በፔሩ ተራራማ አካባቢዎች የሠፈሩት የቬነዙዌላ ስደተኞች ዕርዳታን እያገኙ እንደሆነ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከባሕር ጠለል በ3,000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚትገኝ የፔሩ ኩዝኮ ከተማ በአንዴስ ተራሮች ላይ የተቆረቆረች እና በደረቃማ የአየር ጸባይ የምትታወቅ ስትሆን ነዋሪዎችዋ እንግዳ ተቀባዮች እንደሆኑ ተነግሯል።
በአንድ ወቅት የኢንካ ግዛት የስልጣኔ ዋና ከተማ በሆነች የኩዝኮ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቬነዙዌላ ስደተኞች የሠፈሩባት ሲሆን፥ ከስደተኞቹ መካከል ብዙዎቹ በአገራቸው ሊያጋጥም የሚችል አደጋን እና ድህነትን በማምለጥ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሺዎች የሚቆጠሩ አደገኛ እና አድካሚ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዙ ናቸው።
ከየአገራቱ የሚደርስላቸው ዕርዳታ
በሰላም ወደ ኩዝኮ ከተማ መድረስ የቻሉ የቬንዙዌላ ስደተኞች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2025 ዓ. ም. መጀመሪያ ጀምሮ፥ በጣሊያን የታክስ ልገሳ ፕሮግራም እና በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተነሳሽነት በተቋቋመ “አፑሪማክ ኢትስ” ከተሰኘ ክርስቲያናዊ የጣሊያን የዕርዳታ ድርጅት ድጋፍን አግኝተዋል።
የዕርዳታ ፕሮጀክቱን ማርታ የተባለች ጣሊያናዊት ወጣት የምትመራው ሲሆን፥ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፥ በፔሩ የሚገኝ የቬነዙዌላ ስደተኛ ማኅበረሰብ ሰፊ መሆኑን ገልጻ፥ ዕርዳታው መጀመሪያ የሚደርሳቸው ብዙውን ጊዜ የፔሩ ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ እና አስተዳደራዊ ሥርዓቶችን አልፈው ለሚመጡ ስደተኞች እንደሆነ አስረድታለች።
የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤታቸው፥ ስደተኞቹ በፔሩ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት የሚያግዙ ሂደቶችን እና የጤና አገልግሎትን ለማመቻቸት የሚሠራ መሆኑን ገልጻ፥ ተቀባይነት ያለው የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት መብት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር ለሆኑ ቬንዙዌላውያን ሴቶች ብቻ እንደሆነ አስረድታለች።
ስደተኞቹ ከሚገጥሟቸው እጅግ አስቸኳይ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጤና እንክብካቤን ማግኘት እንደሆነ የገለጸችው ወጣት ማርታ፥ በዚህ ምክንያት ፕሮጀክቱ ውጤታማ የጤና አገልግሎቶችን በኩዝኮ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ሳንታ ሪታ ሆስፒታል ጋር እንደሚያመቻች እና ይህን የሚያደርገው በጤና ሥርዓቱ መመዝገብ የማይችሉትን ወይም በረጅም ወርፋ ምክንያት የተገለሉ ቬነዙዌላውያን የጤና ፍላጎቶች ለማሟላት እንደሆነ አስረድታለች።
ሌላው የአፑሪማክ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወሳኝ ጉዳይ በቬንዙዌላውያን ስደተኛ እናቶች፣ ትናንሽ ሕጻናት እና እርጉዝ ሴቶች መካከል የሚታይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሲሆን፥ ለዚህ ተጋላጭ ቡድን የታለሙ የአመጋገብ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ወጣት ማርታ አስረድታለች።
በቅዱስ አጎስጢኖስ የበጎነት ምግባር የሚመራ ማኅበር
በኩዝኮ ከተማ ውስጥ የአፑሪማክ የበጎ አድራጎት ድርጅት ዕለታዊ ጥረቶች በአብሮነት እና በሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር መንፈሳዊ ፍቅር ላይ የተመሠረተ እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ተልዕኮዎቹ ውስጥ ለሰብዓዊ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚመራ መሆኑ ታውቋል።
የአፑሪማክ በጎ ፈቃደኞች በዚህ ወሰን በሌለው የፍቅር መንፈስ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደ ፔሩ ከደረሱ ስደተኞች ጎን መቆማቸውን ገልጻ፥ ነገር ግን ስደተኞቹ ከኅብረተሰቡ ጋር ሙሉ በሙሉ ለመዋሃድ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን አስረድታለች።
ምንም እንኳን ዛሬ የመጡ ባይሆኑም አሁንም ቢሆን በማኅበራዊ ትስስር ላይ ትልቅ ፈተናዎች እንዳሉባቸው ገልጻ፥ “ብዙዎች በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ባለመሆናቸው መደበኛ ሥራን የማግኘት መብት ስለሌላቸው የመኖሪያ ፈቃድ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል” ስትል ተናግራለች።
ለምን ረጅም መንገድ ተጓዙ?
ሌሎች አማራጭ መንገዶች ቢኖሩም ብዙውን ጊዜ ስደተኞቹ ኩዝኮን ለመድረስ በኮሎምቢያ እና ኢኳዶር በኩል እንደሚያልፉ የገለጸችው ወጣት ማርታ፥ የቬነዙዌላውያን ስደት በዋነኛነት ወደ መላው የላቲን አሜሪካ አገራት የተደረገ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል እና በኩዝኮ ውስጥ የቬንዙዌላ ማኅበረሰብ ይበልጥ የተረጋጋ እንደሆነ አብራርታለች።
የዚህ የጅምላ ስደት ዋነኛ መንስኤ በቬነዙዌላ ውስጥ ጥሩ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት አለመኖር መሆኑን ወጣት ማርታ ገልጻ፥ በተጨማሪም እነዚህ ስደተኞች ከትውልድ አገራቸው ጋር ምን ያህል በስሜት የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግራ፥ ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቬነዙዌላ የመመለስ ህልም እንዳላቸው እና ባለፉት ዓመታት ውስጥ የስደት መጨመር አለመታየቱን እና አጠቃላይ ፍሰቱ የተረጋጋ መሆኑን አስረድታለች።
በራስ ጥረት ወደፊት መጓዝ
ዛሬ የአፑሪማክ የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩዝኮ ውስጥ የሚሠራ ብቸኛው የዕርዳታ ድርጅት እንደሆነ የምትናገረው ወጣት ማርታ፥ ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ በአካባቢው ይሠራ ነበር አስታውሳለች።
ኃላፊነቱ ከባድ ቢሆንም ከመንፈሳዊ ማበረታቻ ጥንካሬን በማግኘት እና የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል የሆኑት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጥ ለሥራቸው አዲስ ጉልበት እና ብሩህ ተስፋ እንደሰጣቸው ወጣት ማርታ እና በጎ ፈቃደኞቿ ገልጸዋል።