ካቶሊካዊ የንግድ ሥራ መሪዎች በታይላንድ በእምነት ላይ የተመሰረተ የሥራ አስፈፃሚ ፕሮግራም መጀመራቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በታይላንድ የካቶሊክ የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች እና ባለሙያዎች ህብረት (CBEP) እንዲሁም በፊሊፒንስ የክርስቲያን ነጋዴዎች እና ባለሙያዎች ወንድማማችነት (BCBP) የተዘጋጀው ይህ ፕሮግራም የዓለም አቀፍ የክርስቲያን የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች ህብረት (UNIAPAC) ትብብር አካል እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ የትሥሥር መድረክ ከ 38 አገሮች የተውጣጡ ከ 45,000 በላይ የሥራ አስፈፃሚዎችን የሚወክል ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ በእምነት ላይ የተመሰረተ አመራርን የሚያበረታታ ተቋም እንደሆነም ተነግሯል።
የታይላንድ የካቶሊክ የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች እና ባለሙያዎች ህብረት የትምህርት ተቋም የተመሰረተው ማስተዋልን፣ ኃላፊነት የሚሰማው አመራርነትን እና ሥራን እንደ ጥሪ መረዳትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ እና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ለማጎልበት ታስቦ እንደተቋቋመ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በፊሊፒንስ የክርስቲያን ነጋዴዎች እና ባለሙያዎች ወንድማማችነት ትሥሥር በሃገሪቷ ውስጥ ከ 20,000 በላይ አባላትን በማፍራት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተነሳሽነት መሆኑ ተነግሯል።
የፊሊፒንስ የንግድ ተቋም የሆነው 'ፊንማ ፋውንዴሽን' ሊቀመንበር የሆኑት ቦቢ ላቪና “ሥራ የኃጢአት መዘዝ ሳይሆን የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል ነው” ሲሉ በመርሃ ግብሩ ላይ የተናገሩ ሲሆን፥ ሥራ የተከበረ ነገር እንደሆነ እና ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽ አንድ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፥ ተሳታፊዎቹ በዘመናዊው የንግድ አሠራር ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ላይ በጥልቀት እንዲወያዩ በማስታወስ፥ በአሁኑ ወቅት ንግዱ የሚካሄድበት መንገድ የክርስቶስን ገጽታ እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ ትልቁ ፈተና ምን እንደሆነ ተሳታፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ጠይቀዋል።
የአቬላና የንግድ ሥራዎች ድርጅት ፕሬዘዳንት የሆኑት ጆይ አቬላና በበኩላቸው ይሄንን መንፈሳዊ እሴት በማስተጋባት፥ “እግዚአብሔር ራሱ ሠራተኛ ነው፣ ያውም የመጀመሪያው ሠራተኛ” ካሉ በኋላ “እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ በመፍጠሩ ምክንያት፥ ሰውን ሠራተኛ አድርጎ ፈጥሮታል የሚል ትርጉም ይሰጣል፥ ይህም በመሆኑ እኛ የእግዚአብሔር ተባባሪዎች ነን” በማለት አብራርተዋል።
አቶ አቬላና አክለውም አንዳንድ ሥራን በተመለከተ በሰዎች ዘንድ የተለመዱ አባባሎችን ማለትም “በሥራ ስኬታማ ሆንክ ማለት በህይወትህ ስኬታማ ነህ” የሚለውን ጨምሮ “ክፍያ እስከተከፈለኝ እና ቤተሰቤን እስከረዳሁበት ድረስ ሥራ በቂ ነው” የመሳሰሉ የተሳሳቱ አሉታዊ አመለካከቶችን በመንቀፍ ትክክል እንዳልሆኑ ገልጸው፥ ተሳታፊዎች ተነሳሽነታቸውን እንደገና እንዲመረምሩ እና “በርግጥ ይሄ የእኔ ጥሪ ነው?” ብለው እንዲጠይቁ ካሳሰቡ በኋላ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው እቅድ ምንድን ነው? ብሎ መመርመር እንደሚገባ እና ከትርፍ በዘለለ ተነሳሽነት መመራት እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው ይህ ስብሰባ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች የሚቆጣጠሩ ካቶሊካዊያን ሥራ አስፈፃሚዎችን በአንድ ላይ እንዳሰባሰበም ጭምር ተገልጿል።
ከእነዚህም በተጨማሪ የባንኮክ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፍራንሲስ ዣቪር እና የእስያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን (FABC) ረዳት ዋና ፀሀፊ አባ ዊልያም ላሩሴ በስብሰባው ላይ በመገኘት በእምነት እና በንግድ መካከል ጥልቅ ግንኙነት እንዲኖር የአጥቢያ ቤተክርስትያን ድጋፍ እንደምትሰጥ አፅንዖት በመስጠት ተናግረዋል።
የታይላንድ ካቶሊካዊያን የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች እና ባለሙያዎች ህብረት ሊቀመንበር ጆርጅ ቫራ-ኮርን በበኩላቸው ይህ ተነሳሽነት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ በመግለጽ፥ ከፊሊፒንስ የክርስቲያን ነጋዴዎች እና ባለሙያዎች ወንድማማችነት ጋር በመተባበር በመስራታቸው እና በመጨረሻም ይህን የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ይሄንን ፕሮጄክት ለዓለም አቀፍ የክርስቲያን የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች ህብረት የቦርድ ስብሰባ ላይ እንዳቀረቡ እና የሁለት ሀገራት ነጋዴዎች ይህን አይነት ስልጠና ለካቶሊክ ስራ አስፈፃሚዎች ማካፈላቸው በጣም አስደሳች መሆኑን አስበው እንደነበር፣ እንዲሁም ህብረቱን የበለጠ ጠንካራ እና የእስያ አባላትን የበለጠ ለማስፋፋት እንደሚያስችል መግለፃቸውን ጠቅሰዋል።
አዘጋጆቹ እንዳሉት የታይላንድ የካቶሊክ የንግድ ሥራ አስፈፃሚዎች እና ባለሙያዎች ህብረት አካዳሚ በጸሎት፣ በአላማ እና ለጋራ ጥቅም ቁርጠኝነትን መሰረት ያደረገ የአመራር አቀራረብን በማስተዋወቅ የምስረታ ፕሮግራሞችን በመላው እስያ መስጠቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።