የናይጄሪያ ሊቀ ጳጳስ 'ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መመረጣቸው እግዚያብሄር በሥራ ላይ እንዳለ ያመላክታል' አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ አንድ ወር የሞላቸው ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ አልፍሬድ ስለ ብጹእነታቸው ያላቸውን ሃሳብ፣ ምኞት እንዲሁም በሃዋሪያዊ መሪነት ዘመናቸው ቤተክርስቲያን ምን ልታገኝ እንደምትችል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ ብጹእነታቸው መመረጣቸው ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ መልኩ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳረፉ እንዲሁም ከሁሉም ምልክቶች እና እስካሁን ከተፈጸሙት ሁነቶች ሁሉ ማስተዋል እንደሚቻለው እርሳቸው ዛሬ ለቤተክርስቲያናችን እና ለዓለማችን ትክክለኛ ምርጫ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ከተለያዩ አከባቢ የመጡ ሰዎች እንደሚናገሩት በዚህ ምርጫ አማካይነት እግዚአብሔር በሥራ ላይ እንደሚገኝ ያመኑ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ስለዚህም እግዚአብሔርን ስለ እርሳቸው እናመሰግናለን በማለትም አክለዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አንዳንድ ምልክቶች፣ የሚናገሩበት መንገድ እና የተናገሯቸው ነገሮችም አበረታች እንደነበሩ ያነሱት ሊቀ ጳጳስ አልፍሬድ፥ ‘በእርግጥም በዚህ ጊዜ እሳቸውን በማግኘታችን እግዚአብሔር በሥራ ላይ እንዳለ ጥሩ ማሳያ ነው’ ብለዋል።
በርዕሰ ሊቃነ ጳጳስነት በመመረጣቸው ምክንያት የተጣለባቸውን የተለያዩ ሃላፊነቶች በጽናት እንዲወጡ ብሎም ብርታቱን እና ጸጋውን እንዲሰጣቸው፣ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ሥራቸውን እንዲመሩ ወደ አምላክ መጸለይ እንደሚገባም ጭምር አስታውሰዋል።
የሰላም ድምፅ
ከዚህም ባሻገር በዓለም ላይ እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የሰላም ድምጽ ሆነው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ እና ለዚህም እንደሚጸልዩ በመግለጽ፥ ድርጊቶቻቸው እና ውሳኔዎቻቸው በዓለም ላይ ሰላምን ለማምጣት እንደሚሰሩ በተለይም በጋዛ፣ ዩክሬን እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ሰላምን በማስመልከት የሚያደርጓቸው ንግግሮች አበረታች እንደሆኑ በመጥቀስ፥ “የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግር በእርግጠኝነት እርሳቸውን በሚያዳምጡ ሰዎች ሁሉ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብለዋል።
“ምክራቸውን እንደሚከተሉ ተስፋ እናደርጋለን” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ አሁን ያለውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው የቤተክርስቲያንን አንድነት ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ በመጥቀስ፥ አሁን እየታዩ ያሉት ምልክቶች በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ካሉት የተለያዩ ቡድኖች እና ቦታዎች መካከል ድልድይ እንደሚገነባ ከወዲሁ ያመላክታሉ በማለት ገልጸዋል።
በእግዚአብሔር ረዳትነት፣ ቤተክርስቲያኒቷ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አብባ እንደምትቀጥል ብዙ እንደሚጠብቁ እና ለእርሳቸውም መጸለያቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አፍሪካን እንዲጎበኙ በጉጉት እንጠባበቃለን
የአፍሪካ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅርቡ ወደ አፍሪካ መጥተው እንደሚጎበኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ብጹእነታቸው ከዚህ በፊት ናይጄሪያን ብዙ ጊዜ ጎብኝተው ስለነበር የሃገሪቷን ሁኔታ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ካነሱ በኋላ “ከእኛ የቅዱስ አውገስጢኒዮስ ማህበር ወንድሞቻቸው ጋር ጥሩ ቀረቤታ እና መረጃ አላቸው” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የናይጄሪያ ፕረዚዳንት ብጹእነታቸው በግል ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት በርዕሰ ሊቃነ ጵጵስናቸው ሥነ ስርዓት ላይ እንደተገኙ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አልፍሬድ፥ በመጨረሻም በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሃገሪቷ ብጹአን ጳጳሳት ናይጄሪያን እንዲጎበኙ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መደበኛ ግብዣ ሲያቀርቡ ፕረዚዳንቱ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ማሳወቃቸውን እና ይሄንን በጉጉት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።