ፈልግ

ሰማዕት ፍሎሪበርት ቧና ቹዊ ሰማዕት ፍሎሪበርት ቧና ቹዊ  

የወጣት ፍሎሪበርት የብጽዕና አዋጅ በሮም ይፋ እንደሚሆን ተነገረ

ዋና ጽሕፈት ቤት በሮም የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ፥ ኮንጓዊ ሰማዕት ፍሎሪበርት ቧና ቹዊ ብጽዕናን በደስታ የተቀበለው መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ምሥራቃዊ ግዛት ጎማ ውስጥ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ኃላፊ ወ/ሮ አሊን ሚናኒ የፍሎሪበርት ቧና የብጽዕና አዋጅ እሁድ ሰኔ 8/2017 ዓ. ም. በሮም በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ በሚፈጸም የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሃገሪቱ የተስፋፋውን ሙስና በመቃወም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2007 ዓ. ም. በ26 ዓመቱ የተገደለው ወጣት ፍሎሪበርት ቧና በጎማ በሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ውስጥ በትጋት ይሳተፍ እንደነበር ተነግሯል። ማኅበረሰቡ በተለይም በጎማ ከሚገኙ አባላት መካከል አንዱ የሆነውን የወጣት ፍሎሪበርት ቧና ብጽዕናን በምስጋና እና በደስታ መቀበሉን አስታውቋል።

ፍሎሪበርት የጎዳና ሕጻናትን ለመርዳት ያለው ቁርጠኝነት

“ወጣት ፍሎሪበርት የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ የመጀመሪያው ብጹዕ ይሆናል” ያሉት ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ ወጣቱ በጎማ ማኅበረሰብ ውስጥ ማገልገል ለሚፈልግ እያንዳንዱ ሰው አስፈላጊ ምሳሌ ሆኗል ብለዋል።

በተለይም በኪስዋሂሊ ቋንቋ “ማይቦቦ” ተብለው የሚታወቁ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመርዳት ቁርጠኛ እንደ ነበር የገለጹት ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ እነዚህ ሕጻናት መጠለያ የሌላቸውም፣ ትምህርት ቤት ያልገቡ፣ ለአሁን ሆነ ለወደፊት ሕይወታቸው ምንም ዋስትና የሌላቸው መሆኑንም ገልጸው፥ ነገር ግን ከወጣት ፍሎሪበርት ትልቅ ትኩረት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ በጎማ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ኃላፊ
ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ በጎማ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ኃላፊ

ፍሎሪበርት፥ የሰላም፣ የአንድነት እና የኅብረት ሰው

ወጣት ፍሎሪበርት ለጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት ካለው ቁርጠኝነት በተጨማሪ የሰላም፣ የአንድነት እና የኅብረት ሰው እንደነበር ወ/ሮ አሊን ሚናኒ ተናግረዋል። 

“የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ያጋራው ፎቶ ወጣት ፍሎሪበርት ከሕጻናት ጋር በማዕድ ዙሪያ ተቀምጦ የሚያሳይ ሲሆን፥ ይህም በማኅብረተሰቡ አዘጋጅነት ለድሆች የተዘጋጀ የብርሃነ ልደቱ በዓል እንደ ነበር ያሳያል። በፎቶ ግራፍ ላይ እንደሚታየው፥ በማዕድ ዙሪያ ሆነው የሚያገለግሉት እና የሚገለገሉት የማይነጣጠሉ ናቸው” ያሉት ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ “የወጣት ፍሎሪበርት ፍላጎትም ያ ነበር” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

እጆችን ንጹሕ በማድረግ  ክፋትን በመልካም ማሸነፍ

ወጣት ፍሎሪበርት በሕይወት ዘመኑ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል የተበላሸ ሩዝ እንዳይላክ በመከልከሉ እና ሙስናን በመቃወም በ26 ዓመቱ በሰማዕትነት መሞቱ ይታወሳል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ባደረጉበት ወቅት በኪንሻሳ በሚገኝ የሰማዕታት ስታዲየም ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ወጣት ፍሎሪበርት አፈና፣ ስቃይ እና በመጨረሻም ግድያ ተፈጽሞበት ለወጣቶች ታላቅ አብነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ማንም በማያውቀው መንገድ ከፍተኛ ግፍ እንደተፈጸመበት፣ በርካታ ገንዘብ ማግኘት የሚችል የነበረ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ክርስቲያን በጸሎት፣ ለሌሎች በማሰብ ሙስናን መቃወም የመረጠ ወጣት እንደነበር ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሞገስ እና ሃብት የሚሰጣችሁ ቢሆንም ነገር ግን በመታለል ወጥመድ ውስጥ እንዳትገቡ” በማለት ወጣቶችን መምከራቸው ይታወሳል።

“የኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ እና የአፍሪካ ወጣቶች ይህንን ጥሪ ተቀብለው የወጣት ፍሎሪበርትን ፈለግ በመከተል አዲስ ታሪክ መፃፍ ይችላሉ” ያሉት ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ “ወጣቶች የእርሱን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ ከእሱ ጋር የሚመሳሰሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ትክክለኛውን ምርጫ እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ ያውቃሉ”  ሲሉ ተናግረዋል።

ወጣት ፍሎሪበርት እንዳደረገው ሁሉ ወጣቶች ቅዱሳን መጽሐፍትን ደጋግመው እንዲያነቡ መክረው፥ የእርሱ መጽሐፍ ቅዱስ በሮም በሚገኝ በቅዱስ ቤርተሎሜዎስ ባዚሊካ ውስጥ በክብር ተቀምቶ እንድሚገኝ ገልጸዋል።

ፍሎሪበርት ለፖለቲካ መሪዎችም አብነት ነው

ከወጣቶች በተጨማሪ የፍሎሪበርት ሕይወት ሌሎችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊያነሳሳ እንደሚችል የተናገሩት ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ በሀገራቸው ውስጥ ማኅበራዊ ዘርፍ ከቀን ወደ ቀን እየተበላሸ መሆኑን አስታውሰዋል።

ወጣት ፍሎሪበርት፥ “ሁሉም ሰው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀመጥባትን ኮንጎ አልማለሁ” ብሎ በተናገረው መሠረት የኮንጎ ነዋሪዎች ለሀገራዊ አንድነት እንዲሠሩ ወ/ሮ አሊን ሚናኒ አሳስበዋል።

ወ/ሮ አሊን ሚናኒ፥ ለታላላቅ ሃይቆች ክልል መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የሁሉም ሰው ሕይወት ለሁሉም ሰው ነው” ብለው፥ እንደ ፍሎሪበርት ያሉ ደፋር ምርጫዎችን በማድረግ ክፉን በመልካም መዋጋት፣ ግድያን እና ደም ማፍሰስን በማስቆም ሰላምን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰላምን በማምጣት ሁሉም አሸናፊ ይሆናል

ወይዘሮ አሊን ሚናኒ የፍሎሪበርት ብጽዕና ለመላው የኮንጎ ሕዝብ ደስታን የሚያመጣ እንዲሆን፣ የኮንጎን ሕዝብ አንድ በማድረግ እና በአገራቸው ስላለው ሁኔታ እንዲወያዩ የሚያበረታታ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በሮም በሚገኝ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ የሚፈጸም የብጽዕና መስዋዕተ ቅዳሴን ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ፥ ከብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ፣ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ እና ከብጹዕ አቡነ ዊሊ ንጉምቢ፥ የፍሎሪበርት የትውልድ ሥፍራ ጎማ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በኅብረት እንደሚያሳርጉት ታውቋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ የፍሎሪበርት ቤተሰብ፣ በሮም የሚገኝ የኮንጎ ማኅበረሰብ እና የኮንጐ መንግሥት ተወካዮች እንደሚገኙ ታውቋል።

 

 

 

14 Jun 2025, 17:09