምክንያት፣ በአንድ የተወሰኑ ሁኔታዎች የተጨባጭ ግንዛቤ አካል የሆነውን ነገር ወደ ደንብ ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም። ይህም ትእግሥት ወደሚያሳጣ አከራካሪና ውስብስብ የሕግና የሞራል ምክንያታዊ አቀራረብ መምራት ብቻ ሳይሆን፣ በልዩ እንክብካቤ መጠበቅ የሚገባቸው እሴቶችንም አደጋ ላይ ይጥላል።
በዚህ ምክንያት፣ አንድ ጳጳስ ‹‹ሕጋዊ ባልሆኑ›› ሁኔታዎች ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ግብረ ገባዊ ሕጎችን መጠቀም ቀላል ነው ብሎ አያስብም፤ እነዚህ ግብረ ገባዊ ሕጎች በሰዎች ሕይወት ላይ የሚወረወሩ ድንጋዮች አይደሉምና። ይህ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ በስተጀርባ የተሸሸገ፣ ‹‹በሙሴ መንበር ላይ ተቀምጦ አንዳንድ ጊዜ በአስቸጋሪ ጉዳዮችና በቆሰሉ ቤተሰቦች ላይ በበላይነትና በጥራዝ ነጠቅነት የሚፈርድ›› ድብቅ ልብን ያሳያል። በተመሳሳይ፣ ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት ኮሚሽን እንዳመለከተው፡- ‹‹የተፈጥሮ ሕግ በግብረ ገብ ባለቤት ላይ የተጫኑ ሕጎችን አስቀምጦአል ማለት አይቻልም፤ ይልቁንም የተፈጥሮ ሕግ ጥልቅ ለሆነ ግላዊ ውሳኔ ተጨባጭ የሆነ ቀስቃሽ ምንጭ ነው››። በአላማጅና አለዛቢ ምክንያቶች የተነሣ፣ በግል የማያስወቅስ ወይም ሙሉ በሙሉ የሚያስነቅፍ ኃጢአት ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ፣ አንድ ሰው በእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ ሊኖር፣ ሊወድና የቤተክርስቲያንን እርዳታ እያገኘ በጸጋ ሕይወትና በፍቅር ሊያድግ ይችላል። ደጉንና ክፉውን መለየት ለእግዚአብሔር ምላሽ የሚሰጥባቸውንና በውስንነቶች ውስጥ የማደግ መንገዶችን ለመፈለግ ይረዳል። ሁሉም ነገር ጥቁርና ነጭ ነው ብለን በማሰባችን፣ አንዳንድ ጊዜ የጸጋና የእድገት መንገድን እንዘጋለን፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሰጡ የቅድስና መንገዶችን አናበረታታም። ስለዚህ፣ ‹‹በትልቅ የሰው ልጅ ድክመቶች መሃል ያለ ትንሽ እርምጃ፣ ከውጭ ሲታይ ትክክል ከሚመስል፣ ነገር ግን ትልልቅ ችግሮች ሳያጋጥሙት ቀኑን ከሚያሳልፍ ሕይወት ይልቅ እግዚአብሔርን ይበልጥ ደስ እንደሚያሰኝ እናስታውስ››። የአገልጋዮችና የማኅበረሰብ ተጨባጭ ሐዋርያዊ እንክብካቤ ይህን እውነታ መሳት የለበትም።
በማናቸውም ሁኔታ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ በሙላት የመኖር ችግር ያለባቸውን ሰዎች አያያዝ በተመለከተ፣ የፍቅርን መንገድ የመከተል ጥሪን በግልጽ መስማት ያስፈልጋል። የወንድማማችነት ፍቅር የክርስቲያኖች የመጀመሪያ ትእዛዝ ነው (ንጽ. ዮሐ. 15፡ 12፤ ገላ. 5፡ 14)። ስለዚህ፣ ‹‹ፍቅር ብዙ ኃጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ›› (1 ጴጥ. 4፡8)፤ ‹‹ኃጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፣ ክፋትን ትተህ ለተጨቆኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል›› (ዳን. 4፡27)፤ ‹‹የምትነድድ እሳትን ውሃ ያጠፋታል። ምጽዋትም ኃጢአትን ታስተሰርያለች›› (ሲራክ 3፡ 28) የሚሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አጽናኝ ቃላትን አንርሳ። ቅዱስ አጉስጢኖስም ያስተማረው ይህንን ነው- ‹‹እሳትን ፈርተን እሳቱን ለማጥፋት ለውሃ እንደምንሯሯጥ፣… እንዲሁ የኃጢአት ነበልባል ከገለባችን ሲነሣና ጭንቀት ሲሰማን፣ የምሕረት ሥራ የመሥራት ዕድል ሲናገኝ፣ ቃጠሎውን የምናጠፋበት የውሃ ምንጭ እንደ ተሰጠን ሆነን እንደሰት››።
ምንጭ፡ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 304-306 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ